6ኛውን አገራዊ የምርጫ ሒደት ተከትሎ የሚነሱ የምርጫ ክርክር ጉዳዮች በልዩ ሁኔታ የሚያስተናገዱበት ፍርድ ቤቶች እየተደራጁ መሆኑ ታውቋል።
የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንትና የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ቃል አቀባይ አቶ ተስፋዬ ንዋይ በአገሪቷ ምርጫን በበላይነት የሚመራው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሚሰጣቸውን ውሳኔዎች መነሻ በማድረግ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ለፍርድ ቤት ማቅረብ እንደሚቻል በአዋጅ መደንገጉን ገልጸዋል።
ይሕን ተከትሎም ለሚነሱ ክርክሮች አፋጣኝ ውሳኔ መስጠት የሚያስችሉ ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቷል።
ረቂቅ ደንቡ የመራጮችና የዕጩዎች ምዝግባ፣ የስነ-ምግባር ጥሰት፣ የድምፅ አሰጣጥና ቆጠራን አስመልክቶ ለሚነሱ ክርክሮች ፈጣን ውሳኔን መስጠት የሚያስችሉ አካሔዶችን ማስቀመጡን ጠቁመዋል።
ፍርድ ቤቶቹ የምርጫ ጉዳይ ክርክሮችን ቅዳሜና እሑድ እንዲሁም በሕዝብ በዓላት ቀን ጭምር የሚያስተናግዱ እንዲሆን ይደነግጋል ነው ያሉት አቶ ተስፋዬ።
የምርጫ ጉዳዮች ብቻ የሚዳኙባቸው 10 ችሎቶች በከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ 11 ችሎቶች ደግሞ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ስር መደራጀታቸውንም ጠቁመዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 125 መጋቢት 18 2013



