ታሪክ አንድን አገር ከዜጎች መፈቃቀድ፣ መከባበር ብሎም መተሳሰብ መሳ ለመሳ እየገነባ እና ታሪካዊ ትምህርት እየሰጠ አገርን ወደ ፊት የሚያስቀጥል እንዱ አምድ ነው። አንድ አገር ታዲያ የተለያዩ አይነት ታሪኮችን ሊያስተናግድ እና ሊታዘብ ይችላል። በታሪክም ውስጥ ታዲያ ሁሉም አኩሪ ሁሉም ደግሞ አንገት የሚያስደፋ ባይንም ነገር ግን እንደ አገር የአንድ አገር ታሪክ ናቸው እና ሲዘከሩ የሚኖሩ ናቸው።
መልካም ታሪኮች ለወደፊት መማሪያ እና መኩሪያ፣ አንገትን ቀና ማድረጊያ የመሆናቸውን ያህል በአንጻሩ ደግሞ ከመጥፎ የሆነው የአገር ታሪክ አንገትን የሚያስደፋ እና ዳግመኛ እንዳይከሰት ትምህርት መውሰጃ ለአገር ብሎም ለሰፊው ዓለም መማሪያ ሆኖ የሚቀጥልም ይሆናል ማለት ነው። በተለያዩ የዓለም አገራት የራሳቸው ደግም ሆነ መጥፎ ታሪክ ያላቸው ሲሆን ዓለምም ይህን ታሪካቸውን በራሱ ላይ እንዳይፈጠር አስቀድሞ ትምህርት የወሰደበት ከአገራቱ ታሪክነት ባለፈም የዓለም ታሪክ ሆኖው የቀጠሉ እና አሁንም ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበሩ እና የሚዘከሩ የታሪክ ጠባሳዎች መኖራቸው የማይታበል ሀቅ ነው።
በመልካም ጎን ተነስተው ደግሞ እንዲሁ የሰው ልጆችን ጉልህ ተጋድሎ በታሪክ ውስጥ ተዘክሮ አሁኑ እና መጪው ትውልድ ሊማርባቸው እና ሊያስቀጥላቸው የሚገቡ ታሪኮችም በዛው ልክ ይስተዋላሉ።
በአገራችን ኢትዮጵያም አንገት አስደፊ ታሪክ የመኖራቸውን ያህል የአልበገር ባይነት፣ የጀግንነት፣ የእምቢ ባይነት እና ከራስ በፊት ለአገር እና ለወገን መኖር እና መሞትን የሚያስተጋቡ የተጋድሎ ታሪኮችም ኢትዮጵያን እንደ አገር አስቀጥለዋት እናያለን። አንድነት የተሰበከባቸው፣ መተሳሰር የተስተዋለባቸው፣ አገራዊ አንድነት ከፍ ብሎ የተውለበለበባቸው ጋራ ድሎች እልፍ እና እልፍ እንደሆኑም የታሪክ ድርሳናት ያወሳሉ። ምስራቁ ከምዕራቡ ጋር ተጋምዶ፤ ሰሜኑ ደቡቡን አቅፎ አገር አቆይቷል፣ ዳር ድንበር አስከብሯል፣ በዋናነት ደግሞ አገር ሳትደፈር አስቀጥሏል። የተለያዩ ጊዜያት ነገስታት ራሳቸውን ዜና መዋዕል ቢያስከትቡም ነገር ግን ዞሮ ዞሮ ትልቁን ስዕል ስንመለከት ግን ለአገር እና ዳር ድንበር ያፈሰሱትን ደም እና የገበሩትን መስዋዕትነት እንመለከታለት ስንኮራበትም እንኖራለን።
በኢትዮጵያ ታዲያ በአኩሪነታቸው ከሚጠቀሱት አገራዊ የታሪክ ኹነቶች ውስጥ የጥቁር ሕዝብ ድል ነው እየተባለ ሚዘከረው የአድዋ ድል አንዱ እና ግንባር ቀደሙ ነው። ይህ ድል የቅኝ ግዛት ህልሙን ለማሳካት ከአውሮፓ ተጉዞ መስራቅ አፍሪካዊቷን አገር ለመውረር ያሰበውን የኢጣሊያን ጦር በጀግኖች አርበኞች እና የአገርን ዳር ድንበር እያስከበሩ መሰዋት ክብራቸው በሆኑ የአገር ምሶሶ ኢትዮጵያዊያን አድዋ ተራራ ሶሎዳ አናት ላይ ድባቅ የተመታበት ታሪካዊ ኹነት ነው። ይህ ኹነት ታዲያ በእርግጥም ኢትዮጵያዊያን ከሌሎች አፍሪካዊያን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በተለየ ሁኔታ እንድንኖር ያደረገን፣ አንገታችን በየትኛውም የዓለም አደባባይ ላይ ቀና አድርገን እንድንራመድ እና በጉልህ ድምጻችንን አሰምተን እንድንናገር ያደረገን የማንነታችን መሰረትም ነው። ይህን ስንል ደግሞ የነጻነት ምድር ከሆነችው አገራችን አርማዋ የሆነውን አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ሰንደቅ ሌሎች አፍሪካዊያን እንደ ነጻነት ምልክት በመውሰድም የራሳቸውን ሰንደቅ መፍጠር የቻሉበት መነሻ እስከ መሆንም የደረስንበት የታሪክ ኹነትም ነበር።
ይሁን እንጂ ይህ ከኢትዮጵያ አልፎ አፍሪካ ብሎም መላው ጥቁር የቆዳ ቀለም ያለው ሁሉ የሚዘክረው እና የሚኮራበት ታሪካዊ ኩራት ከጊዜያት ወዲህ በፖለቲካ ሲሸበብ እና ፖለቲካዊ አቋም እንዲሁም አመለካከት ሲያንሻፍፈው ይታያል። ምንም እንኳን አድዋን በአድዋነቱ ምንም አይነት ብዥታ በየትኛውም ወገን ዘንድ እንደሌለ ቢታወቅም ነገር ግን የድል በዓሉን በማክበሩ ሂደት ግን ከባድ የሆነ ሽኩቻ እና የፖለቲካ ጨዋታ እንዳለ አዲስ ማለዳ ትታዘባለች። አድዋን የማክበሪያ ስፍራ እና አድዋን ከአድዋ የጦር አዝማቹ ወይም በጊዜው አገርን ከመሩት ንጉስ አጼ ምኒልክ ውጪ የማክበር እንቅስቃሴዎችን ማየትም የተለመደ መሆኑን አዲስ ማለዳ በጽኑ ትገነዘባለች ይህንንም ታወግዛለች።
ታሪክ ደህናም ሆነ መጥፎ እንደ ታሪክነቱ የሚዘከር እና ለተተኪው ትውልድ የሚተላለፍ እንጂ የፖለቲካው ንፋስ በተቀያየረ ጊዜ አብሮ የሚቀየር እና ቅርጹን እየቀያየረ የሚከበር ሳይሆን እንደወረደ፤ እንደተፈጠረው ገድል፣ ጀግኖች ሳይሰስቱ የገበሩትን ነብስ በማሰብ እንደሆነም ሊታወቅ ይገባል። አገርን ለማስተዳደር ታሪክ አጋጣሚ ያገኘ ሁሉ የሚበርዘው ሳይሆን ካለፈው የአድዋ ጀግንነት በመማር አገርን የማስተዳደር ጥበብ፣ ሕዝብን በአንድነት አስተሳስሮ ለአንድ አላማ የማሰለፍ ችሎታን የሚማሩበት እንዲሆን አሁንም አዲስ ማለዳ አበክራ ታሳስባለች። በኢህአዴግ ዘመን የነበረውን እና አድዋ በተመለከተ በአጼ ምኒልክ በኩል የሚሰነዘሩ መረጃዎች መኖራቸውን የሚታወስ ነው። ይህንንም ተከትሎ የአድዋ ድል ሲነሳ አብሮ መነሳት ያለበት አጼ ምኒልክ ሳይሆኑ በሻ አዋሎም ናቸው እስከመባል የተደረሰበት አጋጣሚም ነበር።
ይህ ጉዳይ በእርግጥ ታሪክን የሚያደበዝዝ ባይሆንም ነገር ግን በተወሰነ መልኩ የሚበር በመሆኑ በርካቶች ሲቃወሙት እንደነበርም ይታወሳል። ይህ አካሔድ ደግሞ ዘንድሮ ለ125ኛ ጊዜ የተከበረው የአድዋ ድል በተለያዩ ስፍራዎች ተበታትኖ የመከበሩ አጋጣሚ ከአድዋ አንድነት ስሜትም የሚቀረን መሆኑን አዲስ ማለዳ ተገንዝባለች። ከዚህም ጋር ተያይዞ በመስቀል አደባባይ የጠቅላይ ሚንስትር አቢይ አሕመድን እና የደጅ አዝማች ባልቻ ሳፎን ፎቶ በመስቀል እንዲከበር ማድረግ ቢያንስ የአጼ ምኒልክም ሆነ የባለቤታቸው የእቴጌ ጠሀይቱን መስዋዕትነት መዘንጋት ነው ስትልም አዲስ ማለዳ ታስባለች። በእርግጥ የደጅ አዝማች ባልቻ ሳፎ ገድል ከማንም በላይ እንደሆነ እና አገርን ለማዳን ክቡር ሕይወታቸውን ለመስጠት የቆረጡ በኋላም በድል የተመለሱ አገር አውራ ለመሆናቸው ይህ ትውልድ ብሎም ቀጣዩ ሲዘክራቸው ይኖራል። ጠቅላይ ሚንስትር አቢይም ቢሆኑ በዘመናዊት ኢትዮጵያ ስሟን በዓለም መድረክ ያስጠሩ የኖቤልን የሰላም ሽልማት ውጥንቅጧ የወጣን አገር አንድ አድርገው በማስቀጠል የተሸለሙ የአገር መሪ ብቻም ሳይሆኑ የቁርጥ ቀን ልጅ ለመሆናቸው እንኳን ዜጎች ባዕዳን የሚመሰክሩት ሀቅ ነው። ነገር ግን የአድዋ ድል ላይ መዘከር ካለባቸው በጊዜው የነበሩ የአገር መሪዎች፣ እና ነገስታት እንሆኑ ግን አዲስ ማለዳ ታምናለች። በመሆኑም ከዚህ በኋላም ያለፈው ማለፉ በቂ ሆኖ ነገር ግን ትክክለኛ ትምህርት ሰጥቶን ማለፉን እርግጠኛ መሆን እንዳለብን አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። ታሪክ በፖለቲካ ንፋስ የማይነዳ የአገር መሶሶ መሆን እንዳለበትም ታሳስባለች። ይህም ደግሞ የሚመለከተው አካል ልብ ሊለው እና ከታሪክ ላይ እጁን እንዲሰበስብም አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።
ቅጽ 2 ቁጥር 122 የካቲት 27 2013


