ትግራይ በነዋሪዎቿ አንደበት

0
1047

ማርታ ኪሮስ(ለዚህ ጽሁፍ ሲባል ስሟ የተቀየረ) በማለዳ ቡናዋን አፍልታ ከልጆቿ ጋር ቁርሷን አጣጥማ አምላኳ ቀኑን እንዲባርክላት “ቀኝ አውለኝ” ብላ ተማጽና አስቤዝዋን ልትሽምት ወደ ገበያ እያቀናች ነው።

ከቤቷ ወጥታ ብዙም ሳትጓዝ ከእርሷ ማልደው ወደ ገበያ ያቀኑ ጎረቤቶቿ እርሷ ወደ እያቀናችበት ካለው መንገድ በተቃራኒ እየተመለሱ ያሉ ጎረቤቶቿን መንገድ ላይ አገኘቻቸው። ወደ ቤታቸው በመመለስ ላይ ያሉትን ጎረቤቶቿን “ምነው በሰላም ነው የተመለሳችሁት ” ስትል ትጠይቃለች። ወደ ቤታቸው የሚመለሱት ጎረቤቶቿ “ገበያ የለም ተብሏል” የሚል ምላሽ ሰጧት። እናም ጎረቤቿን ከገበያ የተመለሱበትን ሚስጥር ከሰማች በኋላ ፊቷን ወደ መጣችበት መንገድ መልሳ ወደ ቤቷ አቀናች።
ብዙም ሳትጓዝ የተኩስ ድምጽ ሰማች። ቤት ትታቸው የመጣቻቸው ኹለት ልጆች ትዝ አሏት። በሰማችው የተኩስ ድምጽ ተደናግጣ ልጆቿን እያሰበች ወደ ቤቷ መገስገሷን ቀጠለች።

“ቤቴ አንደደረስኩ አንድ ልጄን አዝዬ ሌላኛዋን ልጄን ለሌላ ሰው አሳዝዬ አፍታም ሳንቆይ ወደ ገጠር ቤቱን ለቀን ወጣን” በማለት ከቤቷ የወጣችበትን ቅጽበት ታስታውሳለች የኹለት ልጆች እናት የሆነችው ማርታ።

ማርታ ከመቀሌ በ82 ኪሎ ሜትር እርቀት ላይ የምትገኘውን የምትኖርባትን ፍረወይኒ ከተማ ለቃ በወጣችበት እለት ገጠር ገብታ አደረች። ማርታና ኹለት ልጆቿ ያረፉበት የገጠር መንደር አንደ ማርታ ሁሉ በድንጋጤና በፍረሀት በተሞሉ የከተማ ሰዎች ተጨናንቋል።

ማርታ ያረፈችበት መንደር ከከተማ ሸሽተው በሚመጡ ሰዎች ሞላ። መንደሩን ከሞሉት ሰዎች መካከል እናቶች፣ ህፃናትና ነፍሰ ጡር እናቶች እንደነበሩ ማርታ ታስታውሳለች። በመንደሩ ኗሪዎች በድንገት ከከተማ የመጡባቸውን እንግዶች ድንጋጤ በተሞላበት ስሜት ቤት ያፈራውን እያበሉ እና እያጠጡ ለአንድ ሳምንት ቆዩ።
ከአንድ ሳምንት በኃላ የመንደሩ ኗሪዎች ለከተሜዎቹ የሚያቀርቡላቸው ምግብ አለቀ። የሚቀመስ ነገር በሌለበት ሁኔታ መቆየት ከባድ እንደሆነ የተረዳችው ማርታ፣ ልጆቿን በተጠለለችበት መንደር ትታ ወደ ፍረወይኒ ከተማ ምግብ ለማምጣት አቀናች።

ማርታ ካረፈችበት የገጠር መንደር ፍረወይኒ ከተማ ከሚገኘው ቤቷ የሚቀመስ ነገር ይዛ ለመመለስ በጉዞ ላይ እያለች ያላሰበችው ነገር አንደገጠማት ለአዲስ ማለዳ አስረድታለች።

“ወደ ፍረወይኒ ከተማ እያቀናሁ ባለሁበት መንገድ ላይ የኤርትራ ወታደራዊ ልብስ የለበሱ መሳሪያ የታጠቁ ወታደሮች አገኙኝ፣ ወዴት እንደሚሄደም ጠየቁኝ በትግሪኛ ቋንቋ ጠየቁኝ። ከለበሱት ወታደራዊ ዩኒፎርም ሌላ የኤርትራ ሰዎች መሆናቸውን በትግሪኛ ቅላጼያቸው ተረዳሁኝ፣ ትላለች ማርታ በስልክ በነበረን ቆያታ።
ከምኖርበት መንደር ምግብ አልቆብኝ ለልጆቼ ምግብ ከከተማ ምግብ ይዤ ልመለስ አንደሆነ ብነግራቸውም ፣ ወታደሮቹ ግን ሊያምኑኝ አልቻሉም። አስከትለው ልጆችሽ የት አሉ? አስከትሎም ሌላኛው ወታደር ልጆችሽን አምጫቸው አለኝ በቀጭን ትእዛዝ መልክ።

አማራጭ ስላልነበረኝ ከገጠሩ መንደር ተመልሼ ልጆቼን አዝዬ ወደ ወታደሮቹ ተመለስኩ። ልጆቼን ይዤ ሲያዩኝ አራሩልኝ እና አሳለፉኝ።” ስትል ማርታ የገጠማትን ገጠመኝ ለአዲስ ማለዳ ተርካለች።

ማርታ ከወታደሮች የይለፍ ፈቃድ እንድታገኝ ምክንያት የሆኗትን ኹለት ልጆቿን ይዛ ፍረወይኒ ከተማ ከተማ ገባች። ፍረወይኒ አንደገባች በቀጥታ ወደ መኖሪያ ቤቷ ብታቀናም ከቤቷ ደጃፍ ስትደርስ ግን የቤቷ በር አንደዘጋችው አልጠበቃትም። ይልቁንም በሩ ተሰባብሮ እና ክፍት ሆኖ ነበር ያገኘችው።

የቤቷ በር መከፈቱንና መሰበሩን የተመለከተችው ማርታ ወደ ውስጥ ዘልቃ ስትገባ ፣የቤቷ በር አንደመሰበሩ በቤት ውስጥ ከነበሩት አንዳንድ እቃዎች መሰበርና ከቤቷ መመሰቃቀል ውጭ የተለየ ነገር በቤቷ ውስጥ አልተመለከተችም። ማርታ የምግብ ፍጆታዎችን ይዛ ወደ መጣችበት አነስተኛ መንደር ተመለሰች።

ማርታ እና ልጆቿ ባረፉበት የገጠር መንደር ዳግመኛ ለአንድ ሳምንት አንዲቆዩ ግድ ሆነባቸው። ሁኔታው አስቸጋሪ ቢሆንም ማርታና ልጆቿ በገጠር መንደር መኖሩ አማራጭ ያልነበረው ጉዳይ ነበር።

ሁኔታዎች በመጠኑም ቢሆን እየተሻሻሉ ሲመጡ ማርታ ምግብ ይዛ ወደ ገጠር መንደር በተመለሰች በአንድ ሳምንት ወደ ፍረወይኒ ከተማ ተመለሰች። ማርታ ወደ ቀድሞ መኖሪያዋ ፍረወይኒ ከተማ በተመለሰችበት ጊዜ ሌሎችም የከተማዋ ኗሪዎች ተመለስው እንደነበር ትናገራለች። በአካባቢውም የምግብ እርዳታ እየተሰጠ ነበር ትላላች። እርዳታ በሚሰጥበት ጊዜ ስዓት እየጠበቀ አልፎ አልፎ የተኩስ ድምጽ ይሰማ ነበር የምትለው ማርታ ፍረወይኒ ከተማ ብዙም አልቆየችም።

ከፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ተደጋጋሚ ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እየደረሱ ስለመሆኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ሪፖርት ሲደርሳቸው መቆየቱን መግለጻቸው ይታወሳል።

በተባበሩት መንግሥታት በግጭቶች ውስጥ ጾታዊ ጥቃቶችን የሚከታተሉት ፕርሚላ ፓተን፣ ጥር 14 2013 የቤተሰብ አባላታቸውን ተገደው እንዲደፍሩ የተደረጉ ግለሰቦች ስለመኖራቸው የሚረብሹ ሪፖርቶች ደርሰውናል ብለው ነበር።

ፕራሚላ መሠረታዊ ቁሶችን ለማግኘት ሲባል ከወታደሮች ጋር ወሲብ ለመፈጸም የሚገደዱ ሴቶች ስለመኖራቸው፣ ድንገተኛ የእርግዝን መከላከያ መድሃኒቶችን የሚፈልጉ ሴቶች ቁጥር ስለመጨመሩ እንዲሁም በመጠለያ ጣቢያዎችም በሴቶች እና ሕጻናት ላይ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶችን የሚያትቱ ሪፖርቶች ጨምረዋል ማለታቸው ይታወሳል።

በትግራይ ክልል የተከሰተውን ቀውስ ተከትሎ ተፈጽመዋል የተባሉ ጾታዊ ጥቃቶችን የሚመረምር ከጤና ሚንስቴር፣ ከሴቶች፣ ህጻናት እና ወጣቶች ሚንስቴር፣ ከአገር መከላከያ እና ከጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተወጣጡ አባላትን ያካተተግብረ ኃይል መቀሌ መድረሱን የሴቶች፣ ህጻናት እና ወጣቶች ሚንስቴር ሕዝብ ግነኙነት ኃላፊ አድነው አበራ ተናግረዋል።

ማርታ ፍረወይኒ ከተማን ለቃ የወጣችው በቤተሰብ አማካኝነት አንደሆነ ለአዲስ ማለዳ አስረድታለች። ሁኔታው ማርታ አዲስ አበባ የሚኖሩ ዘመዶች ስለነበሯት በዘመዶቿ አማካኝነት ወደ አዲስ አበባ አንድትመጣ ጥያቄ አቅርበውላት ነበር።

ዘመዶቿ ወደ አዲስ አበባ አንዲትመጣ ያመቻቹላት ማርታ ከመቀሌ አየር ማረፊያ ወደ አዲስ አበባ በአውሮፕላን በመጓዝ አሁን ላይ አዲስ አበባ ከዘመዶቿ ጋር አንደምትገኝ ማርታ ተናግራለች። ማርታ በትግራይ የነበረውን ሁኔታ ወደ ኋላ በመመለስ ለአዲስ ማለዳ የተረከችው እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ ከደረሰች በኃላ።
በሕግ የማስከበር ዘመቻው በሕውሓት በኩል ግልጽ ጦርነት የተባለው ጉዳይ በትግራይ ሕዝብ ላይ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን አንዳስከተለ ከአገር እስከ ዓለም አቀፍ ደረጃ እየተነገረ ነው። ጦርነቱ በትግራይ ክልል በሚገኙ ነዋሪዎች ላይ ካስከተለው ዋነኛ ችግር ሰብዓዊ ቀውስ መሆኑን ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች ሳይቀር መረጃ እያወጡ ነው። በኤርትራ ወታደሮች በኩል የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰትም አሳሳቢ እንደሆነ በስፋት እየተነገረ ይገኛል።

በክልሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች ድጋፋቸውን ለማድረስ መቸገራቸውን በመግለጽ ኢትዮጵያ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት ምቹ ሁኔታዎችን አንዲፈጥር ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፎችን እያደረስኩ ነው ብሏል።አዲስ ማለዳ በጉዳዪ ላይ በትግራይ ክልል የሚኖሩ ኗሪዎችን አነጋግራ ያገኘችው መረጃ አንደሚያመለክተው ከሆነ በትግራይ ክልል አልፎ አልፎ ሰብዓዊ ድጋፍ እየቀረበ ቢሆንም ችግሩ ባለባቸው አካባቢዎች ሙሉ ደርሷል ለማለት የጸጥታ ችግር ማዳረሱን አዳጋች እንዳደረገባቸው ምትኩ ካሳ መናገራቸው ይታወሳል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መሪ የሆኑት ሙሉ ነጋ(ዶ/ር) በጉዳዩ ላይ አዲስ ማለዳ ማብራሪያ አንድትሰጣቸው ብትጠየቅም ምንም አይነት ምላሽ አልሰጥም በማለት በአጭር መልስ ደምድመዋል።

አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው ኗሪዎች ውስጥ ኗዋሪነቷን በውቅሮ ከተማ ያደረገች ሄለን ገብረ መድህን የተባለች የ29 ዓመት ወጣት በውቅሮ ከተማ ለአንድ ቤተሰብ 30 ኪሎ ግራም ስንዴ እየተሰጠ መሆኑን ተናግራለች። ነግር ግን ከከተማ ወጣ ባሉ ገጠራማ ቦታዎች አንዲሁም ከዋና መስመር ገባ ብለው የሚገኙ ከተሞች ላይ እርዳታው እየደረሳቸው አለመሆኑን ጠቁማለች።

ሰብዓዊ ድጋፉን በሁሉም አካባቢዎች ማድረስ ያልተቻለው በክልል በአንዳንድ ቦታዎች ላይ አሁንም ድረስ ግጭቶች ስላሉ በጸጥታ ችግር ሊሆን አንደሚችል ተናግራለች።

አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው የትግራይ ኗሪዎች ውስጥ የአድዋ ከተማ ነዋሪ አንዲት ወጣት ትገኝበታለች። ይቺ ስሟ እንዳይጠቀስ ፈቃደኛ ያልሆነችው ወጣት ፣የ2012 የአዲግራት ዩኒቨሪሲቲ የጋዜጠኝነት እና ተሥነ ተግባቦት ተመራቂ ተማሪ ፣በአድዋ አካባቢ የነበረው የተኩስ ልውውጥ በእጅጉ አንዳስደነገጣትና በእድሜዋ አይታው የማታውቀው አስደንጋጭ ነገር እንደሆባት ታስታውሳለች።

የጦርነቱ ኢላማ በሕውሓት አመራሮች ላይ ያነፃጸረ ነው ቢባልም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የትግራይን ኗሪዎች ችግር ውስጥ የከተተ ነው ትላለች የአድዋ ከተማ ነዋሪዋ ወጣት።

በትግራይ ክልል ያለው የሰብዓዊ መብት አያያዝና የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነት በዓለም አቀፍ ተቋማት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት መግለጫ እየተሰጠበት ይገኛል።
የተባበሩት መንግታት የዓለም ምግብ መርሃ ግብር እና አንዳንድ ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች ትግራይ ውስጥ የረሃብ አደጋ ተደቅኗል እያሉ ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ትግራይ ውስጥ ምንም አይነት የሰብዓዊ ድጋፍ እጥረት የለም ብሏል።ይልቁንም ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ትግራይ ክልል ያለውን ነባራዊ እውነታ በተመለከተ ይዘውት የሚወጡት መረጃ ትክክል አንዳልሆነም መንግሥት ማስተባበሉ የሚታወስ ነው።

በቅርቡ ወደ ትግራይ ያቀኑት የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊለፖ ግራንዲ በክልል ያለው ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን መግለጻቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የኖርዌጂያን ሪፊውጂ ካውንስል (ኤንአርሲ) በትግራይ ድጋፍ የሚስፈልጋቸው ዜጎች በበቂ ሁኔታ እርዳታ እያገኙ እንዳልሆነ ለቢቢሲ ገልጿል። ካውንስሉ አንዳለው ባለፉት ሦስት ወራት ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች ዘላቂነት ያለው ድጋፍ ማድረግ አልቻሉም ይላል።

በትግራይ ክልል ኹለት ሚሊዮን ገደማ ዜጎች አፋጣኝ ድጋፍ አንደሚስፈልግ ይሄው ካውንስል ጠቁሟል። የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ለአንድ ነጠብ ሰምንት ሚሊዮን ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ አቅረቤያለሁ ብሏል። መንግሥት የትግራይ ሰብዓዊ ድጋፍ ነባራዊ ሁኔታ ላይ የሚለውና ዓለም ዓቀፍ ተቋማት የሚወጡት መረጃም የተለያየ ሆኖ ተገኝቷል።

ድርጅቶቹ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል እየደረሱ ነው የተባሉት ድጋፎች እንዳልደረሱ የገለጹ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ማዳረስ የቻለው የሰብዓዊ ድጋፍ ከመቀሌ እና ለዋና መሥመር ቅርብ ከሆኑ አካባቢዎች ውጭ እንዳልደረሰ ነው በዓለም አቀፍ ድርጅቶች በኩል የተገለጸው። አዲስ ማለዳ ከላይ ያነጋገረቻቸው የትግራይ ኗሪዎችም ይህንኑ አረጋግጠዋል። እየተሰጠ ያለው እርዳታ ቢኖርም ለሁሉም ተደራሽ እንዳልሆነ ኗሪዎቹ አረጋግጠዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 118 ጥር 29 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here