መነሻ ገጽማረፊያሰሞነኛበትግራይ ‹‹ረሃብ አንዣቧል!?››

በትግራይ ‹‹ረሃብ አንዣቧል!?››

ጥቅምንት 24 የሕወሓት በሰሜን ዕዝ ሠራዊት አባላት ላይ ድንገተኛ ጥቃት ከፈጸመና የፌደራል መንግሥት ሕግ የማስከበር ያለውን ዘመቻ ባወጀ በሦስት ሳምንታት አጠናቅቂያለሁ ብሏል። የክልሉን ርዕሰ ከተማ መቐለን ተቆጣጥሯል፤ ከብልጽግና እና በክልሉ ውስጥ ይንቀሳቀሱ ከነበሩት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተወጣጣ ጊዚያዊ መንግሥት አቋቁሞ የመንግሥት መዋቅርን እንደአዲስ በመገንባት ላይ እንደሆነ መግለጫዎችም እያሳወቀ ይገኛል።

የሕግ ማስከበሩ ዘመቻ አልቆ መከላከያ ሠራዊቱ በሕግ የሚፈለጉ የሲቪል እና ወታደራዊ አመራሮችን ያሉበትን በማነፍነፍ ለሕግ የማቅረብ ርብርብ ላይ መሆኑን በተደጋጋሚ ማስታወቁ ይታወቃል። በዚህም የሕወሓት ቁንጮ ባለሥልጣናት የነበሩት አቦይ ስብሃትንና አባይ ወልዱን የመሳሰሉት ባለሥልጣናት በቁጥጥር ሥር ሲውሉ፤ ስዩም መስፍን፣ አባይ ጸሐዬ እና ሽመልስ ወልደሥላሴ መደምሰሳቸው በይፋ ተነግሯል። የሕወሓት ሊቀመንበር እንዲሁም የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የነበሩት ደብረጽዮን ግብረሚካኤል (ዶ/ር)፣ ጌታቸው ረዳ እና የቀድሞው የደህንነት ሹም ጌታቸው አሰፋ እምጥ ይግቡ ስምጥ ሳይታወቅ እስካሁን በመታደን ላይ ናቸው።

ከሕግ ማስከበሩ እና የትግራይ ክልል መንግሥታዊ መዋቅርን መልሶ የመገንባት ሥራዎች በመከናወን ላይ ቢሆኑም የትግራይ ሕዝብ ከፍተኛ ፈተና ከፊቱ ተደቅኗል፤ ‹‹ረሃብ››። ከረሃብ ማንዣበብ ጋር በተያያዘ የተለያዩ እርስበርሳቸው የሚቃረኑ መረጃዎች እየተለቀቁ ሲሆን አንዳንዶቹ እጅግ በጣም የሚያሳቅቁና የሚያሸማቅቁ ናቸው።

ቢቢሲ አማርኛ በሰኞ፣ ጥር 10 ዘገባው ‹‹ትግራይ፡ ‘በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ ምክንያት ሊሞቱ ይችላሉ’›› በሚል ርዕስ አስነብቧል። ዘገባውን አገኘኹት የሚለው አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን ከእርዳታ ሠራተኞች ጋር ካደረጉት ስብሰባ ላይ ሾልኮ የወጣ ማስታወሻ ላይ ከሰፈረ ጽሁፍ መሆኑን ጠቅሷል። የመረጃው ምንጭ አጠራጣሪ ቢሆንም መሬት ላይ ያለው እውነት ግን በክልሉ የሚገኙ ሰዎች አፋጣኝ ሰብኣዊ እርዳታ ማግኘት እንዳለባቸው ግን መካድ እንደማይቻል የብዙዎች እምነት ነው።

ይኸው ዘገባ ጨምሮም ምግብ አለመኖር ወይም በገበያ ላይ ያለው አቅርቦት ውስን መሆን እየባሰ የሚሄድ የምግብ እጥረት አደጋን እየፈጠረ መሆኑን ከተባበሩት መንግሥታት መግለጫ መረዳቱንም አስፍሯል። በመንግሥታቱ ድርጅት ሪፖርት መሰረትም አሁን በትግራይ ክልል 4.5 ሚሊዮን ሕዝብ የአስቸኳይ እርዳታ ጊዜ የምግብ እርዳታ ያስፈልገዋል ብሏል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ በትግራይ ረሃብ ተከስቷል እንዲሁም 4.5 ሚሊዮን ሕዝብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልገዋል የሚለውን እንደማይቀበል በብሔራዊ የአደጋ እና ስጋት ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ በኩል አስታውቋል። ከሚሽነሩ ኀሙስ፣ ጥር 13 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በክልሉ ከዚህ ቀደም በ‹‹ሴፍቲኔት›› ከታቀፉት 1.2 ሚሊዮን ሕዝብ ጨምሮ ለ1.8 ሚሊዮን ሕዝብ የዕለት ደራሽ እርዳታ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ይኸው ኮሚሽኑ ባስጠናው መሰረት በክልሉ ተጨማሪ 110 ሺሕ ሰዎች ከተለያዩ አካባቢዎች በግጭቱ ምክንያት የተፈናቀሉ መኖራቸውን እንዲሁም በጥናት የደረሳባቸው ደግሞ 700 ሺሕ ሰዎች እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ማረጋገጡን ጨምሮ አስታውቋል።

ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው ኮሚሽኑ በቂ እህል እንዳለው እና ወደ ክልሉ መላኩን እንዲሁም ተጨማሪ እህሎችንም ከውጪ እያስገባ መሆኑን ጠቅሰው፥ ትልቁ ተግዳሮት ሆኖ ያገኙት ግን ስርጭቱን በተመለከተ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተዋል። የመሰረተ ልማት መጎዳት፣ የስርጭት መዋቅር ዝርጋታ እና አልፎ አልፎ ከጸጥታ ጋር በተያያዙ የሚገጥሙ ችግሮች መሆናቸውንም ገልጸዋል። የተረጂ ቁጥር መጋነን በተመለከተም ዓለም ዐቀፍ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ጋር በተያያዘ የተገባበት አላስፈላጊ ፍክክር መሆኑን በገደምዳሜው ኮሚሽነር ካሳ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ ተናግረዋል።

በተያያዘ ከእርዳታ ልግስናና ማሰባሰብ ጋር በተያያዘም በውጪ የሚኖረው በተለይ ትግራዋይ ከቀናት በፊት 2.5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ማሰባሰብ የቻሉ ሲሆን እርዳታው ግን ለተፈለገለት ዓላማ አልዋለም፤ ምክንያቱ ደግሞ በገንዘብ አሰባሳቢዎች በኩል በተነሳ ውዝግ መሆኑ በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ላይ በሰፊው ሲነገር ሰንብቷል። በሌላ በኩል ደግሞ በግሉ ተነሳሽነት ናትናኤል አስመላሽ የሚባል ግለሰብ በ‹‹ጎፈንድሚ›› እስከ ትላንት አርብ፣ ጥር 14 ድረስ ከ32 ሺሕ ዶላር በላይ ማሰባሰቡ ታውቋል።

የአዲስ አበባ መስተዳደር በበኩሉ ለክልሉ 18.3 ሚሊዮን ብር የሚገመት የምግብ እህል ማለትም ኹለት ሺሕ ኩንታል ጤፍ፣ ኹለት ሺሕ ኩንታል ስንዴ እና ኹለት ሺሕ በቆሎ ድጋፍ አድርጓል።

የሆነው ሆኖ ዜጎች የሰብአዊ እርዳታ ማግኘት አለባቸው፤ በረሃብ አንድም ሰው መሞት የለበትም የሚሉ ድምፆች በከፍተኛ ደረጃ በመሰማት ላይ ናቸው።

ቅጽ 2 ቁጥር 116 ጥር 15 2013

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች