የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማህበር የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ያወጣው ህግ በ24 ሰአት ውስጥ ማውጣት የሚቻለው የከፍተኛ የገንዘብ መጠን ጣሪያው 75 ሺህ ብር መሆኑ እንዲሁም በሳምንት አምስት ትራንዛክሽን ብቻ ነው መፈፀም የሚቻለው የሚለው መመሪያ ስራቸውን እንዳስተጓጎለባቸው ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ።
ለአዲስ ማለዳ ጉዳዩን ያስረዱት የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጮች ማህበር ፕሬዚዳንት ግርማ ሀብተማርያም ከገንዘብ ኖት ቅያሪው ጋር በተያያዘ የብሄራዊ ባንክ ያወጣው መመሪያ ለኮንስትራክሽን ስራዎች አስቸጋሪ እንደሆነ ተናግረዋል።
ይህ የብሄራዊ ባንክ መመሪያ ለኮንስትራክሽን ዘርፉ እንቅፋት ሆኖበታል ምክንያቱም ለአንድ በቢሊየን የሚቆጠሩ ብሮች ለሚሰራ ፕሮጀክት በቀን 75 ሺሕ ብር ብቻ ማውጣት ምንም አይጠቅመውም በአሁኑ ጊዜ በ75 ሺሕ ብር ምን አይነት እቃ መግዛት ይቻላል ሲሉም ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
ይህ መመሪያ ከፍተኛ ትራንዛክሽን ለሚፈፅሙ ፕሮጀክቶች ቀርቶ አነስተኛ ናቸው የሚባሉትን በሰብኮንትራት እና በዳይሬክቲቭ ሌበር ክፍያ ባላቸው አነስተኛ ግዢ ለሚያከናውኑ ፕሮጀክቶች እንኳን ብሩ ዝቅተኛ በመሆኑ ሊያሰራቸው እንደማይችል ተናግረዋ።
የኮንስትራክሽን ዘርፉ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ እንደነዚህ አይነት መመሪያዎች ሲሰጡ ዘርፎች ተለይተው ነው መሆን ያለበት ብለዋል።
በዚህ መመሪያ ምክንያት የኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ ከፍተኛ የሆነ ጫና አለው በተለይም የተያዙ ፕሮጀክቶች መጓተቶች በተያዘለት ጊዜ አለመጠናቀቅ ዋነኛው ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በዋናነት እንደ ማህበር ይህንን ችግር እንዲፈታልን በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን በኩል ጥያቄያችን ለብሄራዊ ባንክ እንዲቀርብልን ተናግረን ምላሽ በመጠባበቅ ላይ ነን ብለዋል።
እንዲሁም አንዳንድ ባንኮች ላይ መስጠት ከነበረባችሁ ገደብ አልፋችኋል እና አቁሙ ተብለው አንዳንድ የግል ባንኮች ያቆሙ አሉ ንብረታቸውን አስይዘው ለመጫረት ሁሉን ነገር ጨርሰው ጉልበታቸውን፣ ንብረታቸውን እንዲሁም ጊዜያቸውን ሰውተው ቢልቦንድ ለማሰራት ሲሄዱ ታግቷል የሚል ነገር መጣ ይህም ትክክል አይደለም ብለዋል።
በዚህም በአሁኑ ወቅት በባንኮች በኩል እየተተገበሩ ባሉ የአሰራር ስርአቶች ምክንያት በግንባታ ተቋማት ላይ ፣ ስራዎች በአፋጣኝ እንዳይሰሩ እያደረገ ይገኛል ቁጥራቸው በርከት ያሉ ባንኮች የቅድሚያ ክፍያ ዋስትና ቦንድ እንዳይሰጡ በመከልከላቸው ምክንያት በስራ ተቋራጮች ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ ስለመሆኑም አክለው ተናግረዋል።
በትንንሽ ከተሞች የሚገኙ ባንኮች ቅርንጫፎቻቸው እጅግ የተራራቁ በመሆኑ ፣ በስፍራው በመከናወን ላይ የሚገኙ ግንባታዎች ለሚሰሩ ሰራተኞች ደሞዝ ለመክፈል እና የግንባታ ግብአቶችን ለመግዛት እንቅፋት እንደሆነባቸው አንስተዋል።
እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በሲሚኒቶና በአርማታ ብረት ላይ ያለው የዋጋ ጭማሪ ከፍተኛና ከአቅም በላይ በመሆኑ ፣ አብዛኞቹ ፕሮጀክቶች እንዲቆሙ እያስገደደ ይገኛልም ብለዋል።
የሚመለተው አካል የኮንስትራክሽን ስራው ላይ የሚፈጠረው ችግር በአገር ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደሚያደርስ በመረዳት ለጉዳዩ በአፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጠን እነጠይቃለን ብለዋል።
የገንዘብ ቅየራውን ተከትሎ የብሄራዊ ባንክ ከፍተኛ ካምፓኒዎች 75 ሺሕ የግል ድርጅቶች ደግሞ 50 ሺሕ ብር ብቻ በቀን ማውጣት የሚችሉት እንደሆነ እንዲሁም ትራንዛክሽን መፈፀም የሚቻለው በሳምንት አምስት ጊዜ ብቻ እንደሚፈፀም መወሰኑ ይታወሳል።
አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ያነጋገረቻቸው የብሄራዊ ባንክ የባንኮች ሱፐር ቪዥን ዳይሬክተር ፍሬዘር አያሌው እንደተናገሩት የትራንዛክሽን ገደቡን በተመለከተ ለባንኮች ደብዳቤ መላኩን አስታውቀዋል ።
እንደ ፍሬዘር ገለፃ ለባንኮች በራሳቸው መወሰን እንደሚችሉ የሚገልፅ ደብዳቤ ከብሄራዊ ባንክ መላኩን አክለው ገልፀዋል። በዚህ መሰረት ደንበኞቻቸውን እያዩ ፍቃድ ያለው ተቋም ፣ ጥሩ የስራ ግንኙነት ያላቸው እንደሆነ እና ታማኝ መሆናቸውን ካረጋገጡ በዛ መሰረት ከገደብ ውጪ መንቀሳቀስ ይችላሉ ብለዋል።
በዚህም ባንኮች የደንበኞቻቸውን ሁኔታ እርግጠኛ ከሆኑ በልዩ ሁኔታ ከገደብ ውጪ ማስተናገድ እንደሚችሉ ከብሄራዊ ባንክ በያዝነው ሳምነት ደብዳቤ መላካቸውን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 118 ጥር 29 2013



