የአስተምህሮው ማዕከል ረቂቅ አዋጅ ጥያቄ አስነሳ

0
577

የሕገ መንግሥትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል ለማቋቋም የወጣዉ ረቂቅ አዋጅ ከፌደሬሽን ምክር ቤት ሥራ ጋር ይጋጫል በሚል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥያቄ አስነሳ። ጥር 4 ቀን ረቂቅ አዋጁን መርምሮ ለዝርዝር እይታ ወደ ሕግ፣ ፍትሕና ዲሞክራሲ ቋሚ ኮሚቴ ለመምራት በተደረገ ዉይይት የፌደሬሽን ምክር ቤት በተመሳሳይ ሁኔታ በሕገ መንግሥት አስተምህሮ ላይ የሚሰራዉ ሥራ ስላለ አዲሱ አስተምህሮ ማዕከል ምን የተለየ ነገር ይሰራል የሚል ጥያቄ ተነስቶበታል። ከዚህ ቀደም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ከፌደሬሽን ምክር ቤት ሥልጣን ጋር ይጋጫል በሚል የተነሱ አዋጆች ላይ ክርክር እንደተነሳባቸዉ የሚታወስ ሲሆን ለዚህም በዋናነት የወሰን ፣የማንነት እና አስተዳደር ኮሚሽን እና የእርቀ ሰላም ኮሚሽንን ማንሳት ይቻላል።
ከምክር ቤት በተነሳዉ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ አስተያየት የሰጡት የፌደራሊዝም ምሁር የሆኑት እና በአማካሪነት ሥራ ላይ የሚገኙት ቴዎድሮስ ንብረት ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ፌደሬሽን ምክር ቤትን በአስተምህሮዉ ዙሪያ ማሻሻያ እንዲያደርግ ማጎልበት ነበር ትክክለኛዉ አካሄድ ይላሉ። አያይዘዉም በዚህ ዉስን በሆነ የአገሪቱ የበጀት አቅም ተመሳሳይ ሥራ የሚሰራ ሌላ ማዕከል ማቋቋም ጉዳቱ ከፍተኛ ነዉ ብለዋል። በሌላ በኩል ደግሞ በሰላም እና ደኅንነት የዶክትሬት ዲግሪ ያላቸዉ ስማቸዉ እንዳይገለፅ የፈለጉ ግለሰብ በበኩላቸዉ ”የማዕከሉ መቋቋም ትክክል ነዉ” ሲሉ ይጀምራሉ አያይዘዉም የተለያዩ ችግሮች በአገር አቀፍ ደረጃ በተከሰቱ ቁጥር የፌደራሊዝም እና የሕገመንግሥት ዕዉቀት ማነስ ነዉ እየተባለ ባለበት ሁኔታ ይህ የአስተምህሮ ማዕከል መቋቋም እጅግ ጠቃሚ ነዉ ይላሉ። ነገር ግን ከዛ በፊት የሰላም እና የሥርዓተ ፆታ አስተምህሮዎች ቢቀድሙ የበለጠ ጠቀሜታ ይኖረዋል ሲሉ አስተያየታቸዉን አጠቃለዋል።
ፌደሬሽን ምክር ቤት ከዚህ ቀደም በሕገ መንግሥት አስተምህሮ ዙሪያ ሰፊ ስራ ይሰራ እንደነበር ይታወቃል። ነገር ግን በዋናነት የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት ብቻ ስለነበሩ ተሳታፊ የነበሩት እና የዘርፉ ሙያተኞችን ያላካተተ ስለነበር ከፍተኛ ችግሮች ታይተዉበታል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በእስካሁን ሂደት ይህ ነዉ ሊባል የሚችል ዉጤታማ አስተምህሮ ሥራ አለ ብሎ መናገር አዳጋች ነዉ በማለት በአዲሱ ረቂቅ ላይ ለመጠቆም ተሞክሯል።
በሌላም በኩል በፌደሬሽን ምክር ቤት የተዘረጋዉ የሕገ መንግስትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ባልተደራጀ መልኩ የሚከናወን፣ የክትትልና ግምገማ ሥርዓት ያልተዘረጋለት እና ቅንጅታዊ አሰራርን ያልተከተል እንደነበር ለማወቅ ተችሏል። ከዚህም በተጨማሪ አስተምህሮዉ ተደራሽና አሳታፊ እነዳልነበርም ታዉቋል።
በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ላይ ለመግለፅ እንደተሞከረዉ አዲሱ የሕገ መንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ መዕከል ከዚህ በፊት በፌደሬሽን ምክር ቤት በኩል በሕገ መንግሥት አስተምህሮ ላይ የታዩ ክፍተቶችን ለመሙላትና፤ በቀጣይም ክፍተቶችን በየጊዜዉ እያጠና በሕገ መንግሥትና ፌዴራሊዝም አስተምህሮ ላይ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ተብሏል። የተጠቀሱትን ክፍተቶች ታሳቢ በማድረግ የፌደሬሽን ምክር ቤት ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት በመስራት አስተምህሮዉ በሥርዓት የሚመራበትን ስትራቴጂ ቀርጿል። ከተደራሽነትና አካታችነት ጋር በተያያዘ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተነሳዉ ጥያቄ ይህ የአስተምህሮ ማዕከል ተደራሽነቱን ለማስፋት ክልሎች ላይ ቅርንጫፍ ማዕከላት የሚከፈቱበትን መንገድ አንስተዋል።
ተጠሪነቱ ለፌደሬሽን ምክር ቤት የሆነዉና በዋና ዳይሬክተር የሚመራዉ የሕገ መንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከል እንደ መዕከል የተለያዩ ተግባራትን ያከናዉናል። ከእነዚህም ዉስጥ የሕገ መንግሥትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ዉጤታማ ለማድረግ የሚያስችል መርሐ ግብርና ፕሮጀክቶች ይቀርፃል ፣ የስልጠና ሞጁል ያዘጋጃል። በረቂቅ አዋጁ ላይ በተቀመጠዉ መሰረት ማዕከሉ የንብረት ባለቤት የመሆን መብት ያለዉ ሲሆን ራሱን ችሎ መክሰስም ሆነ መከሰስ ይችላል።የማዕከሉ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ በሙሉ ደምጽ ወደ ሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 9 ጥር 4 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here