የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ ማግኘት የቻለው የሰው ኃይል 20 በመቶ ብቻ ነው

0
1428

በትግራይ ክልል በተደረገው ጦርነት ከሥራ ገበታቸው የተበተኑ ከክልሉ ጤና ባለሙዎች ውስጥ የክልሉ ጤና ቢሮ ግንኙነት መፍጠር የቻለው ከጠቅላላው የሰው ኃይሉ 20 በመቶ ከሚሆነው ጋር ብቻ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል ያለውን የጤና ተቋማትና አገግሎት ሁኔታ በተመለከተ ባወጣው ሪፖርት ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር ግንኙነት እስካደረገበት ጊዜ ድረስ ግንኙነት መፍጠር የተቻለው 20 በመቶ ከሚሆነው የጤና ባለሙያ ጋር ነው።
ኮሚሽኑ ባወጣው ሪፖርት በአጠቃላይ በትግራይ ክልል የጤና ቢሮ ሥር ወደ ሥራ የገቡ የጤና ተቋማት ከ30 በመቶ በላይ እንደማይሆኑ ከክልሉ ጤና ቢሮ አረጋግጫለሁ ብሏል።። ተጨማሪ የጤና ተቋማት በቅርቡ ወደ ሥራ እንዲገቡ ጥረት እየተደረገ እንደሆነም ኮሚሽኑ አመላክቷል።

በሰባቱ የትግራይ ዞኖች ውስጥ ያሉ ከ90 በላይ ወረዳዎች በአፋጣኝ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ግንኙነት ፈጥረው ወደ ሥራ የማይገቡ ከሆነ የጤና ኬላዎችን ወይም የጤና ጣቢያዎችን ወደ ሥራ ማስገባት ስለማይቻል የጤና አገልግሎት ችግሩን የሚያባብስ እንደሚሆን ኮሚሽኑ አሳስቧል።

በሌላ በኩል ኮሚሽኑ ለአዲስ ማለዳ በላከው ሪፖርት በክልሉ የተከሰተ ጦርነት እና የቀድሞው መስተዳድር መፍረስን ተከትሎ ጾታዊ ጥቃቶች ተፈጽመዋል ብሏል። በዚህም በመቀሌ ከሚገኙ ሕክምና ባለሙያዎች እንዲሁም ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጤና ቢሮ በተገኙ መረጃዎች መሰረት ባለፉት ኹለት ወራት ብቻ በመቀሌ ሆስፒታል 52፣በአይደር ሆስፒታል 27፣ በአዲግራት ሆስፒታል 22፣ በውቅሮ ሆስፒታል 7 በአጠቃላይ 108 (አንድ መቶ ስምንት) የአስገድዶ መድፈር ጥቃቶች ለጤና ተቋማት ሪፖርት ተደርገዋ ሲል አብራርቷል።
በአንዳንድ የሰሜን ምዕራብ እና የምሥራቃዊ ዞን የትግራይ ክልል አካባቢዎች የኤርትራ መንግስት ወታደሮች መኖራቸው ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ጠቅሷል።

የጾታዊ ጥቃት ተጎጂዎች ወንጀሉን ለማሳወቅና የሕክምና እርዳታ ለማግኘት የሚሄዱባቸው እንደ ፖሊስ ጣቢያ እና ጤና ጣቢያ ያሉ ተቋማት በአንዳንድ አካባቢዎች ፈርሰው በመቆየታቸው ሪፖርት የተደረጉ ጥቃቶች ቁጥር ትክክለኛውን የጉዳት መጠንና ስፋት እንደማያመላክት እና የጾታዊ ጥቃት መጠኑ ከዚህ የበለጠ ሊሆን እንደሚችል ኮሚሽኑ አመላክቷል።

እንደ ጤና ዘርፉ ሠራተኞች ማብራሪያ በክልሉ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ የጣለው የሰዓት እላፊ ገደብ የሕክምና እርዳታ ፈላጊዎች በምሽት ወደ ጤና ተቋማት እንዳይሄዱ እንቅፋት መሆኑ አሳሳቢ መሆኑንም ነው ኮሚሽኑ የገለጸው።
ኮሚሽኑ ከጥር ኹለትእስከ ጥር 15/2013 በመቀሌ ከተማ እና በአላማጣ፣ መሆኒ እና ኩኩፍቶ ከተሞች ክትትል እና ምርመራ በማድረግ፣ በተለይም በመቀሌ የሚገኙ ከፍተኛ ወታደራዊ እና ሲቪል አመራሮችን፣ የጤና ዘርፍ ሠራተኞችን፣ ነዋሪዎችን፣ ተጎጂዎችን እና ተፈናቃዮችን ማነጋገሩን ለአዲስ ማለዳ በላከው ሪፖርት አመላክቷል።

በሪፖርቱ እንደተመለከተው ኮሚሽኑ ገና በአካል ተገኝቶ ክትትል ለማድረግ ባልቻለባቸው በርካታ የትግራይ ክልል አካባቢዎችም ጭምር የሰው ሕይወት ማለፉን፣ የአካላዊ እና ሥነልቦናዊ ጉዳት መድረሱን፣ ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት፣ ዘረፋ እና ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ስለመፈጸማቸው መረጃዎች ደርሰውኛል ብሏል።

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ(ዶ/ር) እንደገለጹት በትግራይ ክልል እየደረሰ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት መጠን የሚያመላክቱ በርካታ ጥቆማዎች እና መረጃዎች ቢኖሩም የአካባቢው የፀጥታ ሁኔታ ገና ያልተረጋገጠ በመሆኑ፣ በሲቪል ሰዎች ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን ገና በተሟላ መንገድ ለማወቅ አልተቻለም። ሆኖም ኮሚሽኑ የማጣራትና የመመርመር ስራውን ይቀጥላል ብለዋል።

ዋና ኮሚሽነሩ ኮሚሽኑ ጦርነቱ ያስከተለውን የሞትና የመፈናቀል አደጋ በተመለከተ ኢሰመኮ ያቀረባቸውን ጥሪዎች አስታውሰው ‹‹እጅግ አሳዛኝና አሳሳቢው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ጾታዊ ጥቃትና በሕጻናት ላይ የደረሰው ጥቃትና ጉዳቱ ከዚህ የበለጠ እንዳይስፋፋ ልዩ ትኩረትና ጥረት ይሻል›› ሲሉ አሳስበዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 119 የካቲት 6 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here