ይሔ ፉክክር አይደለም!

0
499

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ከየትና እንዴት እንዲሁም መቼ እንደሰማሁት ባላውቅም፤ ብቻ ትዝ ይለኛል። ምን ትዝ ይለኛል? የስርዓተ ጾታ ጉዳይ እንደ ብሔር ቢሆንስ ኖሮ የሚለው ሐሳብ። በዚህ ጊዜ ባለማወቅ ተታሎ ኢትዮጵያዊነቱን የዘነጋ ወገኔ፤ እንኳን ብሔሩ ተሰድቦበትና «ሊሰድበኝ እያሰበና እያቀደ ነው!» ብሎ በገዛ ወገኑ ድንጋይ እያነሳ፣ ሰይፍ እየተማዘዘ አይደለ?
እንዲያው ከአገራቸው ጠብበው «ብሔሬ ተነካ!» ብለው ኡኡ እንደሚሉት ሰዎች፤ ሴቶችም ለሴትነታችን እንደዛ ብንሆን፤ ሌላው ቢቀር በየመንገዱ «እናትህን…» እያሉ የሚሳደቡትን እናስተርፋቸው ነበር? በጭራሽ! ግን ዝም ብለን እንዳልሰማ እናልፋለን፤ ልብ ይስጥልን እያልን!
እንደምታውቁት ታድያ የብሔር ብሔረሰቦቻችን ወይም እንደ ሕዝብ የእኛ ችግር ሁሉን ፉክክር ማድረጋችን ነው። አንድ ሰው ስለራሱ መብት ሲጠይቅ፤ አበበ ወይም ከበደ የተባሉ ሌሎች ሰዎችን አጣቅሶና የእነርሱ መብት ስለተከበረ ብሎ አይደለም። ሰው ስለሆነና እንደሰው መብቱ ሊከበር ስለሚገባ ነው። እንዲሁም አንድ ብሔር ተጨቆንኩኝ ብሎ ሲያማርር፤ ሌላው ታሪክ እየመዘዘና ከራሱ ጥቅም አንጻር እያየ፤ «ይሄ ብሔር መብቱ ቢከበርለትና እንዲህ ቢያደርገኝስ!» ሊል አይገባም።
ጊዜው የሩጫና የውድድር ነው። ውድድራችን ግን ከጊዜ ጋር ነው። ከዛሬ አልፈን ነገ ላይ ምን እንመስላለን? ዛሬስ ከትላንትናችን በምን ተሽለናል? እንላለን። ለምሳሌ ተማሪን ራሱን ችሎ ጎበዝ እንዲሆን መገፋፋት አንድ ነገር ነው። «እንዴት እገሌ ይበልጥሃል!?» ማለት ደግሞ ሌላ።
መቼም በዚህ ጊዜ ሁላችን እንደ «ፖለቲከኛ» እየተጫወትን ስለሆነ፤ ነገሩ በዚህ ምሳሌ ይገለጥልናል ብዬ ነው ይህን ማስቀደሜ። እንዲህ ነው! በአጠቃላይ ወንዶች የሴቶችን ጉዳይ ከፉክክር መንፈስ በጸዳ መልኩ ሊያዩት ይገባል። ያ ካልሆነ ዛሬ ላይ የሴቶችን መብት ለማስከበር የሚጥሩ ሰዎች የድካማቸው ፍሬ ሌላ ለሴቶች መብት ታጋይ ሰዎችን መፍጠር ይሆናል።
ወንድሞች ሆይ! እናንተ በሥልጣን ላይ በብዛት ስላላችሁ አይደለም፤ እናንተ ባሻችሁ ሰዓት ያለስጋት መንቀሳቀስ በመቻላችሁ አይደለም፤ እናንተ ከስማችሁ በፊት ያለው ቅጥያ የትዳር ትርክታችሁን መያዝ አለመያዙ አይደለም፤ እናንተ ወጥታችሁ ስለገባችሁም አይደለም ወይም ሌላ። ይህ ሁሉ ስለሆነ አይደለም ሴቷ መብቷን የምትጠይቀው። ሰው ስለሆነች ነው።
የቸገራቸው ሴትን ልጅ እንደ ሰው ተቆጥራ ክብር እንድታገኝ መጠየቁ የማይሆን ሲመስላቸው፤ «ሴት እናት፣ ሚስት፣ እህት፣ ልጅ ናት» ይላሉ። እንደዛ እንኳ ከተረዳችሁት የእናታችሁ፣ የሚስታችሁ፣ የእህታችሁና የልጃችሁ ጥሪ መብቴ ይከበር መሆኑን እንጂ ከእናንተ ጋር የተገባ ፉክክር አለመሆኑን ዕወቁ። ይሄ የሰው የመሆን ጥያቄ ብቻ ነው!

ቅጽ 1 ቁጥር 9 ጥር 4 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here