በቡራዩ፣ አዲስ አበባና ሐዋሳ በነበሩ ግጭቶች ተሳትፈዋል በተባሉ 209 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ መመስረቱን የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ገለጸ።
በመስከረም የመጀመሪያ ቀናት በቡራዩና በአዲስ አበባ ከተማ ተከሰቶ በነበረው ሁከትና ብጥብጥ ተሳትፈዋል በተባሉ 109 ሰዎች ላይ ክስ ተመስርቷል። ከተከሳሾቹም 81ዱ በማረሚያ ቤት ሲገኙ፣ 28ቱን ለመያዝ እያደንኳቸው ነው ብሏል።
በቡራዩው ግጭት የ37 ሰዎች ሕይወት ሲጠፋ፣ በ315 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱንም ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ባሳለፍነው ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 24 በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
በተያዘ ዜና በሐዋሳ ከተማና ማረሚያ ቤት ተነስቶ በነበረው ግጭት 100 ተከሳሾችን የያዙ ኹለት መዝገቦች ተጣርተው ክስ የተመሰረተ ሲሆን፣ 75 ተጠርጣዎች የሚገኙበት ሦስተኛው መዝገብ ምርመራ እየተጠናቀቀ መሆኑም ተመልክቷል።
በሌላ ዜና ሰኞ፣ ታኅሣሥ 29 የሚከበረውን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ ለ538 የፌደራል የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ መደረጉ ተገልጿል። ይቅርታው ሕፃናት ልጆችን ይዘው በማረሚያ ቤት ለሚገኙ እናቶችና ዕድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ ለሆኑ ታራሚዎች ቅድሚያ መስጠቱም ተነግሯል።
ቅጽ 1 ቁጥር 8 ታኅሣሥ 27 ቀን 2011