የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአዲስ አበባ ምርጫ ሙሉ እድሉን ባለደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባለደራስ) እንዲጠቀመበት መፍቀዱን ባልደራስ አስታወቀ።
የአብን እና ባልደራስ በአዲስ አበባ ጉዳይ በጋራ ለመንቀሳቀስ ከዚህ ቀደም ትብብር መፍጠራቸው የሚታወስ ነው። ‹‹የእናንተ ድምጽ እንዳይከፋፈል ብሎ አብን አዲስ አበባን ለኛ ለቀቀልን።›› ሲሉ የባልደራስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በቃሉ አጥናፉ(ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
በቃሉ አክለውም አብን በአዲስ አበባ ጉዳይ ባልደራስ ለአገር ደህንነት፣ አንድነትና ለሕዝብ ጥቅም የቆመ ፓርቲ ነው መሆኑን በማመን ባልደራስ በአዲስ አበባ እንድወዳደር ቦታውን እንደለቀቀለት ነው ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ የተናገሩት።
አብን በአዲስ አበባ ምርጫ ሙሉ ቦታውን ለባልደራስ መልቀቁ ከባልደራስ በላይ የአብንን ትልቅነት አመላካች ሲሉ በቃሉ ገልጸውታል። በቃሉ አክለውም አብን ይህን ያደረገው የሚሰራው ለአገር ደህንነትና ለህዝብ ጥቅም ብሎ ስለሆነ ነው ብለዋል።
ባልዴራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አገራዊ ፓርቲ አለመሆኑን ያስታወሱት በቃሉ፣ ባልደራስ አገራዊ ፓርቲ ባይሆንም በተለያዩ አከባቢዎች ደጋፊዎች እንዳሉት በቃሉ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል። በመሆኑም አብን አዲስ አበባን ለባልደራስ በቅንነት እንደሰጠሁ ሁሉ ባልደራስም አብን በሚወዳደርባቸው ቦታዎች ያሉት ደጋፎዎቹ አብንን እንድደግፉ ሀሳብ እንደሚቀርብ ተመላክቷል።
አብን አዲስ አበባ ላይ እጩዎችን አለማቅረቡን የገለጹት በቃሉ፣ አብን ያቀረባቸው እጩዎች በባልደራስ ሥም እንደቀረቡ ነው የተቆሙት።
በአዲስ አበባ ምርጫ የፊታችን ግንቦት 28/2013 በሚደረገው አገራዊ ምርጫ ተገዳዳሪ የሚሆኑት ፓርቲዎች የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ)፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አበን)ና ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሚክራሲ ፓርቲ ናቸው ሲሉ በቃሉ ገልጸዋል።
ባልደራስ በአዲስ አበባ አንድ እጩ ቢጎድልበትም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሙሉ እጩዎቹን ማስመዝገቡን የጠቆሙት በቃሉ፣ በአዲስ አበባ ምርጫ ማጭበርበር ካልተከሰተ ባልደራስ ጠንካራ ተገዳዳሪ ሆኖ እንደሚሸንፍ እምነት አንዳላቸው ተናግረዋል። ባልደራስ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 23 እጩዎችን አስመዝግቧል። ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ማቅረብ የሚገባው 138 እጩዎች ቢሆንም በስህተት ባላጠመ ስህተት አንድ እጩ ሳይመዘገብ ቀርቶ 138 እጩዎችን አስመዝግቧል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ(ባልደራስ) መጋቢት 9/2013 በራስ አምባ ሆቴል ስለመሰረቱት ፖለቲካዊ ትብብር በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ፓርቲዎቹ ለወራት ሲያደርጉት የነበረውን ድርድር አጠናቀው በቀጣዩ አገራዊ ምርጫ አሸናፊ ለመሆንና አገርና ሕዝብን ለማሻገር በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ላይ መድረሳቸውን የገለፁ ሲሆን በቀጣይም ሌሎች ፓርቲዎችን በማቀፍ የበጎ ኃይሎች ጥምረት ለመፍጠር እንደሚሰሩ ገልፀዋል።
ፓርቲዎቹ አሁን የፈጠሩት ሕብረት ለሌሎች አርዓያ የሚሆንና ከመጠላለፍና ከሴራ ፖለቲካ ርቆ የሕዝብን ጥቅም በዘላቂነት ለማስጠበቅ የሚያስችል በመሆኑ እስከአሁን በተለያዩ ምክንያቶች አብሮ ለመስራት ያልቻሉ ፓርቲዎችም ሕብረቱን እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል።
አብን አገርና ሕዝብን ለማዳን በሊሂቃንና በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል መቀራረብ እና በጋራ መስራት እንዲኖር ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን የገለፁት የአብን ሊቀመንበር በለጠ ሞላ ትብብሩ የሕዝባችን ድምጽ እንዳይከፋፈል ከማድረግ በዘለለ ጽንፈኛና ጸረ ሕዝብ ኃይሎችን ከፖለቲካ ምኅዳሩ ለማስወጣት ሚናው የጎላ መሆኑን ገልፀዋል።
በለጠ አክለውም አብንና ባልደራስ የጀመሩትን ሕዝብን ያስቀደመ ትብብር ሌሎችም ለመቀላቀል ፍላጎቶች መኖራቸውንና ውጤቱን በተመለከተ ለሕዝቡ በቀጣይ ይፋ የሚደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የመዋቅራዊና ሥርዓታዊ ችግሮቻችንን ሰንኮፍ ነቅሎ የሁሉም የሆነ ሥርዓት ማስፈኛ ጊዜው አሁን ነው!
ቅጽ 2 ቁጥር 124 መጋቢት 11 2013



