ህንዳውያኑን ለማስለቀቅ የተጠየቀው ክፍያ በ7 ሚሊዮን ብር ዝቅ አለ

0
385

በወሊሶ፣ ነቀምትና ቡሬ የመንገድ ግንባታ ቦታዎች እገታ ከተፈጸመባቸው አንድ ወር ከግማሽ የሆናቸውን ህንዳውያን ሠራተኞች ለማስለቀቅ በተደረገ ድርድር ከአጋቾች ወገን እንደ ቅድመ ሁኔታ ተቀምጦ የነበረዉ የስምንት ወር ደሞዝ ክፍያ ጥያቄ ወደ አራት ወር ዝቅ ማለቱን ምንጮች አስታወቁ።
ከስምንት ወር ደሞዝ ጋር በተገናኘ አይ. ኤል ኤፍ ኤስ 12 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር መክፈል የነበረበት ሲሆን አሁን በተደረሰዉ ስምምነት ግን ወደ አራት ወር ዝቅ ብሎ 5 ሚሊዮን ብር እንዲከፍል ከአጋቾች ወገን የተሰማ ሲሆን ኩባንያውም የተባለዉን ገንዘብ ለመክፈል ተስማምቷል።
ይሁን እንጂ፤ ኪሳራ ላይ የሚገኘው አይ. ኤል ኤፍ ኤስ ፤ ገንዘቡን ለመክፈል ለህንድ ኤግዚም ባንክ ጥያቄ ቢያቀርብም በባንኩ አሰራር መሰረት ኩባንያው በቂ ተቀማጭ ስለሌለው የጠየው የብድር ጥያቄ ወድቅ ሆኗል። በተጨማሪም፤ ኩባንያው በኢትዮጵያ ለሚገኙት ህንዳውያን ሠራተኞቹ ደሞዝ የሚውል ግማሽ ሚሊየን ብር ከባንኩ እንዲለቀቅለት ቢጠይቅም፤ ተቀባይነት ሊያገኝ አለመቻሉን ምንጮች ገልጸዋል።
ባለፈዉ ኅዳር ወር አጋማሽ ላይ ለወራት ደሞዝ አልተከፈለንም በሚል የህንድ ዜግነት ባላቸዉ ሰባት ሠራተኞች ላይ በኢትዮጵያዉያን ሠራተኞች እገታ የተፈጸመ ሲሆን ከታጋቾቹ ዉስጥ ኹለቱን ያለባቸዉን የጤና ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ ወዲያዉ እንዲለቀቁ ተደርጓል። ባጋጠመዉ የገንዘብ ችግር ምክንያት ለሠራተኞቹ የወር ደሞዝ መክፈል ያልቻለዉ ኩባንያዉ አሁን ላይ የተደረገለትን ቅነሳ ተጠቅሞ ያለበትን ዕዳ በመክፈል ህንዳውያን ሠራተኞቹን እንደሚያስለቅቅ ታዉቋል።
ባለፈው መስከረም በህንድ የአክሲዮን ገበያን መዉደቅ ተከትሎ ትልቅ ኪሳራ ዉስጥ የገባዉ ኩባንያዉ ዐሥራ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ገደማ እንደ ከሰረ ያሳወቀ ሲሆን በዚህም የተነሳ ውዝፍ ክፍያዎችን መክፈል እንዳልቻለ ተናግሯል። ይህንም ተከትሎ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚገኙት የህንድ ዜግነት ያላቸዉ ሠራተኞቹ እንደታገቱበት አሳዉቋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በታገቱት ህንዳውያን ጉዳይ ዙሪያ የህንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ አቻው ጋር እየተወያየ ሲሆን አዲስ አበባ የሚገኘዉ የህንድ ኢምባሲም ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለዉ እንደሆነ ምንጮች ተናግረዋል። በጤና መታወክ ምክንያት የተለቀቁት ኹለቱ ህንዳውያን እንደተናገሩት ከሆነ ደሞዝ ከተከፈላቸዉ አምስት ወራት እንደሆናቸዉ እና የደሞዝ ጉዳይ የኢትዮጵያውያን ሠራተኞች ብቻ ጥያቄ እንዳልሆነ አሳዉቀዉ ብዙ ጊዜ ስለጉዳዩ ለበላይ አመራሮች እንዳሳወቁ ተናግረዋል። አያይዘዉም ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች ይህን ዓይነት ተግባር የፈፀሙት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወደ ግንባታ አካባቢዉ የኩባንያዉ የሥራ ኃላፊዎች መምጣት በማቆማቸዉ እና ሠራተኞቹ ጉዳያቸውን በተገቢው ሁኔታ የሚያቀርቡበት ዕድል ባለመኖሩ ህንዳውያኑን ብናግታቸው መፍትሔ እናገኛለን በሚል እሳቤ ነዉ ይላሉ። የክልሎች የፖሊስ ኃይልም ከአጋቾች ጎን መቆሙንም ጨምረዉ ገልፀዋል።
በእገታ ላይ የሚገኙት ህንዳውያን በተለያዩ ማኅበራዊ መገናኛዎች ላይ ከፍቃዳቸዉ ዉጪ በሆነ ሁኔታ ተይዘው መታገታቸውን ገልጸዉ የህንድ መንግሥት ለኢትዮያውያን የኩባንያው ሠራተኞች ደሞዛቸዉን እንዲከፍልና እነሱንም ነፃ እንዲያወጣቸዉ ተማጽነዋል። ያሉበትንም ሁኔታ ሲገልጹ ካሉበት የሰራተኞች መኖሪያ ግቢ መዉጣት እንደማይችሉ እና ምግብም መግዛት እንደማይፈቀድ ገልጸዉ አሁን ላይ የተቀቀለ ሩዝ፣ ስኳር ድንች እና አትክልቶች ብቻ ለምግብነት እየተጠቀሙ ሲሆን ምን ያህል እንደሚያቆያቸውም ማወቅ እንዳልቻሉ ገልፀዋል። እነዚህ ለምግብነት የሚዉሉት ግብዓቶች በጊቢዉ ዉስጥ የበቀሉ ናቸዉ። በጊቢዉ ዉስጥ ለመጠጥነት የሚጠቀሙበት ውሃም እያለቀ እንደሆነ አሳውቀዋል። በመኖሪያ ጊቢዉ በቁም እስር ላይ የሚገኙት ኒራጅ ራጉዋንሽ በተደጋጋሚ በትዊተር ገፃቸዉ ላይ እንዳስነበቡት ሁኔታዎች ከቁጥጥር ዉጭ እየሆኑ እንደመጡ እና መጥፎ ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት የህንድ ከፍተኛ ባለስልጣናት መፍትሔ እንዲያመጡ አሳስበዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የታገቱት ህንዳውያን እንዲለቀቁ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ትዕዛዝ በደብዳቤ ለሚመለከተዉ አካል የተላለፈ ሲሆን ይህም ሊሆን የቻለዉ ከውጭ በተፈጠረ ጫና ነዉ ሲሉ ምንጮች ይገልፃሉ። ምንጮች ጨምረዉ እንደገለፁት የጠቅላይ ሚኒስትሩን የማዘዣ ደብዳቤ ተከትሎ ፖሊስ የሚወስደዉን እርምጃ በመፍራት አጋቾቹ የሚቀርብላቸዉን የመደራደሪያ ገንዘብ ያለማንገራገር ይቀበላሉ ይላሉ።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ለኣዲስ ማለዳ እንደገለጸው የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ቀጥተኛ ግንኙነት ያለዉ ከተቋራጭ ኩባንያዉ ጋር ሲሆን መስሪያ ቤቱም የሚጠበቅበትን ክፍያ በጊዜዉ እና በአግባቡ ለኩባንያዉ እንደከፈለ ተናግሮ ከሰራተኞች ክፍያ ጋር በተየያዘ ቀጥተኛ ግንኙነት እንደሌለዉ አክሏል።
ተቀማጭነቱ በህንድ ሃገር የሆነዉ እና በህንድ መንግሥት ባለቤትነት ስር የሚተዳደረዉ የመንገድ ሥራ ተቋራጭ ኩባንያ ስፔን ሃገር ከሚገኙት ኤለሳሜከስ እና ኤኮአስፋልት ጋር በጥምረት በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ሦስት የመንገድ ግንባታ ሥራዎች እንዳሉት የታወቀ ሲሆን በተፈጠረዉ ጉዳይም ታጋቾች አዲስ አበባ ለሚገኘዉ የስፔን ኢምባሲ ደብዳቤ በመፃፍ ጉዳዩን አሳዉቀዋል። በኹለቱ ሃገራት ኩባንያዎች ጥምረት የሚካሄደዉ የመንገድ ግንባታ ከስድስት መቶ በላይ ሰራተኞችን በስሩ እንደሚያስተዳድር ለማወቅ ተችሏል።

ቅጽ 1 ቁጥር 9 ጥር 4 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here