የምግብ እና መድኃኒት አስተዳደርን እና ቁጥጥርን በተመለከተ ረቂቅ አዋጅ ወጥቶ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመርቷል። ኢሳያስ መኮንን ረቂቁን ተመልክተውና ከነባሮቹ አዋጆች እና አሠራሮች አንፃር በመገምገም ሙያዊ ትችታቸውን በሚከተለው መልኩ አሰናድተው ልከውልናል። ክፍል አንድን እነሆ።
በአገራችን የምግብ እና የመድኃኒት አስተዳደርን አስመልክቶ ከዚህ ቀደም የተለያዩ ሕጎች የወጡ ሲሆን እነዚህ ሕጎች በየጊዜው እየተፈተሹ ጥናቶችም በዓለም አቀፍ ደረጃ ባሉ ተቋማት እና በአገር ደረጃም ጭምር እየተሠሩ ያሉባቸውን ችግሮች ለመቅረፍ እየተሻሻሉ እና እየተለወጡ ይገኛል። የምግብ እና የመድኃኒት አስተዳደርን በተመለከተ በአሁኑ ሰዓት ላይ በተግባር ላይ ያለውና እየተሠራበት የሚገኘው በ2002 የወጣው “የምግብ፣ የመድኃኒት እና ጤና ክብካቤ አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 661/2002” የተሰኘው ሕግ ሲሆን፥ በዚህ ሕግ መነሻነትም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ2006 ዝርዝር ድንጋጌዎችን ያካተተውን “የምግብ፣ የመድኃኒት እና ጤና ክብካቤ አስተዳደር እና ቁጥጥር ደንብ ቁጥር 299/2006” አውጥቶ በሥራ ላይ ይገኛል።
ባለሥልጣኑ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ ከ2002 ጀምሮ በአዋጁ ውስጥ ከሌሎች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ጋር የሥልጣን መደራረብ እና የግልጽነት ችግር፣ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ግብዓቶች እና አገልግሎቶች የትርጉም ችግር፣ የድንጋጌ ክፍተቶች፣ እና ሌሎች ግድፈቶች እንዳሉበት ከአሠራር፣ ከተገልጋዮች እና ከባለድርሻ አካላት በየጊዜው ይነሱ ነበር። እነዚህን ክፍተቶችንም ለመሙላት ባለሥልጣኑ ችግሮችን ለመፈተሽ እና ለመፍታት በማሰብ የሕጎቹን ክፍተቶች የሚያጠና እና የመፍትሔ ሐሳብ የሚያቀርብ ቡድን በመመሥረት ከ2006 ጀምሮ ሲያስጠና ከቆየ በኋላ ይህም አጥኚ ቡድኑ ዝርዝር ችግሮቹን በመለየት መፍትሔ ሐሳቦችንም በመለየት መሻሻል ያለባቸው ነገሮች ላይ ባቀረበው የውሳኔ ሐሳብ መነሻነት የተሻሻለ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ እንዲቀርብ መደረጉን ከባለሥልጣኑ የተገኘው መረጃ ያሳያል። የዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነውም በዚህ የአጥኚ ቡድን አባላት ማሻሻያ ሐሳቦች መነሻነት የተረቀቀውን እና በሚኒስትሮች ምክር ቤት ዘንድ ቀርቦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲያፀድቀወ የላከውን የምግብ እና የመድኃኒት አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ።
ረቂቅ አዋጁ በዘጠኝ ክፍሎች የተከፋፈለ ሲሆን ጠቅላላ ድንጋጌዎች፣ ስለ አስፈፃሚ አካላት፣ የምግብ ደኅንነት ቁጥጥር፣ የመድኃኒት፣ የሕክምና መሣሪያ እና የውበት መጠበቂያ ቁጥጥር፤ የትምባሆ ምርት እና የኤሌክትሮኒክ ኒኮቲን መስጫ መሣሪያ ቁጥጥር፣ ስለ ኢንስፔክተር (የጤና ተቆጣጣሪ) ሥልጣን፣ ተግባርና ግዴታ፣ ክልከላዎች፣ ስለ አስተዳዳራዊ እርምጃና የወንጀል ቅጣት እና ሌሎች ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች የሚመለከቱ 88 አንቀፆችን አካቷል። በረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ ላይ በግልጽ እንደተመለከተው አዋጅ ቁጥር 661/2002 ረቂቅ አዋጅ አንፃር ሲታይ ረቂቁ የ661/2002 ድንጋጌዎችን ከፍ ባለ ደረጃ የሚለውጥ እና መሠረታዊ ይዘቱንም የሚቀይር ስለሆነና በረቂቅ አዋጅ የተካተቱ ጉዳዮችን በማሻሻያ ማውጣት አስቸጋሪ ወይም አዳጋች ስለሆነ ነባሩን አዋጅ ቁጥር 661/2002 በመሻር ሙሉ በሙሉ አዲስ ሕግ ሆኖ እንዲወጣ ማድረግ የተሻለ አማራጭ ሆኖ ስለተገኘ ረቂቁ ሙሉ በሙሉ አዲስ ሕግ ሆኖ እንዲወጣ በሚያስችል መልኩ እንደተዘጋጀ ነው። የዚህ ጽሑፍ ዓላማም የዚህን ረቂቅ አዋጅ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች ፈትሾ ሙያዊ አስተያየት መስጠት ነው።
የረቂቅ አዋጁ ጠንካራ ጎኖች
ረቂቅ አዋጁ በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ቁጥር 661/2002ን እንደመነሻ በማድረግ ያለበትን ችግሮች በማጥናት የመፍትሔ ሐሳቦችን ያቀረበ እና የድንጋጌዎቹም አካል አድርጎ ያስቀመጠ መሆኑ በተነፃፃሪነት የተሻለ ፍሬ ነገሮችን ይዞ ይገኛል። ረቂቅ አዋጁ አሁን ካለው የአገራችን የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዕድገትና ለውጥ አኳያ የጤና ቁጥጥሩ ስርዓት ከሕግ፣ ከአደረጃጀትና ከአሠራር አንፃር እንደገና መፈተሹ የኅብረተሰቡን ጤና የሚያውኩ ችግሮችን በውጤታማነት ለመቆጣጠር ችግር እንዳያጋጥም እና እየተስፋፋ የመጣውን የኢንዱስትሪና የማምረቻ ዘርፍን ለመደገፍ የራሱን አስተዋፅዖ ያደርጋል።
ረቂቅ አዋጁ መንግሥት የሕዝብን ጥቅም ለማስከበር ያለበትን ኃላፊነትን ከመወጣት ጋር ተዛምዶ ባለው መልኩ በአገሪቱ መሠረታዊ የመድኃኒት ዝርዝር ውስጥ የተካተተ ወይም በብዛት የሚሰራጭ መድኃኒት ወይም የሕክምና መሣሪያ በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋ እንዲሆን የሚያስገድድ ድንጋጌ፣ መድኃኒት ወይም የሕክምና መሣሪያን ከውጭ ለማስገባት በአምራች እና ከ3 በማይበልጡ አስመጭዎች መካከል የሚደረግ ሥምምነት ከአገሪቱ የንግድ ውድድር እና የሸማቾች ጥበቃ ሕግ ጋር የሚፃረር በመሆኑ አሠራሩን ዕውቅና እንደማይሰጠው የሚያስገድድ ድንጋጌ፣ እንዲሁም የተወሰኑ የመድኃኒት ነጋዴዎች ምርታቸው በስፋት እንዲሸጥላቸው እና ከነጋዴዎች ጋር የጥቅም ግንኙነት ያላቸው የጤና ባለሙያዎች መድኃኒትን በንግድ ሥም በማዘዝ ታካሚውን/ተገልጋዩን ከአቅም በላይ ለሆነ ወጪ ሊዳርጉ ስለሚችሉ የጤና ባለሙያዎች በመርሕ ደረጃ መድኃኒትን በፅንስ ሥም እንዲያዙ የሚያስገድደው ድንጋጌ ማስቀመጡ የተሻለ የሚያደርገው ነው። ጸሐፊው ከታች መስተካከል አለባቸው ብሎ የሚያምንባቸው ነጥቦች እንደተጠበቁ ሆነው፥ ረቂቅ አዋጁ የኅብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ በተለይም የወጣቶች ጤና ለመጠበቅ ከግምት አስገብቶ የኤሌክትሮኒክስ ትንባሆ እና ሺሻን መጠቀምን መከልከሉ የአልኮል መጠጥ አጠቃቀም፣ ሽያጭ እና ማስታወቂያ ጋር ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ ጠንከር ያሉ ገደቦች መቀመጣቸው የወንጀል ኃላፊነት በሚያስከትልም ሁኔታም መደንገጉ በጠንካራ ጎንነት የሚታይለት ነው።
በሌላ በኩል በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ቁጥር 661/2002 ሥር ትንባሆን የሚመለከት የፍሬ ነገር ድንጋጌ ስላልነበርና አዋጁ ከወጣ በኋላ ኢትዮጵያ በዓለም ጤና ድርጅት የወጣውን የትንባሆ ቁጥጥር ሥምምነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥምምነቱን በአዋጅ ቁጥር 822/2006 መሠረት አድርጋ ስላፀደቀች ይህ የፀደቀው ሥምምነትም የአባል አገራትን ግዴታ የሚጥል፣ ሊከተሉት የሚገባውን መርሖዎች የሚያስቀምጥ፣ በሕጎቻቸው ላይ አካተው እንዲያወጡ የሚያስገድድ ይዘት ያለው በመሆኑ የፍሬ ነገር ድንጋጌዎችን በአዋጅ ደረጃ መደንገጉ መደረጉ ረቂቅ አዋጁን የተሻለ የሚያደርገው ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ሳይነሳ መታለፍ ያለበትን ትልቅ ነጥብ ቢኖር በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ቁጥር 661/2002 ትንባሆን የሚመለከት የፍሬ ነገር ድንጋጌ ሳይኖረው የሚኒስትሮች ምክር ቤት በደንብ ቁጥር 299/2006 የፍሬ ነገር ድንጋጌዎችን ማውጣቱ ተገቢ እንዳልነበርና ከተሰጠው ሥልጣን ውጪም የወጣ ሕግም መሆኑ ከግምት መግባት ያለበት ነው።
በኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜያት እየወጡ ያሉ ሕጎች ላይ በአዋጅ ደረጃ ያልወጣንና የዜጎች ሰብኣዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ ገደብ የሚጥሉ ድንጋጌዎች እንዲሁም መብትንና ግዴታን የሚያስቀምጡ ድንጋጌዎችን የሕዝብ እንደራሴ በሆኑት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚያወጣው አዋጅ መውጣት ሲገባ የፍሬ ነገር ድንጋጌን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደረጃ በደንብ እንዲሁም አስፈፃሚ መሥሪያ ቤቶች ወይም ሚኒስቴሮች በመመሪያ ሲያወጡ የሚታይበትን ሁኔታ አግባብ አለመሆኑን አስተምሮ የሚሔድ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ረቂቅ አዋጁ ትንባሆን በተመለከተ ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም በደንብ ቁጥር 299/2006 እና ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በተለያየ ጊዜ ያወጣቸውን የፍሬ ነገር ድንጋጌ የያዙ መመሪያዎች ወደ አዋጅ ደረጃ ከፍ ያደረገና የሕግ አወጣጥ ስርዓትን በአግባቡ ለመከተል ጥረት ያደረገ በጠንካራ ጎንነት የሚታይ ነው።
ረቂቅ አዋጁ በአዋጅ ቁጥር 661/2002 ላይ የተካተቱ የነበሩ እንዲሁም ከሌሎች የመንግሥት አስፈፃሚ አካላት ሕጎች እና ሥልጣኖች ጋር ግጭት የነበረባቸውን ድንጋጌዎች በማስተካከል መውጣት ያለበትን በማውጣት በሌላ ተቆጣጣሪ አካላት አጠቃላይ የቁጥጥር ማዕቀፍ ሥር እንዲገባ ማድረጉ በጠንካራ ጎንነት የሚታይ ነው።
የረቂቅ አዋጁ የሥያሜ እና የአቀራረፅ ችግሮች
የረቂቅ አዋጁ አሁን በሥራ ላይ ከሚገኘው አዋጅ ቁጥር 661/2002 የምግብና የመድኃኒት አስተዳደርን በመለየት የጤና ክብካቤ አስተዳደር እና ቁጥጥር ዘርፍ አካል የነበሩትን ድንጋጌዎች በማውጣት የተዘጋጀ መሆኑን ለማየት ይቻላል።
ጸሐፊው ለመረዳት እንደቻለው ይህ ረቂቅ አዋጅ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ከተቋሙ ሥያሜ ጀምሮ ተግባርና ኃላፊነቱ ተደርጎ የተሰጠውን ሥልጣኑ ላይ የምግብ እና የመድኃኒትን ጥራት አስመልክቶ ያሉትን ሥራዎችን በመለየት በአንድ ዘርፍ እና በአንድ ተቋም ለማስተዳደር እና ለመቆጣጠርን መሠረት አድርጎ የተዘጋጀ ሲሆን የጤና ክብካቤ አስተዳደር እና ቁጥጥር ሥራ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ደግሞ ቀድሞ ባለው አዋጅ ቀጥሎ ለማስኬድ የሚሻሻሉ ነገሮችም ካሉት የጤና ክብካቤ አስተዳደር እና ቁጥጥር ተግባራትን በአንድ የሕግ ማዕቀፍ በሌላ ጊዜ ለማውጣት ያለመ ነው።
ይህም ማለት ረቂቅ አዋጁ የምግብ እና የመድኃኒት አስተዳደርን የመከታተል እና የመቆጣጠር ሥራን የሚሠራ ተቋምን ብቻውን ችሎ በአዲስ መልክ ለማቋቋም፣ ባለሥልጣኑንም ለሁለት ለመክፈል እና የጤና ክብካቤ ዘርፍ የሆኑ ሥራዎችንም የሚሠራ አዲስ ተቋም ለመመሥረት ያለመ አካሔድ ላይ የተነደፈ ነው። ጸሐፊው እንደሚገነዘበው ግን አንድ የሕግ ማዕቀፍ የሚዘጋጀው በተለይም መሠረታዊ መርሖዎች የሚዘጋጀው፣ ሕጉም የሚዋቀረው፣ የአስተዳደር እና የቁጥጥር ሥራን በዋነኛነት የሚያከናውነውን ተቋም የሥራ ሁኔታ ተንተርሶ መሆን የለበትም። የምግብም የመድኃኒትም ሆነ ሌሎች ጤና እና ጤና ነክ ሕጎች የዜጎች ጤናን ለመጠበቅ ታስቦ እንደ አገር ሊኖረን የሚገባንን ደረጃ ምን መምሰል እንዳለበት፣ ዜጎች ሊያከብሯቸው የሚገቧቸው ደንቦች ምን መሆን እንዳለባቸው ማዕቀፍ የማስቀመጥን ዓላማ አድርጎ መሆን ይገባዋል።
ረቂቅ አዋጁ የምግብ እና የመድኃኒት አስተዳደርን የሚመራውን አካል ሥራና ተግባርና ታሳቢ አድርጎ የተዋቀረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከአዋጁ ርዕስ እና መግቢያ ጋር ምንም ዓይነት ዝምድና የሌላቸውን ምናልባትም የጤና አገልግሎት ዘርፍ እና በሌሎች ሕጎች ላይ ሊጠቃለሉ የሚችሉ ድንጋጌዎች አካቶ ይገኛል። ለአብነት ያህል በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 27 ላይ የተጠቃለለው የሕክምና ሙከራ ድንጋጌ፣ በአንቀጽ 29 እና 37 ላይ የተጠቃለለው ስለ ሕክምና መሣሪያ የሚያወሳው ድንጋጌ፣ በአንቀፅ 30 ላይ የተቀመጠው ስለ ደም እና የደም ተዋፅዖ የተመለከተው ድንጋጌ፣ በክፍል አራት ንዑስ ክፍል ሁለት ላይ ከአንቀፅ 42 እስከ 45 የውበት መጠበቂያ ምርትን በተመለከተ የተቀመጡት ድንጋጌዎች፣ በክፍል አምስት ላይ ከአንቀጽ 46 እስከ 52 ድረስ ስለ ትምባሆ እና ተያያዥ ምርቶች አስተዳደር በሚል ርዕስ የተካተቱት ድንጋጌዎች እንዲሁም በሌሎችም በረቂቁ አዋጅ የተለያዩ ቦታዎች ላይ የተቀመጡት ድንጋጌዎች ምግብ እና መድኃኒት አስተዳደርን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች አይደሉም።
እነዚህ አንቀፆች ምግብና መድኃኒት አስተዳደርን ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው መሆኑን ለመገንዘብ ረቂቅ አዋጁ ስለ ምግብ እና ስለ መድኃኒት ምንነት በትርጉም ክፍሉ ላይ በአንቀፅ 2 (1) እና 2 (7) ላይ በግልጽ የተቀመጡትን የትርጉም ድንጋጌዎች አይቶ መረዳት ይቻላል። በጸሐፊው እምነት ረቂቅ አዋጁ ስለ ምግብ እና መድኃኒት ብቻ የማያወሳ ስለሆነ የተፈፃሚነት ወሰኑም (አንቀጽ 3) ምግብ እና መድኃኒት ላይ ብቻ ያተኮረ ስላይደለ ርዕሱ ሁሉንም ቁጥጥር ሊደረግባቸው የታሰቡ ነገሮችን የሚዳስስ መሆኑን የሚገልጽ ሥያሜ ሊሰጠው ይገባል፣ አልያም ከምግብ እና ከመድኃኒት ቁጥጥር ውጪ ያሉ ድንጋጌዎች ከረቂቅ አዋጁ ላይ ማውጣት ያስፈልጋል የሚል እምነት አለው። ለምሳሌ ረቂቅ አዋጁ “የምግብ፣ የመድኃኒት፣ የሕክምና መሣሪያ፣ የውበት መጠበቂያ እና የትንባሆ አስተዳደር አዋጅ” የሚል ሥያሜ ቢሰጠው መፍትሔ ይሆናል።
በሌላ በኩል ረቂቅ አዋጁ ሲዘጋጅ በአዋጅ ቁጥር 661/2002 ላይ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት ታሳቢ አድርጎ ሆኖ ሳለ የጤና ክብካቤ ወይም አገልግሎት ዘርፍን ግን የማሻሻያው አካል አለመሆኑ ከመግቢያው ላይ ከተገለጹት ነጥቦች እና ከተፈፃሚነት ወሰኑ ድንጋጌ ላይ ለመረዳት ይቻላል። ነገር ግን ረቂቁ ከመግቢያው እና ከተፈፃሚነት ወሰኑ ውጭ በመውጣት በጤና ክብካቤ ወይም አገልግሎት አስተዳደር ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን አካቶ ይገኛል። ከላይ ከተገለጹት የሕክምና ሙከራን እና የደም እና ደም ተዋፅዖን የሚዳስሱ ድንጋጌዎችን በተጨማሪ በረቂቅ አዋጁ በአንቀጽ 72 ላይ ስለተላለፈ ሥልጣን እና ተግባር እና በአንቀጽ 73 ላይ የተቀመጠው የመሸጋገሪያ ድንጋጌ በተመለከተ የተቀመጡት ድንጋጌዎች ከዚህ አዋጅ ጋር ምንም ተያያዥነት የሌላቸው ድንጋጌዎች ናቸው። እንደውም ረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 70 (1) ላይ ስለ ተሻሩ እና ተፈፃሚነት የሌላቸው ሕጎች በሚለው አንቀፅ ውስጥ “በዚህ አዋጅ መሠረት የተደነገገጉ ጉዳዮችን በሚመለከት አዋጅ ቁጥር 661/2002 ተሽሯል” በሚል የተቀመጠው ድንጋጌ የአንቀፅ 72 እና 73 አስፈላጊ አለመሆንን በደንብ የሚያስገነዝብ ነው። ምክንያቱም ይህ ረቂቅ አዋጅ በአዋጅ ቁጥር 661/2002 ላይ ያሉትን ሁሉንም ድንጋጌዎች ያልሻረ በመሆኑ ሥልጣንና ተግባር ለማስተላለፍ እንዲሁም የመሸጋገሪያ ድንጋጌ ማስቀመጥ አያስፈልገውም። እንዲያውም ሥልጣንና ተግባርን ለማስተላለፍ እና ለሚመለከተው አካል ለመስጠት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ሊያወጣው በሚችል ደንብ ላይ ማጠቃለል የሚቻል ሆኖ ሳለ ምንም ዝምድና በሌለው አዋጅ ጋር አምጥቶ ማያያዝ ተገቢነት አለው ተብሎ የሚታመን አይደለም።
በመጨረሻም ቀጥተኛ መልዕክቱን ለማስተላለፍ የሚያስችል አቻ የአማርኛ ቃል ከማጣት፣ እንዲሁም የሕክምና እና የመድኃኒት ቅመማ ሳይንስ ውስጥ የሚጠቀሱ ቃላትን አካቶ የሚገኝ እንደሆነ በሚያስመስል መልኩ፣ ረቂቅ አዋጁ በቁጥር ከ43 በላይ የእንግሊዘኛ ቃላትን ተጠቅሟል። ነገር ግን በጸሐፊው እምነት ቀጥተኛ አቻ ትርጉም የማይገኝባቸውን በተለይም ሳይንሳዊ ሥያሜ ካላቸው ቃላት ውጭ ያሉ እንዲሁ በቀላሉ በዕለት ተለት ሕይወታችን ጥቅም ላይ እየዋሉ እንደ ‘ኢንተርኔት’ (በይነመረብ)፣ ‘ጋይድላይን’ (መመሪያ ወይም መሪ ሐሳቦች)፣ ‘ማኑፋክቸሪንግ’ (አምራች)፣ ‘ሶፍትዌር (የኮምፒውተር አውታር) እና ሌሎችንም ቃላትን እየለዩ አቻቸው በሆኑት አማርኛ ቃላት የመለወጥ ሥራ ቢሠራ የተሻለ ነው። ከቃላት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ በቅርብ ጊዜያት በአገራችን እየወጡ ያሉ ሌሎች ሕግጋትም ችግሩ በስፋት እየታየ መሆኑን የምንታዘበው ጉዳይ ነው።
ስለ አስተዳደራዊ እና የወንጀል ቅጣቶች
ረቂቅ አዋጁ ከዚህ ቀደም ወጥተው ከነበሩ ጤና እና ጤና ነክ ሕጎች በተለየ እና በአዲስ መልኩ በአዋጁ ላይ የተካተቱትን መሠረታዊ ድንጋጌዎች የማያከብሩ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች ላይ አስተዳደራዊ እና የወንጀል ቅጣቶችን የሚያስከትልባቸው መሆኑን የሚያስገነዝቡ ድንጋጌዎችን አካቶ ይገኛል። የእነዚህ ድንጋጌዎች መካተት በጤና እና ጤና ነክ ሕጎች ላይ ሲወጡ የነበሩት ሕጎች ላይ ሲሰጣቸውን የነበረውን ‘ጥርስ የሌላቸው አንበሳ ሕጎች’ የሚል ተረት አዘል ሥያሜን የሚቀይር እና የሕጎቹም ቅጣት አዘል በመሆናቸው በተገቢው መልኩ እንዲፈፀሙ መንገድ የሚያበጅ ይመስላል።
የአስተዳደራዊ እና የወንጀል ቅጣቶች በረቂቅ አዋጁ መካተቱ ይበል የሚያሰኝ ሆኖ ሳለ ግን የድንጋጌዎቹ አቀራረብ ግን ለትርጉም ክፍት የሆነ፣ የጥፋቱን ዓይነት፣ ልክ እና ክብደት ያላገናዘበ፣ ሁሉንም አጥፊዎች በአንድ ቅርጫት ውስጥ ከትቶ የሚመለከት እንዲሁም የድንጋጌዎቹ አቀራረፅ የወንጀል ሕግን መሠረታዊ ፍልስፍናዎች የተከተለ አይመስልም። እነዚህን ነጥቦች በዝርዝር ለመመልከት እንሞክር፦
የአስተዳደራዊ እርምጃዎች ድንጋጌ አቀራረፅ
የአስተዳደራዊ እርምጃዎችን በረቂቅ አዋጁ ላይ ሲያስቀምጥ አስተዳደራዊ እርምጃ የሚያስከትሉ ወይም የሚያስወስዱ ጥፋቶችን ምንነት ግልጽና በዘርፍ ዘርፍ በመለየት የሚያስቀምጥ አይደለም። የእርምጃው ልክም ዝቅተኛ፣ መካከለኛ ወይም ከባድ የሆኑትን በአግባቡ ለክቶ እና ለይቶም የማስቀመጥ ችግሮች ይታይበታል። በሌላ አገላለጽ ረቂቅ አዋጁ በአንቀጽ 65 ላይ ስለ አስተዳደራዊ እርምጃ ሲደነግግ ጥፋቱን፣ የጥፋቱን ጥልቀትም ሆነ የእርምጃ አወሳሰድ ልኮችን በአንድ ላይ በዐሥር ንዑስ አንቀፆች አጭቆ የያዘ ነው። ይህ ዓይነት አቀራረብ በአሠራር ላይ ትልቅ ክፍተት የሚፈጥር ይሆናል። አጥፊ አካላትን ላጠፉት ጥፋት ተገቢውን ቅጣት እንዳያገኙ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ አስፈፃሚውንም አካል ሕጉን ያለአግባብ በተግባር ላይ እንዲያውለው ለብልሹ አሠራርም ሊያጋልጥ ይችላል።
በአገራችን ከዚህ ቀደም የአስተዳደራዊ እርምጃዎችን አስመልክቶ የሚደረግጉ ሕጎች ከዚህ ረቂቅ አዋጅ ጋር ሲተያይ የተሻለ አቀራረብ ያላቸው ናቸው። ለአብነት ያህል የታክስ አስተዳደር አዋጅን ብንመለከት የአስተዳደራዊ እርምጃን ሲደነግግ የሕጉ አንድ ምዕራፍ በማድረግ በዘርፍ ዘርፍ የጥፋቶቹን ዓይነት በመለየት የሚያስከትሉትንም የቅጣት ልክ ለይቶ ያስቀምጣል (የፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ 983/2008 አንቀጽ 101 እስከ 113 ያሉትን ድንጋጌዎች መመልከት ይቻላል)። እንዲሁም በታክስ አስተዳደር አዋጁ ላይ ልዩ ልዩ ቅጣቶችን በግልጽ በአንድ አንቀፅ (በአንቀፅ 114) ላይ ያስቀምጣል የአስተዳደራዊ ቅጣት አወሳሰን መንገድም በምን አግባብ እንደሆነ ራሱን በቻለ አንቀፅ ደንግጎ ይገኛል።
ይህ ዓይነት አቀራረብ በአሠራር የሚፈጠርን አለመግባባት ለመፍታት የራሱ የሆነ አስተዋፅዖ ያለው ነው። በመሆኑም በጸሐፊው እምነት በረቂቅ አዋጁ ላይ ስለ አስተዳደራዊ እርምጃዎች የተቀመጠው ድንጋጌ በዘርፍ ዘርፍ የጥፋቱን ምንነት፣ ክብደት መጠን በመለየት ከነቅጣቱ በግልጽ ማስቀመጥ ይገባዋል።
(ሳምንት ይቀጥላል)
ኢሳያስ መኮንን የሕግ አማካሪ እና የማናቸውም ፍርድ ቤት ጠበቃ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው
esayasmeklawoffice@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።
ቅጽ 1 ቁጥር 9 ጥር 4 ቀን 2011