የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ባለ 32 ወለል ዋና መሥሪያ ቤት ህንፃ ሊገነባ ነው

0
922

የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር በአዲስ አበባ ከተማ የማኅበሩ ዋና ምሥሪያ ቤት ሆኖ የሚያገለግል ባለ 32 ወለል ህንፃ ሊገነባ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ማኅበሩ የዋና መሥሪያ ቤቱን ህንፃ የሚገነባው በአዲስ አበባ ሲሆን ማኅበሩ እየተጠቀመበት የሚገኘውን አንድ ሺሕ 963 ካሬ ቦታ ዋና መስሪያ ቤት በሌላ ተለዋጭ ቦታ ለማስፋፋት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ማኅበሩ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል፡፡ የማኅበሩ ዋና መሥሪያ ቤት የሚገነባበትን የቦታ ማስፋፋፊያ ሥራ ማኅበሩ ከፌደራል ከተማ ልማት እና ቤቶች ሚኒስቴር ጋር ውል ገብቶ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንት ዮሐንስ በንቲ(ዶ/ር) ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡

በዚህም የማኅበሩ ዋና መሥሪያ ቤት አሁን በሚገኝበት ብሔራዊ አካባቢ ተለዋጭ አራት ሺሕ 330 ካሬ መሬት ማገኘቱን የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ጠቁመዋል፡፡ ተለዋጭ ቦታውን ማኀበሩ አንዲያገኝ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ አንደወሰነም ፕሬዚዳንቱ አክለዋል፡፡

ማኅበሩ ሚያስገነባውን ባለ 32 ወለል ዋና መሥሪያ ቤት ህንፃ ዲዛይን በባለሙያዎች ጥናት በታገዘ አሰራር ተሰርቶ ማጠናቀቁ ተመላክቷል፡፡ የዋና መሥሪያ ቤት ዲዛይን የምርምር ማዕከል፣ የማሰልጠኛ ማዕከል፣ የስብሰባ አዳራሽ፣ ቤተ መጽሐፍት፣ የአይሲቲና የቢሮ አገልግሎትን ያካተተ ነው ተብሏል፡፡

ማኅበሩ በ2005 አካሂዶት በነበረው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ አገር አቀፍ የማኅበሩን ቢሮ ግንባታ እና የማደራጀት ሥራ መወሰኑን ያስታወሱት ዮሐንስ(ዶ/ር) የማኅበሩን ህንፃ በአገር አቀፍ ደረጃ ማደራጀት ከተጀመረ ቆይቷል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር በኢትዮጵያ ትልቁ ማኅበር መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ ማኅበሩ ከዋናው መሥሪያ ቤት ህንፃ ግንባት በተጨማሪ በክልሎችና በዞኖች የማኅበሩን ህንፃ ግንባታ እያከናወነ ነው ብለዋል፡፡

ማኅበሩ በክልሎችና በዞኖች የሚገነባው የቢሮ ግንባታ አዲስ አበባ ከተማ ላይ ከሚገነባው ዋና መሥሪያ ቤት ትልቅ ትኩረት በመስጠት ከማኅበሩን የቢሮ አደረጃጀት 60 በመቶ በክልሎችና በዞኖች አንዲገነባ መወሰኑ ተመላክቷል፡፡ ይህም ማለት ማኅበሩ የሚገነባው ዋና መሥሪያ ቤት የማኅበሩን የቢሮ ግንባታ 40 በመቶ ድርሻ አንዳለው ዮሐንስ ገልጸዋል፡፡

የሚገነባው ዋና መሥሪያ ቤት ማኅበሩን በገንዘብ ማገዝ ያስችላል ተብሏል፡፡ ማኅበሩ ከዋናው መሥሪያ ቤት ህንፃ ግንባታ በተጨማሪ በክልሎች ቢሮዎችን እየገነባ መሆኑ ተመላክቷል፡፡ በዚሁ መሰረት በደቡብ ክልል ባለ ሥድስት ወለል ህንፃ በግንባታ ላይ ሲሆን በኦሮሚያ ክልልና በአዲስ አበባ የመሥሪያ ቦታ መዘጋጀቱን ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል፡፡

የማኅበሩን ህንፃ ግንባታ በጀት ከማኅበሩ አባላት መምሕራን የሚሰበሰብ መሆኑን የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡ የማኅበሩ ጠቅላላ ጉባኤ አባላት መምሕራን የአንድ ወር ደምወዛቸውን ለማኀበሩ ገቢ አንዳደርጉ መወሰኑም ታውቋል፡፡ በዚሁ መሰረት በማኅበሩ አመራሮችና በክልሎች የገንዘብ ስብሰባ ሥራው መጀመሩን ዮሐንስ ጠቁመዋል፡፡ እንዲሁም የማኅበሩን ህንፃ ለማስገንባት የሚስፈለገውን ገንዘብ ከመንግሥትና ከግል ድርጅቶች ድጋፍ ለማግኘት ማኅበሩ እየሰራሁ ነው ብሏል፡፡

የዋና መሥሪያ ቤቱ ህንፃ በጀት እስካሁን በውል አንዳልታወቀ ዮሐንስ ተናግረዋል፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት የበጀት ጥናት ሥራው በባለሙያ እየተጠና እና በሂደት ላይ ያለ ስለሆነ ነው ተብሏል፡፡ ዮሐንስ አንዳሉት ከሆነ የበጀት መጠኑ በጥናት ላይ በመሆኑ ባይገለጽም ቀላል ገንዘብ አንደማይፈጅ ነው፡፡
የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ማኅበር ከተመሰረተ ከ70 ዓመት በላይ አስቆጥሯል፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 118 ጥር 29 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here