በማኅበራዊ ብዙኃን መገናኛዎች፣ በተለይም በፌስቡክ እና ትዊተር የመብት አራማጆች በፖለቲካዊ ክስተቶች ላይ እና ሌሎችንም የሕዝብ ፍላጎት ለመጠየቅ ‘ድምፅ መሰብሰብ’ን (polling) እንደ ስልት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። ይሁንና እንዲህ ዓይነቶቹ ‘ድምፅ አሰባሰብ’ ስርዓቶች ከመደበኛ ምርምር አካሔድ አንፃር ትክክለኛ ናሙና (‘ሳምፕል’) ስለማይኖራቸው ውጤታቸው ምንም አያመለክትም የሚል ትችት እየተሰነዘረባቸው ይገኛል። ከዚያም በላይ የሕዝባዊ ድምፅ አሰባሰብ አሠራሮች ፀረ ዴሞክራሲያዊ አካሔዶች ናቸው ብለው የሚከራከሩ አሉ። በኢትዮጵያም አሁን እየተከለሰ ባለው የምርጫ አዋጅ ፖለቲካዊ ፓርቲዎችን የሚያወዳድር የሕዝብ ድምፅ መሰብሰብ እና ውጤቱን ማወጅ ተከልክሏል። ይህም የሆነበት ምክንያት ምርጫ ቦርድ በሚያዘጋጀው ምርጫ የሚሰጠውን ድምፅ ተቀባይነት ያሳጣዋል፤ ለውዝግብም ይዳርጋል በሚል እንደሆነ በተለያዩ አጋጣሚዎች ተገልጿል።
ዴሞክራሲ ወቅቱን እየጠበቀ በሚካሔድ ምርጫ ብቻ አይገለጽም። የዴሞክራሲ ዋነኛው መለያው ሕዝባዊ ተሳትፎ እንደመሆኑ፣ በምርጫ ወቅት ብቻ ሳይሆን በምርጫዎች መካከል ባለው ጊዜ ሕዝቦች በሚመለከቷቸው ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ እና ተፅዕኖ ማድረግ የሚችሉባቸው መንገዶች መኖር አለባቸው። የሕዝብ አስተያየት ድምፅ አሰባሰብ ስርዓትም የዚሁ አካል ነው ብለው የሚያምኑ ደግሞ በሌላ ወገን አሉ።
የኦክስፎርድ ዩንቨርስቲዎቹ ምሁራን ካሮል ሌዊስ እና በርትሌይ ሂልደርት እ.ኤ.አ. በ2012 ባቀረቡት ‘የአስተያየት ድምፆችን መሰብሰብ’ በዴሞክራሲ ውስጥ ስለሚኖረው አዎንታዊ እና አሉታዊ ተፅዕኖ የሚተነትን ጥናታዊ መጣጥፍ ላይ እንዳመላከቱት “የተሰበሰቡ ድምፆች ተጠምዝዘው ሊቀርቡ፣ ግልጽነት የሚጎድላቸው እና በቃላት የታጨቁ ይዘቶች ሊኖሯቸው፣ ለናሙና አመራረጥ መንሻፈፍ፣ እንዲሁም ለትንታኔ ዝምመት እና ቸልተኝነት ተጋላጭ በመሆናቸው የሕዝብን አስተያየት በተሳሳተ መንገድ ለመረዳት ሊዳርጉ ይችላሉ።”
‘የሕዝብ ድምፅ ማሰባሰብ’ እና ቅኝት (‘ሰርቬይ’) ማድረግ የሕዝቡን አስተያየት ይፋ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ የሕዝቡን አስተያየት ቅርፅ ለማስያዝም አገልግሎት ሊውል ይችላል።
Debate.org የተባለ ድረገጽ በጉዳዩ ላይ ‘ሕዝባዊ የአስተያየት ድምፅ’ ሰብስቦ ነበር። ‘የአስተያየት ድምፅ ማሰባሰቦች ዴሞክራሲን ይጎዱታል?’ ለሚለው ጥያቄ 57 በመቶ የሚሆኑት መላሾች ‘አዎ፣ ይጎዳዋል’ የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። ዶኒ እና ቶማስ ማን የተባሉ ‘የብሩኪንግስ’ (በአሜሪካ የሚገኝ የፖሊሲ ጥናት ተቋም) ጸሐፊዎችም የአስተያየት ድምፅ መሰብሰብ ጥሩም፣ መጥፎም አስቀያሚም ገጽታ እንዳለው ጽፈዋል። ጽሑፋቸውን የደመደሙበትን እኛም እዚህ እንጠቀምበት፦ “ድምፅ መሰብሰቢያ መሣሪያ ነው እንጂ መርሕ አይደለም።… ሮናልድ ሬገን እንዳሉት ‘እያመናችሁ አረጋግጡ’” ይሉና፣ ገዢዎች ሕዝቦች መሆን አለባቸው ሆኖም የአስተያየት ድምፆችን በመሰብሰብ ፖሊሲዎችን መወሰንና የሕዝብን ፈቃድ ለመጠምዘዝ መሞከር ሊኖር ስለሚችል ጥንቃቄ ያስፈልጋል ይላሉ።
ቅጽ 1 ቁጥር 9 ጥር 4 ቀን 2011