በግዮን ሆቴል

0
967

በኢትዮጵያ የሆቴል ዘርፍ ቀዳሚ ከሆኑት መካከል አንዱ የሆነው ግዮን ሆቴል ባለበት ከፍተኛ አስተዳደራዊ ችግሮች ምክንያት ተገቢውን ጥቅም እያገኘ አለመሆኑን የሆቴሉ ሠራተኞች ገለጹ። በአሁኑ ወቅት ሆቴሉ በኪሳራ እንደተዘፈቀና በየዕለቱ በሆቴሉ የሚስተናገዱ ደንበኞች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሰራተኞች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል ።
በሆቴሉ ውስጥ ያለው አስተዳደራዊ ብልሽት ሆቴሉን እያጋጠሙት ላሉት ችግሮች ዋነኛው ምክንያት እንደሆነ የሚያምኑት ሰራተኞቹ፣ በተለይም ሕጋዊ ጨረታን ባለተከተለ መንገድ የተለያዩ ግዢዎች በሆቴሉ እንደሚፈጸሙ አመልክተዋል፡፡ ሽያጭ የተከናወነባቸው ደረሰኞች ሕጋዊነት የሌላቸው መሆናቸውንም ይናገራሉ።
ከዚህ ቀደም ለተለያዩ ክፍሎች እድሳት በሚል ከባንክ ከ18 ሚሊየን ብር በላይ ብድር ተፈጽሟል የሚሉት ቅሬታ አቅራቢ ሠራተኞቹ ላለፉት 18 ወራት በሆቴሉ ቅጥር ግቢ የታየ ለውጥም ሆነ ዕድሳት የለም ሲሉም ወቅሰዋል፡፡
በየጊዜውም በሆቴሉ ለመስተናግድ የሚመጡ እንግዶች የሚፈለጉትን አርኪ አገልግሎት እንደማያገኙና በተደጋገሚ ቅሬታዎችን ለሆቴሉ አስተዳዳርና ሠራተኞች እንደሚገልጹም ሠራተኞቹ አክለው ገልጸዋል። በሆቴሉ እየባሰበት ስለመጣው ችግር አስተያየት በምንሰጥበት ወቀትም ዛቻና ማስፈራሪያ ይደርስብነናል ሲሉም ያስረዳሉ።
ከምግብና መሰል አገልግሎቶች ጋር በተያያዘ የጥራት ችግር አለ የሚሉት ሠራተኞቹ እንደ ሥጋ ያሉ የምግብ ውጤቶች ከተማው ውስጥ ከሚገኙ ጥቂት ሱፐር ማርኬቶች ብቻ ለመጠቃቀም በሚል የግዢ ሥርዓቱን ባልጠበቀ መልኩ እንደሚከናወንም እናውቃለን ይላሉ፡፡
የምግብ ግብዓቶቹም ብዙ ጊዜ አገልግሎት ላይ ሳይውሉ እንደሚቀመጡና በጤና ላይ ችግር እየፈጥሩ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ቅሬታ ያሰሙ ሠራኞች ተናግረዋል። በሆቴሉ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የጥቅም ትስስር አለ የሚሉት ሠራተኞቹ በሆቴሉ ባሉ አንዳንድ ኃላፊዎች ዶላርን በትይዩ (ጥቁር) ገቢያ እስከመመንዘር የደረሰ ሕገ ወጥነት መንሰራፋቱንም ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል ከመጋረጃ ግዢ ጋር በተያያዘ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ሳይሰጡ በመጋዘን ውስጥ የተቀመጡ መጋረጃዎች እያሉ ሌላ ጨረታ በማውጣት አዳዲስ መጋረጃዎችን እንዲገዙ ተደርጓልም ይላሉ፡፡
ከ397 በላይ ቋሚ ሠራተኞች ያሉት ሆቴሉ ላለፉት ዓመታት አልባሳትን ጨምሮ ለሰራተኛው ምንም ዓይነት ጥቅማጥቀሞችን እንዳልፈጸመ የሚገልጹት ቅሬታ አቅራቢዎቹ በሆቴሉ አስተዳደር መማረራቸውንም ተናግረዋል።
በሠራተኞቹ ቅሬታ የማይስማማው የሆቴሉ አስተዳደር ያለ ሕጋዊ ሥርዓት የተደረገ የጨረታነ ግዥ ስምምነት የለም ብሏል፡፡ የግዮን ሆቴል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሙሉጌታ እሸቴ ለአዲስ ማለዳ ሲገልጹ ‹‹ለእያንዳንዱ ለምናከናውናቸው ግዢዎች ሪፖርት እናቀርባለን አንድም በድብቅ የተካሄደ ስምምነት የለም›› ብለዋል፡፡ ለምግብነት የሚውሉ እንደ ስጋ ያሉ ግብዓቶችም በከተማዋ ከሚገኙና ሕጋዊ ከሆኑ ተቋማት በሕጋዊ ጨረታና የግዥ ሥርዓት እንደሚገዙም ገልጸዋል።
ስራ አስኪያጁ ይህን ይበሉ እንጂ ሰራተኞቹ ከኹለት ያልዘለሉ ድርጅቶች በጨረታ ሒደት ውስጥ በማስገባት ብቻ ነው እስካሁን ግዢ እየተፈጸመ ያለው ባይ ናቸው።
ከ18 ሚሊዮኑ ብር የባንክ ብድር ጋር በተያያዘም ሆቴሉ ለዕድሳት አገልግሎት መበደሩን በመጥቀስ ያለአግባብ ወጪ አለማውጣቱንም አንስተዋል፡፡ ከመጋረጃ ጋርም ቢሆን ሳያስፈልግ የተገዛ መጋረጃ የለም ብለዋል፡፡
ባለፈው ዓመት ከነበረው የኢትዮጵያ ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ ጋር ተያይዞ በሆቴሉ የደንበዮች ቁጥር እና የገቢያ መቀዛቀዝ ታይቶ እንደነበር የሚናገሩት ሙሉጌታ አሁን ላይ ሆቴሉ የተሻለ ገቢ ሊያገኘ ሚችልባቸውን ሥራዎች እየከወነ መሆኑን ገልጸዋል። በ1941 ተቋቁሞ የሆቴል አገልግሎትን መስጠት የጀመረው ግዮን ሆቴል በመንግሥት የልማት ድርጅት ውስጥ የሚተዳደር የአገልግሎት ሰጪ ተቋም ነው፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 9 ጥር 4 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here