ዓመታዊ የተሽከርካሪ ፈቃድ ማደሻ (ቦሎ) ክፍያ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል እንደሚፈጸም ተገለጸ

0
831

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዓመታዊ የተሽከርካሪ ፈቃድ ማደሻ ክፍያ ለመሰብሰብ ከመንገድ ፈንድ ጽህፈት ቤት ጋር ስምምነት ላይ መድረሱን አስታወቀ። ስምምነቱን የባንኩ የማዕከላዊ ሪጂን ምክትል ፕሬዚዳንት ኪዳኔ መንገሻ እና የመንገድ ፈንድ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ራሺድ መሃመድ ፈርመዋል።
በዚሁ ወቅት ኪዳኔ መንገሻ ስምምነቱ በኢትዮጵያ የሚገኙ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ የተሽከርካሪ ባለቤቶችን የዘመናዊ ክፍያ አሠራር ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ነው የገለጹት።
ደንበኞች የክፍያ አገልግሎቱን በባንኩ ቅርንጫፎች፣ በፖስታ ቤት በሚገኙ የፖስ (POS) ማሽኖች እንዲሁም በኢንተርኔት የባንክ አገልግሎት በኩል በፍጥነት ያለእንግልት ማግኘት እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል።
ኪዳኔ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 53 በመቶ የሚሆነውን አገልግሎቱን በዲጂታል ስርዓት አማካኝትት በመፈፀም ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ ይህም የጥሬ ገንዘብ ዝውውርን በማስቀረት ህብረተሰቡን የዘመናዊ ክፍያ ሥርዓት ተጠቃሚ የማድረግ ጥረት አካል ነው ብለዋል። ራሺድ በበኩላቸው በዓመታዊ የተሸከርካሪ ፈቃድ ማደሻ ክፍያ ከ3 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚሰበሰብ ገልፀዋል። የክፍያ አገልግሎቱ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል መደረጉ ደንበኞችንም ጽህፈት ቤቱንም የተቀላጠፈ አገልግሎት ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።
በተለይ ከዚህ በፊት ወደ መንገድ ፈንድ መግባት ያለበትን ገንዘብ ሀሰተኛ ሰነድ በመጠቀም ይፈፀም የነበረውን ማጭበርበር ያስቀራል፣ የጽህፈት ቤቱን የክፍያ መሰብሰብ አቅም ያሳድጋል ብለዋል ዋና ዳይሬክተሩ።
የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ሃና አርዓያሥላሴ በበኩላቸው በአዲሱ የክፍያ ስርዓት በባንኩ በቅርንጫፎች፣ ከፖስታ ቤት ቅርንጫፍ ጋር በተገናኘ የፖስ ማሽን እንዲሁም በኢንተርኔት ባንኪንግ አሠራር ክፍያቸውን የፈጸሙ ደንበኞች የሚያገኙትን የክፍያ ደረሰኝ እና የተሽከርካሪ ሊብሬያቸውን ለፖስታ ቤት በማቅረብ የክፍያ ማረጋገጫ ካገኙ በኋላ ለትራንስፖርት ባለሥልጣን በማሳየት ዓመታዊ ቦሎ መውሰድ እንደሚችሉ ገልጸዋል።


ቅጽ 2 ቁጥር 122 የካቲት 27 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here