በአዲስ አበባ 20 ትምህርት ቤቶች በኦሮምኛ ቋንቋ እያስተማሩ ነው

0
549

በአዲስ አበባ 20 ትምህርት ቤቶች ከቅድመ መደበኛ እስከ 9ኛ ክፍል የሚማሩ ከ12 ሺሕ በላይ ተማሪዎችን በኦሮምኛ ቋንቋ እያስተማሩ እንደሚገኙ የከተማዋ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ። በተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች ድርጅት እስከ 25 ሺሕ ብር ወርሃዊ ደሞዝ የሚከፈላቸው መምህራን መኖር ቅሬታን አስነስቷል።
በአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የኦሮምኛ ቋንቋ ዘርፍ የመምህራን ልማት ባለሙያው ብርሃኑ ከበበው ለአዲስ ማለዳ እንዳሉት በከተማዋ 20 ትምህርት ቤቶች ከቅድመ መደበኛ እስከ 9ኛ ክፍል ባለው ደረጃ 12 ሺሕ 460 ተማሪዎች በኦሮምኛ ቋንቋ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ነው። ከእነዚህም ውስጥ ስድስት ሺሕ 223ቱ ሴቶች ናቸው። አሁን ላይ በኦሮምኛ ቋንቋ በማስተማር ላይ ካሉት ትምህርት ቤቶች መካከል 9ኛ ክፍልን እያስተማሩ የሚገኙት አራቱ ሲሆኑ ከዓመት በፊት የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ከፍቷቸው የነበሩት የኦሮምኛ ቋንቋ ትምህርት ቤቶች ናቸው።
በተያዘው የትምህርት ዘመን በኦሮምኛ ቋንቋ የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶችን ከኦሮሚያ ክልል የተረከበውና ተጨማሪ ትምህርት ቤቶችን እያስፋፋ እንዲያስተዳድር የተደረገው የአዲስ አበባው ትምህርት ቢሮ በመጪው የትምህርት ዘመን 10ኛ ክፍል መክፈትን ጨምሮ የተማሪዎችንና ትምህርት ቤቶችን ቁጥር የመጨመር ዕቅድ ይዟል።
አሁን ላይ ላሉት 20 ትምህርት ቤቶች ከ570 በላይ መምህራን ተመድበው በማስተማር ላይ ይገኛሉ። ይሁንና ከትምህርት ቤቶቹ መካከል ባሳለፍነው ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 30 የግንባታ ሥራቸው ተጠናቅቆ በይፋ ለተመረቁት ኹለት ትምህርት ቤት ሠራተኞች ከመንግሥት የመምህራን ደሞዝ እርከን የተጋነነ ክፍያ እየተፈጸመ መሆኑ በሌሎች የአማርኛም ይሁን የኦሮምኛ ቋንቋ ትምህርት ቤቶች መምህራንና ሠራተኞች ላይ ቅሬታን አሳድሯል። ይህም ወደ ኹለቱ ከፍተኛ ደሞዝ ከፋይ ትምህርት ቤቶች ለመቀጠር የሚደረገውን ውድድር ወደ አሻጥር ስለመቀየሩ ይነገራል።
ስለጉዳዩ የጠየቅናቸው ብርሃኑ የኹለቱ ትምህርት ቤቶች አነስተኛው ደሞዝ 14 ሺሕ ከፍተኛው ደግሞ 25 ሺሕ ብር መሆን በሌሎች ትምህርት ቤት መምህራን ላይ ቅሬታን እንደፈጠረና ለመቀጠርም ጤናማ ያልሆነ ውድድርን የሚያነሳሳ ሆኖ እንደተገኘ ተናግረዋል። ይሁንን የተጋነነ ነው የተባለውን ክፍያ የሚፈጽሙትን ትምህርት ቤቶች ከግንባታና የትምህርት ቁሳቁስ ጀምሮ የአጠቃላይ ሠራተኞቹን ደሞዝ ክፍያ ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት የሚሸፍነው መሠረቱን በተባበሩት ዓረብ ኢሚሬቶች ያደረገው አል ማክቱም ፋውንዴሽን ስለመሆኑም አክለዋል። ይሁንና ክፍያው የሌሎች መምህራን ቅሬታ ምንጭ ሆኗል በሚል ከፋውንዴሽኑ ጋር ከጥር 2011 ደመወዝ ጀምሮ የሠራኞቹ ደመወዝ ከሌሎች ትምህርት ቤቶቸ ጋር በሚመሳሰል ደረጃ እንዲከፈላቸውና ቀሪውን በጥቅማጥቅምና ሌሎች ክፍያዎች እንዲሰጣቸው ስምምነት ላይ መደረሱንም ብርሃኑ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ይህ ግን በኹለቱ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ያሉ ሠራተኞች ከዚህ ቀደም ይከፈላቸው የነበረውን የክፍያ መጠን የሚቀንስ እንዳልሆነም ታውቅቋል።
የትምህርት ሚንስትሩ ጥላዬ ጌጤ (ዶ/ር) የኹለቱን ትምህርት ቤቶች በይፋ መከፈት አብስረው በይፋዊ የቲውተር ገጻቸው ፋውንዴሽኑናን መስራቾቹን አመስግነዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 9 ጥር 4 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here