“ለትምህርት ዕድገት የለፋነው ተማሪዎች የሚያነሱት ጥያቄ እንደሚመጣ ዘንግተነው አይደለም”

0
1079

ብርሃኑ ሰሙ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኩር የሆነውን የዛሬውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ የሚያትተውንና በአክሊሉ ሀብቴ (ዶ/ር) የተጻፈውን “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ፡ የከፍተኛ ትምህርት መቋቋምና መስፋፋት በኢትዮጵያ” የሚል መጽሐፍ ይዘት እንሚከተለው በአጭሩ ያስቃኙናል።

 

 

በአገርና ሕዝባችን ባሕል፣ ዕውቀት፣ ማንነት… ላይ ሳይመሠረት ማደጉና መስፋፋቱ፣ ዛሬ ላይ በቁጭት ሲያወያይና ሲያነጋገር የሚታየው “ዘመናዊ” ትምህርት፣ የአፄ ምኒልክ ዘመንን መነሻ አድርጎ፣ በ1900 ለዘርፉ ቀዳሚ የነበረው ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት በተከፈተ ማግስት፣ ጅማሬውን ወደ ዩኒቨርሲቲ የማሳደግ ዕቅድ እንደነበር፣ ፍላጎቱም ዓመታት በወሰደ ጥረት፣ በብዙ ውጣ ውረድ እውን ሊሆን የቻለበትን ሒደትና ታሪክ በስፋት የሚያስቃኝ መጽሐፍ በቅርቡ ለአንባቢያን ቀርቧል።
ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን በሐምሌ ወር 1920 በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ተገኝተው “ከጥቂት ዘመናት በኋላ ትልቁን ትምህርት የሚማሩበት ዩኒቨርሲቲ በዚሁ በአገራችን በኢትዮጵያ እንዲቆምላችሁ ተስፋ እናደርጋለን” ብለው ነበር የሚለውን መረጃ የያዘው ጥራዝ፣ በ629 ገጾች ተጠርዞ፣ “የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ የከፍተኛ ትምህርት መቋቋምና መስፋፋት በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ፣ አክሊሉ ሀብቴ (ዶ/ር) የተዘጋጀ ሲሆን ጥራዙ ከአገር ውጭ በታይዋን የታተመ ነው።
የራስ ተፈሪ ንግግር ብዙ ጥያቄዎች እንዲነሱ የሚጋብዝ ነው። ንግሥት ዘውዲቱ አባታቸው ያሠሯቸውን አብያተ ክርስቲያናትን ለማደስና አዳዲስም ለመትከል ይተጉ በነበረበት ዘመን፥ አልጋ ወራሽ የነበሩት ልዑል ራስ ተፈሪ ከባሕላዊው ይልቅ “ዘመናዊ”ውን ትምህርት የማስፋፋት ምኞታቸው መነሻ ምን ነበር? ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት በተከፈተ በ20ኛው ዓመት “ዘመናዊ” ትምህርትን ወደ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ለማሳደግ ያሳሰበውና ያስገደደው፣ አገራዊና ዓለማቀፋዊ እውነታስ? “ዘመናዊ” ዕውቀት ለማስፋፋት አፄ ምኒልክ የጀመሩትን በተሻለ ሁኔታ በማስፋፋት የሚታወቁት አፄ ኃይለሥላሴ በአልጋ ወራሽነት ዘመናቸው የተመኙትን ዩኒቨርሲቲ የማቋቋም ምኞት እውን ለማድግ ሦስት ዐሥርት ዓመታት ሊወስድባቸው እንዴት ቻለ? ዕቅዱ የተወጠነበትን ጨምሮ ከ90 ዓመት በላይ ያስቆጠረው “ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ” ታሪኩ ሳይጻፍ ይህን ያህል ዘመናት የመቆጠራቸውስ ምክንያት ምን ይሆን? የሚል።
ልዑል ራስ ተፈሪ መኮንን በ1920 በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ተገኝተው በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ እንደሚቋቋምና የአገሪቱ ተማሪዎችም የዚያ ዕድል ተጠቃሚ የሚሆኑበት ዘመን እንደሚመጣ ተስፋና እምነታቸውን ሲገልጹ፥ አክሊሉ ሀብቴ ይህን ዓለም አልተቀላቀሉም ነበር። አክሊሉ ሀብቴ ነሐሴ 26 ቀን 1921 ነበር የተወለዱት። አክሊሉ ሳይወለዱ በፊት ታቅዶ፣ በብዙ ውጣ ውረድ እውን ስለሆነው ዩኒቨርሲቲ ታሪክ ለመጻፍ “ዋነኛው ሰው” እንዲሆኑ ያስቻላቸውን ዕድል እንዴት ሊያገኙ እንደቻሉ፥ ጌታቸው ኃይሌ (ፕሮፌሰር) በመጽሐፉ “ቀዳሚ ቃል” ገጽ የሚከተለውን ምስክርነት ሰጥተውላቸዋል፦
“ይህን ታሪክ በአሁኑ ሰዓት ከአክሊሉ በቀር ማንም ሌላ ሰው እንዲህ አሟልቶ ሊጽፍልን እንደማይችል ማንም ይረዳል። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ አገራችን ከፋሽስት ወረራ እንደተላቀቀች፣ ዘመናዊ ትምህርት ሲጀመር፣ ከተጀመረባቸው ልጆች አንዱ አክሊሉ ነበር። ዳዊቱን እንደደገመና የቃል ትምህርቱን እንደ ጨረሰ በአርበኞች ትምህርት ቤትና በሊሴ ገብረማርያም አድርጎ፣ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ገባ። ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅን ያቋቋሙት የተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት አስተማሪዎችና የፈረንሳይ ካናዳ ኢየሱሳውያን ነበሩ። እነዚም አስተማሪዎቹ ሆኑ። ለትምህርት ባለው ፍቅር ምክንያት ለዶክትሬቱ የመረጠው ትምህርት ‘ትምህርት’ን ነበር። የዶክትሬት ትምህርቱን አጠናቆ ከአሜሪካን ሲመለስ፣ የተቀጠረው ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በመምህርነት ነው። ከዚያም የዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ዲን በመጨረሻም የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሆኖ ጠመንጃ ዕውቀት ሰጥቶናል ያሉ ደርጎች አገሪቱን እስኪያመሰቃቅሏት ድረስ አገሩን ያገለገለው በትምህርት መስክ ነው።”
በአምስት ክፍሎችና በዐሥራ አንድ ምዕራፎች ተከፋፍሎ የቀረበው የአክሊሉ ሀብቴ መጽሐፍ ቀዳሚው ክፍልና ምዕራፍ ሙሉ ለሙሉ ስለ “ጥንታዊው፣ አገራዊ ሥርዓተ ትምህርት ቅርስ” መረጃ የቀረበበት ነው። እሴቶቹንም በዝርዝር አስቀምጧል። ከዚህ በመነሳት “ዘመናዊ” ትምህርት አገራችን ከየት ተነስቶ፣ በምን ውጣ ውረድ ውስጥ አልፎ ዛሬ እስከደረሰበት ያለውን ዕድገት ያስቃኛል። ደራሲው አፄ ኃይለሥላሴ “ዘመናዊ” ትምህርት ለማስፋፋት ከፍተኛ ጥረት ያደረጉበትን ምክንያቶች መርምረዋል። ንጉሡ ለትምህርት የነበራቸው ጽኑ እምነት ከየት መጣ? ይህ እምነት በአእምሯቸው እንዴት ሊቀረፅ ቻለ? አገሪቱን ወደ ዘመናዊነት ለመለወጥ መሠረቱ ትምህርት ነው ብለው ለማመን እንዴት በቁ? ብለው ጠይቀዋል።
የአፄ ኃይለሥላሴ ትምህርት አፍቃሪነት ከተገለጸባቸው ማሳያዎች መሐል አፄ ምኒልክ ትምህርት ቤት አቋቁመው “በቤተ መንግሥት አካባቢ የነበሩትን የዘመዶቻቸውንና የመኳንንቱን ልጆች መርጠው እንዲማሩ ሲያደርጉ ተፈሪን በዚያን ጊዜ አልጨመሯቸውም ነበር። ተፈሪ ግን የሆነውን ሲያውቁ” ለአፄ ምኒልክ መማር እንደሚፈልጉ ነግረው ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ገብተው እንዲማሩ ያስፈቀዱበት ታሪክ አንዱ ማሳያ ነው። ልዑል ራስ ተፈሪ መኮንን ንግሥት ዘውዲቱ ሲነግሡ በአልጋ ወራሽነት ሊያስመርጣቸው የቻለው ትምህርትን መሠረት ያደረገ እንዲህ ዓይነት ዕውቀትና ችሎታ ስለነበራቸው ነው የሚሉት አክሊሉ ሀብቴ “መመረጥ”ን በተመለከተ ውዝግብ መነሳት አልነበረበትም ብለው ምክንያታቸውን በሚከተለው መልኩ አኑረዋል።
“ብዙዎች ‘መመረጥ’ የሚለውን ቃል ለመቀበል ይቸግራቸዋል። ግን በዘመኑ የነበሩት ከባድና አንቱ፣ አንቱ የሚባሉ ቱባ ቱባ እንደ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ያሉ መኳንንት፣ በአመራር ጥበብ የበለፀጉና በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነትና ከበሬታ የነበራቸው፣ በወጣት ተፈሪ ተታልለው ወይም በሌላ ዘዴ በተፈጠረ የተፈሪ ኃይል ተፅዕኖ ተሸንፈው፣ ተፈሪን መረጡ ማለት የነበሩትን መኳንንት ብልህነትና ብርታት አለማወቅ ወይም መናቅ ይመስላል። በሌላ መንገድ የወጣት ተፈሪ መሪነት፣ ብልሀነትና አግባቢነት የተመሠከረበት አጋጣሚ መሆኑን ያመለክታል።”
ለአፄ ኃይለሥላሴ “ዘመናዊ” ትምህርት አፍቃሪነት፣ በተለያዩ ጊዜያት የአውሮፓ አገራትን መጎብኛታቸው፣ የአድዋ ድል በማይጨው ሽንፈት ጥላሸት እንዲያጠላበት ምክንያት የሆነው በቴክኖሎጂና በትምህርት ወደኋላ በመቅረታችን ነው ብለው በማመናቸውና በመሳሰሉት ምክንያቶች ነው የሚሉት አክሊሉ ሀብቴ ንጉሠ ነገሥቱ ትምህርትን ለማሳደግ ከነበራቸው ጉጉት የተነሳ የትምህርትና ሥነ ጥበብ ሚኒስትርነትን ኃላፊነት ለራሳቸው አድርገው እንደነበርም ያነሳሉ።
ልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን 1920 በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ተገኝተው ዩኒቨርሲቲ የማቋቋም ምኞት እንዳላቸው የመጀመሪያውን ጥቆማ ከሰጡ አንስቶ ሕልማቸውን እውን ማድረጊያ ዘመኑ እየራቀባቸው ቢሔድም፣ ጉዳዩን በተለያዩ ጊዜያትና መድረኮች ደጋግመው አንስተውታል። በ1924 አሜሪካውያን በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ እንዲያቋቁሙ አፄ ኃይለሥላሴ ጥያቄ ቢያቀርቡም በፋሽስት ጣሊያን ወረራ ምክንያት ድርድሩ ፈቀቅ አላለም።
ጣሊያን በተባረረ ማግስት ሐምሌ 16 ቀን 1935 ኮተቤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ሲመርቁ ባደረጉት ንግገር “ይህ ትምህርት ቤት በኢትዮጵያ ለማቆም ከምንመኘው መጨረሻው አይደለም። ወደፊት በመዘጋጀት ለተሰናዱት ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲ የእናንተ በትምህርታችሁ መትጋት የሚያበረታታ ይሆናል” ብለው ነበር። የአቡነ ጴጥሮስን መታሰቢያ ሐውልት (ሐምሌ 16 ቀን 1938) ሲመርቁም “በቅርብ ጊዜ በአዲስ አበባ ታላቅ ዩኒቨርሲቲ እንዲከፈት ተዘጋጅቷል” ብለዋል።
ሐምሌ 16 ቀን 1941 የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ለንጉሡ ሐውልት የማሠራት ዕቅድ እንዳለው በከንቲባው በኩል ለቀረበው ጥያቄ ከሦስት ወር በኋላ ጥቅምት 23 ቀን 1942 አፄ ኃይለሥላሴ የሰጡት መልስ፣ ዕቅዳቸውን እውን የሚያደርጉበት ዕድል መፈጠሩን አመለከተ። “ሕዝቡ ባዋጣው ገንዘብ ለራሱና መጭው ትውልድ የሚጠቀምበት ዩኒቨርሲቲ እንዲሠራበት መፍቀዳቸውንና መወሰናቸውን አስታወቁ። ከዚያም አልፎ ዩኒቨርሲቲው በራስ ተሰማ ሠፈር ባለው ባዶ ቦታ ላይ እንዲሆን በማሰብና ንግግር በማድረግ የዩኒቨርሲቲውን ሕንፃ መሠረት አኖሩ።”
ንጉሠ ነገሥቱ ብቻቸውን ለፍተውበት አልሳካ ያለው ዩኒቨርሲቲ የማቋቋም ምኞት፣ ሕዝቡ የሚሳተፍበትና ባለድርሻ የሚሆንበት ዕድል ከተፈጠረ በኋላም ቢሆን ተስፋና ጅማሬው እንደታሰበው የሚፋጠን አልሆነም። “ለሐውልት በተያዘ በጀትና ዕቅድ ዩኒቨርሲቲ ይሠራ በመባሉ፣ የዩኒቨርሲቲ የትምህርት ፕሮግራም ሳይጠና የግንባታ ዲዛይን በመሠራቱ፣ የቦታ ድልደላና አጥር ከተሠራ በኋላ ቦታው ይጠባል” በተባሉ ምክንያቶች ነበር የዚያም ዘመኑ ዕቅድ ሊሳካ እንዳልቻለ ግልጽ የሆነው።
ዩኒቨርሲቲ መገንቢያ አማራጭ ቦታ ለማግኘት በአገር ውስጥና በውጭ አገር ባለሙያዎች ፍለጋና ጥረቱ ቀጠለ። በኢትዮጵያውያን የሚመራው ኮሚቴ ሆለታ፣ ጄነራል ዊንጌት ትመህርት ቤት አካባቢ፣ ልዕልት ፀሐይ ሆስፒታል ዙሪያ፣ ከአሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ በታች፣ ኮተቤ፣ ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ ሠፈር፣ ቦሌ… በአማራጭነት ቢያቀርብም በብዙ ችግሮንና የተለያዩ ምክንያቶች አንዱን ቦታ መርጦ ዕቅዱን እውን ለማድረግ ፈተናው በዛ። በመጨረሻም ንጉሠ ነገሥቱ የ6 ኪሎውን ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ግቢ በልግስና ከሰጡ በኋላ ዕቅዱ እውን መሆን ቻለ።
በ1920 ተወጥኖ ከ30 ዓመት በኋላ፣ ታኅሣሥ 9 ቀን 1954 ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የኒቨርሲቲ ከመቋቋሙ በፊት፣ በዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የተማሪ ተቃውሞ ማቆጥቆጥ በጀመረበት ዘመን፣ ልፋታቸው እያስከተለ ስላለው ውጤት ምን እንደተሰማቸው ለተጠየቁት አፄ ኃይለሥላሴ የሰጡት መልስ አስደማሚ ነበር። “በትምህርት ላይ አምርረን ያተኮርነው፣ የገፋንበትም፣ ለጠቅላላ ማኅበረሰብና ለአገራችን የሚያመነጣውን ጥቅም በማሰብና በመቆርቆር ስላመንበት ነው እንጂ ተማሪዎች እንደሚያነሱት ያለ ችግር ሊያመጣ መቻሉን አጥተነው፣ ዘንግተነውም አይደለም።” የአክሊሉ ሀብቴ (ዶ/ር) መጽሐፍ እንዲህ ዓይነት አስገራሚና አነጋጋሪ መረጃዎች የታጨቁበት ጥራዝ ነው።

ብርሃኑ ሰሙ በተለያዩ የሕትመት ብዙኃን መገናኛወች ለሁለት ዐሥርት ዓመታት የሠሩ ሲሆን የመጻሐፍትም ደራሲም ናቸዉ። በኢሜይል አድራሻቸዉ ethmolla2013@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 9 ጥር 4 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here