በምሥራቅ ወለጋ ከኦነግ ሽኔ ጋር በተደረገ ተኩስ ከስምንት ያላነሱ ሰዎች ተግድለዋል

0
1150

በምሥራቅ ወለጋ ኦነግ ሸኔ በተደራጀ ኃይል ባሳለፍነው ሳምንት በንጹሐን ዜጎች ላይ ጥቃት ለማድረስ መንቀሳቀሱን ተከትሎ የአካበቢው ማኅበረሰብ እራሱን ለመጠበቅ ባደረገው ፍልሚያ ከስምንት ያላነሱ ሰዎች መሞታቸውን በስፍራው ላይ የነበሩ የአይን እማኞች ለአዲስ ማለዳ አረጋግጡ።

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ኦነግ ሽኔ ከዚህ በፊት ሲያደርሰው ከነበረው ጥቃት በላቀ ኃይል ጥቃት ለማድረስ መሞከሩን ተከትሎ ካሳለፍነው ሰኞ የካቲት 1/2013 እስከ የካቲት 4/2012 ባሉት አራት ቀናት የአካባቢው ማኅበረሰብ እራሱን በማደራጀት ከኦነግ ሸኔ ታጣቂ ኃይል ጋር የተኩስ ልውውጥ ሲያደርግ አንደነበር የአይን እማኞች ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል።

የአዲስ ማለዳ ምንጮችና ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ኗሪዎች እራሱን ለመከላከል የተደራጀው የማኅበረሰብ ክፍልና ኦነግ ሸኔ ያደረጉትን የተኩስ ልውውጥ ለአራት ቀናት ማለትም ከየካቲት አንድ እስከ የካቲት 4/2013 በማስረጃ በማስደገፍ መረጃዎችን ጠቁመዋል። አዲስ ማለዳ በምሥራቅ ወለጋ ለአራት ቀናት የነበረውን ግጭት ስትከታተል ቆይታ ያገኘችው መረጃ እንደሚመላክተው የተደራጀው የማኅበረሰብ ክፍል ጥቃቱን ለመመከት ባደረገው ጥረት የከፋ ጥቃት አንዳይፈጸም አስችሏል ተብሏል።

እራሱን ለመከላከል የተደራጀው የማኅበረሰብ ክፍል ጥቃት ለመፈጸም በተለያዩ ቦታዎች ተኩስ የከፈተውን የኦነግ ሸኔ የታጠቀ ሀይል ለመከላከል ባደረገው ጥረት በኦነግ ሽኔ ታጣቂዎች ላይ ጉዳት እንዳደረሰ ነው የተነገረው። በተለይ የካቲት 1/2013 ማኅበረሰቡ እራሱን ለመከላከል ባደረገው ጥረት በፓትሮል መኪና ተጭነው ሊሙ ወረዳ የገቡ ከ14 ያላነሱ የኦነግ ሽኔ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን በቦታው የነበሩ የአይን እማኞች አስረድተዋል።

በምሥራቅ ወለጋ በተለያዩ ቦታዎች ጥቃት እየፈተጸመ መሆኑን የሚናገሩት አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ኗሪዎች ጥቃት በሚፈጸምባቸው ቦታዎች አንዳንድ የክልሉ ልዩ ኃይል ቢኖሩም የኦነግ ሸኔን ኃይል የሚመክት አቅም እንደሌላቸው እና ማኅበረሰቡ እራሱን በራሱ ነቅቶ እንዲጠብቅ እንደነገሯቸው ጠቁመዋል። አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም በምሥራቅ ወለጋ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን አስመልክቶ በተደጋጋሚ በሰራችው ዘገባ በአካባቢው ያለው የክልሉ ልዩ ኃይል ከኦነግ ሽኔ ታጣቂ ኃይል ጋር የሚጣጣም አቅም አንደሌለው መናገራቸው የሚታወስ ነው።
በመሆኑም በአካባቢው በተደጋጋሚ ብቅ ጥልቅ እያለ ጥቃት የሚፈጽመውን የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድን ለማስወገድና የአከባቢውን ሰላም ለማረጋገጥ የመከላከያ ኃይል ገብቶ ከማኅበረሰቡ ጋር በመተባበር ችግሩ እልባት እንዲያገኝ ኗሪዎች ጠይቀዋል።

በምስራቅ ወለጋ የተለያዩ ወረዳዎች በ33 የኦነግ ሸኔ አባላት ላይ እርምጃ መወሰዱን የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን የካቲት 3/2013 አስታውቋል። ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ሰሞኑን በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎች የሕግ የበላይነትን የማስከበር ሥራ ተሰርቷል ብሏል። በዚህም 33 የቡድኑ አባላት ላይ እርምጃ መወሰዱን ፖሊስ ገልጿል። እርምጃ ከተወሰደባቸው በተጨማሪ ስምንት የኦነግ ሸኔ አባላት ከነሙሉ ትጥቃቸው መማረካቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል። የዞኑን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ በኦነግ ሸኔ ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ፖሊስ በመግለጫው አንስቷል።

በዞኑ በተደጋጋሚ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለማስቆም የክልሉ መንግሥት ለምን አቃተው የሚለውን ጥያቄ አዲስ ማለዳ ለኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ ብታቀርም ኮሚሽነሩ ምላሽ ለመስጠት ከሥዓታት ብኋላ ስልክ እንዲደወልላቸው ቢገልጹም አዲስ ማለዳ ከስዓታት ቆይታ ብኋላ ደጋግማ ብትደውልም ስልክ ሊመልሱ አልቻሉም።

ቅጽ 2 ቁጥር 119 የካቲት 6 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here