የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር በዋሉት የቀድሞዎቹ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ባለሥልጣናት ላይ ክስ መስርቷል። ክስ ከተመሰረተባቸው ስምንት ግለሰቦች መካከልም ሦስቱ እስካሁን በሕግ ቁጥጥር ስር አለመዋላቸው ታውቋል።
በእነሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኘው መዝግብ ስር ክስ ከተመሰረተባቸው ስምንት ተጠርጣሪዎች መካከል ኮሎኔል ጌትነት ጉድያ፣ ኮሎኔል ጎይቶም ከበደ እና እሌኒ ብርሃን የተባሉ ግለሰቦችን ፖሊስ ካሉበት በመያዝ እንዲያቀርባቸው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ትዕዛዝ ሰጥቷል። በሰባት መዝገቦች ክስ የተመሰረተባቸው የቀድሞ የሜቴክ ባለሥልጣናትና ‹‹በጥቅም ተሳስረው አብረው ሰርተዋል›› የተባሉ ግለሰቦች ሕጋዊ የጨረታ ሥርዓትን ባልጠበቀ መልኩ በርካታ ቢሊዮን ብር በማውጣት ከተለያዩ አገራት የተለያዩ ዓይነት ትራክተሮችን በኮርፖሬሽኑ ስር ለሚገኘው የአዳማ እርሻ መሣሪያዎች ኢንዱስትሪ በማስግባትና ለረጅም ጊዜ ያለሥራ እንዲቆሙ በማደርግ የአገርን ሀብት በማባከን እንዲሁም የሕዝብ ሀብት ለግል ጥቅም በማዋል ከባድ የሙስና ወንጀል መጠርጠራቸውን የዐቃቤ ሕግ ክስ ያሳያል።
የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ኅዳር 3/2011 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ዋና ዐቃቤ ሕጉ ብርሃኑ ፀጋዬ ሜቴክ ያለ ጨረታ ከውጭ አገራት በ37 ቢሊዮን ብር በፈጸማቸው ግዥዎች የአገርና ሕዝብ ሀብት አባክኗል ማለታቸው ይታወሳል። በዚህም መንግሥት የቀድሞውን ዋና ዳሬክተር ሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኛው በከባድ ሙስና ተጠርጥረው ኅዳር 4/2011 ሁመራ ላይ በቁጥጥር ስር መዋላቸው አይዘነጋም።
በአራት መዝገብ ክስ የተመሰረተባቸው የቀድሞ የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄነራል ክንፈ ከሌሎች ተከሳሶች ጋር በመመሳጠር እና መንግሥት የሰጣቸውን ኃላፊነት ወደጎን በመተው በብዙ ቢሊዮን ብር የሚተመኑ ትራክተሮችንና መለዋወጫዎችን በማስገባት ከፍተኛ ኪሳራ በአገር ላይ አድርሰዋል ሲል ዐቀቤ ሕግ አስረድቷል።
በክሱ ላይ 22 የሰውና 24 የሰነድ ማስረጃዎች የቀረቡ ሲሆን አብዛኞቹ የሰነድ ማስረጃዎች በእንግሊዘኛ ቋንቋ የቀረቡ በመሆናቸው ተተርጉመው እንዲቀርቡ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ አስተላልፋል።
በተያያዘ 8ኛ ተከሳሽ ረመዳን ሙሳ የዋስትና መብት የጠየቁ ሲሆን ዐቃቤ ሕግ ተቃውሞታል። የሰሩት ወንጀልም ከ10 ዓመት በላይ የሚስቀጣ በመሆኑ ዋስ ሊፈቀድላቸው አይገባም ያለው ዐቃቤ ሕግ ጥያቄው ውድቅ እንዲሆንለት ችሎቱን ጠይቋል። የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ችሎቱም ተጠርጣሪው የጠየቁትን የዋስ መብት በመሻር ክሳቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ ሲል ወስኗል።
ክሱ የደረሳቸው ተጠርጣሪዎችም ክሱ ላይ መቃወሚያ ለማቅረብ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸው፣ እንዲሁም ብርጋዴር ጀነራል ጠና ቁርንዲም የተከላካይ ጠበቃ ለማቅረብ የጠየቁትን ጊዜ ከግምት ውስጥ ማስገባቱን ፍርድ ቤቱ ገልጿል። ከዚህ ባሻገርም ያልተያዙ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ለሕግ ለማቅረብ የሚያስፈልገው ጊዜ ታስቦ ለጥር 17/2011 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን ችሎቱ አሳውቋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 9 ጥር 4 ቀን 2011