አጀንዳዬ የራሴ እንጂ የማንም አይደለም

0
650

በማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛዎች ላይ በተለይም ደግሞ በሥርዓተ ጉዳይ በሚደረጉ ውይይቶች ላይ የሚሰነዘሩት ትችቶች እና መከራከሪያ ሐሳቦች አመክኗዊ መፋለስ ያለባቸው ናቸው የሚሉት ቤተልሔም ነጋሽ፣ ይህ ነገር ከመለመዱ የተነሳ ሥያሜም ተገኝቶለታል በማለት ጽፈዋል።

 

 

ከወራት በፊት ነው። ወጣት ሴቶች በፌስቡክ የሴቶች የወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያ ምርቶችን ለማሰባሰብ ዘመቻ ነበራቸው። ለዚሁ ዓላማ እንዲሆን ሰዎች ገንዘብ መለገስ ብቻ ሳይሆን ምርቶቹን በተመረጡ ቦታዎች ወስዶ በማስቀመጥም ጭምር እንዲተባበሯቸው እየጠየቁ ነበር። የንጽሕና መጠበቂዎቹ በገጠር ላሉ ለተመረጡ ትምህርት ቤቶች ሴት ተማሪዎች እንደሚሰጡም ጭምር ተገልጾ ነበር።
ሐሳቡን እንደሚደግፍ ሰው መረጃውን በገጻቸው ካጋሩ ሰዎች አንዷ ነበርኩ። ያንን ተከትሎ በመረጃው ግርጌ የተሰጠኝን ሐሳብ አልረሳውም። ‘ይህንን የምዕራባውያን መሬት ያልረገጠ ሥራ ከምትሠሩ ሴቶችን የሚጠቅም ሥራ ብትሠሩ ይሻል ነበር’ የሚል ነበር። ይህን ያለው ወንድ ጸሐፊ ነው። በሕይወቱ አንድም ቀን የወር አበባ የማያይ፣ በሴት ልጅ ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ የማያውቅ፣ ሲቀጥልም በኢትዮጵያ የንጽሕና መጠበቂያ አቅርቦት በማጣት ምክንያት በርካታ ሴት ልጆች ከትምህርት ቤት እንደሚቀሩ በጥናት መረጋገጡን ያልሰማ፣ አዲስ አበባ ውስጥ ላሉ ትምህርት ቤቶች መምህራን ገንዘብ እያዋጡ፣ እያሰባሰቡ ለሴት ተማሪዎች ለሌላ ቀን ይህን የነገርኩት ሌላ ወዳጄ ‘አይ እንደው አሁን አንቺ ሞዴስ ተቸግረሽ ነው ያደግሽው’ ብሎኝ እርፍ! ሲጀመር የአንድ የንጽሕና መጠበቂያ ዋጋ ስንት እንደሆን ያውቅ ይሆን? መንግሥት (ተጨማሪ እሴት ታክስ የሚያስከፍልበት ምርት) ብቻ ሳይሆን አብዛኛው የኢትዮጵያ ቤተሰብ በቅንጦት ዕቃ እንደሚመዘግበውስ;
ከዚህም አልፎ እንደ ኬንያ ባሉ አገራት መንግሥት ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የንጽሕና መጠበቂያ እንዲያቀርብ በሕግ መወሰኑን፣ ጉዳዩ የፖሊሲ ጉዳይ ጭምር መሆኑንስ? ለመረጃ ያህል የወር አበባ ማየት የተፈጥሮ ግዴታ ነው፤ ልጅ ከመውለድ ጋር የሚገናኝ ማንኛዋም ሴት ቢያንስ ለ35 ዓመታት በየወሩ (ልጆች በምትወልድበት ወቅት ከሚኖሩት ጥቂት ወራት በስተቀር) የሚገጥማት ክስተት ነው።
አስተያየት ሰጪዬ ያለ ዕውቀትም ይሁን የሴቶች መብቶች ላይ የምንሠራ ሰዎችን አጀንዳ ለማጣጣል ሲል፣ አልያም በሌላ ይበለው ‘ስለዚህ እንጂ ስለዚህኛው፣ ወይም ደግሞ እኔ ስለፈለኩት ካልሆነ ስለ ሌላ ጉዳይ ለምን ታወራላችሁ?’ ማለት በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያው የተለመደ ጉዳይ ነው። ከመለመድ አልፎ ቃልም አለው፤ በእንግሊዝኛው ‘whataboutery’ ወይም ‘whataboutism’ ሲባል ትርጉሙም ተቀናቃኝን ወይም በሌላኛው ወገን ተሰልፏል ብለው የሚያምኑትን ሰው በወግ አጥባቂነት በመኮነን ሐሳቡን በሐሳብ ከመሞገት ወይንም ትክክል አለመሆኑን ከማሳየት ይልቅ ሌላ ነገር እየጠቀሱ ‘ይሔ እያለ ለምን ይህን ታነሳላችሁ?’ የሚል የሐሳብ መፋለስ ነው። ስለንፅሕና መጠበቂያ ከምታወሩ ስለሚደፈሩ ሴቶች ብታወሩ፣ ስለሚደፈሩ ስታወሩ ምን ለብሰው ነው? ስለ ፆታዊ ትንኮሳ ስታወሩ ስለገጠር ሴት ለምን አይወራም? ወዘተ. የሚባሉ ማስቀየሻዎችን ያነሳሉ።
‘ያኛው እያለ ለምን ስለዚህ ይወራል?’ የማለት አባዜ አስቂኝ የሚሆነው በተለይ በሴቶች ጉዳይ ላይ ሲመጣ፣ አንዳንዱን ነገር ለመረዳትና ተፅዕኖውን ለመገንዘብ ሴት መሆን የሚጠይቅ ሆኖ ሳለ ያንን ወደ ጎን በመተው እንደማይረባ ጉዳይ አይቶ ሌላ በሰውየው መረዳት የባሰ አንገብጋቢ የሴት ጉዳይ አለ ሲል ነው።
ይህ ቀላል ምሳሌ ሰዎች የሌላውን ጉዳይ እንደ ጉዳይ የማየት ችግር እንዳለባቸው ለማመልከት የቀረበ ነው። በአብዛኛው የማነሳው ጉዳይ ከሴቶች መብቶች ጋር የተያያዘ ስለሆነ ተፅዕኖ አድርጎብኝ ብቻ ሳይሆን ይህ ጉዳይ ከእኔ ጋር ተመሳሳይ ሐሳቦች የሚያንፀባርቁ ሴትና ወንድ ጓደኞቼ ላይ ሲደርስ ስለምመለከት በእኛ ላይ ይበረታል ብል አላጋነንኩም።
ከሳሽና ተቺ መሆኑ በተለይ ተምሯል፣ አውቋል፣ ያነባል በምንለው የማኅበረሰብ ክፍል ዘንድ ይበረታል። በተለይ የሴቶች መብት ላይ የምንሠራ እና በይፋ ‘ፌሚኒስት’ ነን ብለን በወጣነው ላይ እንደሚበዛ ለመገንዘብ ‘ፌስቡክ’ አልያም ‘ትዊተር’ ላይ ገብቶ የአንዷን ሴት ጽሑፍ ማየት በቂ ነው። ትችቱ ‘እኛም የሴት መብት ጉዳይ ያገባናል፣ እናንተን ብቻ ማን ተቆርቋሪ አደረጋችሁ?’ ከሚሉ ሴቶችም ጭምር የሚመጣ ነው። ‘ፌሚኒስት’ ሴቶችን ያልሆኑትን ሥያሜ በመስጠት፣ በማጥላላት የሚደረገውን ዘመቻ ብንተወው ለመሞገት በሚመስል መልኩ እግር በእግር በመከተል ከላይ የተጠቀሰውን የተፋለሰ ሙግት የመፈፀም አባዜ ብቻ ሳይሆን፥ ይህን በማድረግ ዋጋ ማሳጣት ይቻላል የሚል ዕሳቤም አለበት።
‘በበኩሌ እዚህኛው ላይ ሳይሆን እዛኛው ላይ ለምን አትሠሩም?’ ለሚለው ሐሳብ መቅረብ ያለበት የመጀመሪያ ጥያቄ ‘ይህን ያህል ተቆርቋሪ ከሆናችሁ እናንተ ለምን አትሠሩትም?’ የሚል ነው። ‘የእኔ አጀንዳ ፍሬ ቢስ ከመሰላችሁ ፍሬ ያለውን እናንተ ፈፅማችሁ ለምን አታስተምሩኝም?’ የሚል ነው።
ራሴን ወክዬ ስናገር ደግሞ የትኛውንም አጀንዳ ለማንሳት የማንም ፈቃድ አያስፈልገኝም። ያመንኩበትን ጉዳይ ጉዳዬ አደርገዋለሁ። ጉዳዬ ነው ካልኩ ጉዳዬ ይሆናል ነው ቁም ነገሩ። እንደ ግለሰብም ይሁን ከሌሎች ተመሳሳይ ሐሳብ ካላቸው ሌሎች ሴቶች ጋር ስተባበር የማነሳው ሐሳብ፣ ለእኔ ዋጋ አለው የምለውን፣ እንደ ሰው ሕይወቴን የነካውን፣ ሌሎችን ይነካል ብዬ የምለውን ሐሳብ ነው የማነሳው።
በእርግጥ ሴትን ልጅ ሲያሳድግ ዙሪያዋን መሥመር አሥምሮ በዚህ ሒጂ፣ በዚያ ዉጪ በዚያ ግቢ ማለት ለለመደ ማኅበረሰብ ይህን ማለት ሊከብድ ይችላል። ማሳሰቢያው ግን ስንኖር የግዴታ የሴት ዘርን ወክለን አይደለም። እንደግለሰብ፣ እንደ ሰው፣ ቢበዛ እንደመረጥነው ቡድን አቋም እንጂ።
ካትሊን ሞራን ‘እንዴት ሴት መሆን ይቻላል’ (‘how to be a woman’) በሚል የጻፈችው መጽሐፍ ላይ እንዲህ ትላለች። “ምንም ተባለ ምን፣ በጊዜ ሒደት የገባኝ መሆን የምፈልገው አንድ ነገር ነው። ሰው። ውጤታማ፣ ሐቀኛ፣ በአክብሮት የምስተናገድ ሰው” ብላለች። ይኸው ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 9 ጥር 4 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here