በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ በ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚገነባው የሲሚንቶ ፋብሪካ በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠለት።
ፋብሪካው በኢትዮጵያው ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ እና በቻይና ዌስት ኢንተርናሽናል ድርጅት በሽርክና የሚገነባ ነው።
የ18 ወራት ጊዜ በተያዘለት የመጀመሪያው የግንባታ ምዕራፍ ሶስት ፋብሪካዎች ወደስራ የሚገቡ ሲሆን በቀን 10 ሺሕ ቶን ሲሚንቶ፤ በዓመት 30 ሚሊዮን ካሬ ሜትር ጂፕሰም ቦርድ እና በቀን 600 ቶን መስታወት የሚያመርቱ ናቸው።
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ “ድህነትም ሆነ ሀብታምነት ከፈጣሪ የተሰጠ ስጦታ አይደለም፤ኢትዮጵያዊያን ድህነትን ከጫንቃችን ላይ አራግፈን መጣል ካልቻልን የሌሎች ተፅዕኖ አይቀርልንም” ብለዋል።
የለሚ ፋብሪካ መገንባትም በድህነት ላይ ለሚደረገው ዘመቻ ትልቁ መብራት ነው ብለዋል፤
ሁሉም አንድ የጋራ አገር እንዳለው በመረዳት ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት በትብብር መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው ከለውጡ በኋላ ሁሉም ክልሎች በመልማት ፀጋቸው ልክ መልማት የሚችሉበት ፍትሃዊ አሠራር ሰፍኗል ብለዋል።
“ለውጡ ባይመጣ ኖሮ ይህ ፋብሪካ እዚህ አይገነባም ነበር የት እንደሚሄድም እናውቃለን” ብለዋል።
የአማራ ክልል መንግስት በክልሉ ሠላም በማስፈንና ለባለሃብቶች ምቹ የሥራ አካባቢ በመፍጠር ሌት ተቀን እንደሚሠራ ገልጸዋል።
በክልሉ ከፍተኛ የሀይል እጥረት መኖሩን የገለጹት አገኘሁ፤ የፌዴራል መንግስት በአገሪቷ አቅም ልክ የተመጣጠነ የኃይል አቅርቦት ማመቻቸት እንዳለበትም ጠይቀዋል።
ቅጽ 2 ቁጥር 122 የካቲት 27 2013



