ሰላም እና መረጋጋት ለዴሞክራሲያዊ ሽግግር ቅድመ ሁኔታ ነው

0
662

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት የሰው ሕይወት መጥፋት ምክንያት እየሆኑ ናቸው። ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚከሰቱት ግጭቶች መልካቸውንና ቦታቸውን እየለወጡ በርካታ የአገሪቱን ክፍሎች በመሸፈን ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር ከማድረግም ባሻገር ዜጎች በሰላም ወጥቶ በሰላም የመግባት ሥጋት እየተፈጠረባቸው ይገኛል።
የመንግሥት አስተዳደር የተጀመረውን የሽግግር ዘመን በማስቀጠልና ከፍተኛ ቁርጠኝነት የሚጠይቁ ውሳኔዎችን እና እርምጃዎችን እየወሰነ አገር የመምራቱን ሚና እንደቀጠለበት አዲስ ማለዳ ታምናለች። አዲስ ማለዳ እስከ ቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ድረስ የዐቢይ አስተዳደር ‘ሊከውናቸው የሚገቡ ወሳኝ ሥራዎች ምንድን ናቸው?’ በሚል ለተደራስያን ባቀረበችው የበይነመረብ የአስተያየት መጠይቅ ባገኘችው ግብረ መልስ መንግሥት በቅደም ተከተል ሊያከናውናቸው የሚገቡ ናቸው የተባሉትን አምስት ዋና ዋና ጉዳዮች መለየት ችላለች። ከነዚህም ውስጥ ‘ሰላምና መረጋጋትን ማስጠበቅ’ ሁሉም መልስ ሰጪዎች ያነሱት እና እያሳሰባቸው ያለ ጉዳይ ነው። ሌሎቹ ብዙዎቹ መልስ ሰጪዎች የተስማሙባቸው የመንግሥት የቤት ሥራዎች ከሰላምና መረጋጋት ጋር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚገናኙ ናቸው። እነዚህም፦ ጠርዝ የረገጠ ብሔርተኝነትን ማለሳለስ፣ የምጣኔ ሀብት መነቃቃት መፍጠር፣ ሕዝባዊ ውይይትና ተቋማዊ መሻሻል/ተሐድሶ ማድረግ እና ለውጡ እንዳይደናቀፍ መሥራት የሚሉት ናቸው።
አዲስ ማለዳ ከተደራሲያን ግብረ መልስ መረዳት እንደቻለችው መንግሥት በቀዳሚነት የሰላም እና መረጋጋት ሥራዎችን እንዲሠራ ብዙኀን ይጠብቃሉ። አለበለዚያ ለውጡ እና ሽግግሩ አዎንታዊ ፍፃሜ ላያገኝ ይችላል የሚል ሥጋት አለ። የብሔርተኝነት ጉዳይ ለሰላምና መረጋጋት የሚሆነው የተለያዩ ብሔሮችን እንወክናለን የሚሉ የፖለቲካ ቡድኖች እና ግለሰቦች እንክለዋለን የሚሉትን የማኅበረሰብ ክፍል በመወገን ከሌሎች ጋር ግጭት ውስጥ ይገባሉ። ይህም ሰላማዊውን የሕዝቦች ኑሮ እና የፖለቲካ ሽግግር ያደናቅፈዋል የሚል ስጋት አለ። እስካሁን የተከሰቱት ግጭቶችም ቢሆኑ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች በነጻነት የመንቀሳቀስ ገደብ እያስከተሉ ስለሆነ ቀድሞም በሕዝባዊ ተቃውሞዎቹ ወቅት የተጎዳው ምጣኔ ሀብታችን ከጉዳቱ እንዳያገግም፣ እንዲያውም ተባብሶ እንዲቀጥል መንስዔ ሆኗል። ስለሆነም ሰላምና መረጋጋት ላይ መሥራት ተደራሲዎቻችን ‘ምጣኔ ሀብቱን ማነቃቃት ያስፈልጋል ለሚለው’ ምላሻቸው አንድ መልስ ይሆናቸዋል ብለን እናምናለን።
የተቋማት ቅቡልነት ማጣት እና ገለልተኛ አለመሆንም እንዲሁ ከሰለምና መረጋጋት ማጣት ጋር የሚያያዙ ነገሮች ናቸው። መንግሥት የተቋማትን ሥር ነቀል የመልሶ ማዋቀር፣ ገለልተኝነት ማረጋገጥ እና ሕዝባዊ አገልጋይነት ማበረታታት ከቻለ በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ እየተከሰቱ ያሉ ችግሮችን በፍትሕ አካላት በኩል መፍታት ይቻለዋል ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች። በተጨማሪም፣ መንግሥት ደጋግሞ እንደገለጸው እና የአዲስ ማለዳ ተደራስያንም እንዳመላከቱት ለውጡን ሊቀለብሱ የሚያስቡ የቀድሞው ብልሹ ሥርዓት አመራሮች ግጭቶችን እዚህም እዚያም እያበረታቱ እና እያነሳሱ በመሆኑ፥ በፍትሐዊ ሕግ አግባብ እነዚህን አካሔዶች እርምት በመስጠት አንድም የአገሪቱን ሰላም፣ አንድም ደግሞ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረገውን ሽግግር ስኬታማ ያደርገዋል።
ሰላም ለዜጎች ደኅንነት፣ ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላው ቦታ እንዳሻቸው ለመንቀሳቀስ ወይም በመንቀሳቀስ ሠርቶ ለማደር፣ መሠረታዊ ጉዳይ ከመሆኑም በላይ ለአገር ምጣኔ ሀብትም ይሁን አሁን ለተጀመረው የፖለቲካ ምኅዳሩን ማስፋት እና ለሁሉም ሁሉም መክረው የሚወስኑባት፣ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመመሥረት ቅድመ ሁኔታ ነው። አዲስ ማለዳ ሰላም ከሌለ በኢትዮጵያ የወጣችው የተስፋ ጀምበር መልሳ ትጠልቃለች ብላ ታምናለች።
ይሁንና መንግሥት የዴሞክራሲ ምኅዳሩን ለማስፋት ቃል የገባውን ያህል ለሰላም ቁርጠኛ እርምጃ እያሳየ አይደለም። ምንም እንኳን ለሰላም የዜጎችም ተሳትፎ አስፈላጊ ቢሆንም፣ በየክልሉ አንዳንድ ቦታዎች ነፍጥ አንግተው የሕዝቡን ፀጥታ የሚያውኩ ቡድኖች የዜጎችን ፍላጎት ይወክላሉ ማለት አይቻልም። መንግሥት አገሪቱ ከከፍተኛ የአፈና እና የማግለል ሥርዓት መመለሷ እንደመሆኑ መጠን፣ ለለውጥ ያለውን ቁርጠኝነት በማሳመን እና ዋስትና በመስጠት እንዲሁም መልሶ ማቋቋሚያ መንገዶችን በማመቻቸት ትጥቅ ያልፈቱ ቡድኖችን እና በዜጎች ደኅንነት ላይ አደጋ የሚጥል ግጭት የሚቀሰቅሱ ሰዎችን በሆደ ሰፊነት የማግባባት ሥራ በመሥራት እና ሌሎችንም ወደ ሰላማዊ ሕዝባዊ ተሳትፎ የሚገቡበትን መንገድ አሟጦ በመጠቀም ዘላቂ ሰላም የማምጣት ኃላፊነት እንዳለበት እናምናለን። ሆኖም ግን ይህንን ለማድረግ ሲባል የዜጎች ሕይወት በየጊዜው እየተቀጠፈ፣ ሰዎች ከቀዬአቸው እየተፈናቀሉ፣ ነጋዴዎች ንብረታቸው እየተዘረፈ መቀጠል የለበትም። የዜጎችን ደኅንነት መጠበቅ እና ታጣቂዎችን ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ውድድር ሜዳ የመመለስ ሥራ ጎን ለጎን መሠራት ይኖርባቸዋል በማለት እናሳስባለን። አለበለዚያ ወደ ምናልመው የዴሞክራሲ ሥርዓት መሸጋገር አንችልም የሚል ሥጋት አለን፤ ሰላም ለዴሞክራሲ፣ እንዲሁም ዴሞክራሲ ለዘላቂ ሰላም ቅድመ ሁኔታዎች ናቸውና።

ቅጽ 1 ቁጥር 9 ጥር 4 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here