የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ምርጫ አስፈጻሚዎችን በመቅጠር የምርጫ ሥራን እያስፈጸመ እንደሆነ ይታወቃል። በዚህ ሂደት ውስጥ ካጋጠሙት ችግሮች መካከል አንዱ የሆነው የምርጫ አስፈጻሚዎች ክፍያ መዘግየት ነው። በተለያየ ወቅት የተለያዩ ክፍያዎች ሲደረጉ ቢቆዩም ከአስፈጻሚዎች ቅሬታ ሲያስነሳ የነበረ ጉዳይ መሆኑ አልቀረም።
የክፍያዎቹ መዘግየት ችግር የነበረው ሥልጠና ከወሰዱ አስፈጻሚዎች መካከል ሥራ ያልጀመሩ በመኖራቸው እንዲሁም ሥልጠና ሳይወስዱ ሥራ ላይ የተሰማሩ በመገኘታቸው፣ ትክክለኛው ሂደት ተከትለው ወደሥራ የተሰማሩ አስፈጻሚዎችን መለየት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው። እነዚህን ልዩነቶች የታዩባቸው ቦታዎችን በመለየት የኮንትራት ማጣራት ማድረግ ጊዜ ፈጅቷል። በዚህ ሳምንት ብቻ ይህንን ችግር ለመፍታት በተደረገው ጥረት ለ67 ሺሕ 405 የምርጫ አስፈጻሚዎች ክፍያ መፈጸም መቻሉን ቦርዱ አስታውቋል።
አስፈጻሚዎች ክፍያ የተፈጸመላቸው ሲሆን ክፍያ ባልተፈጸመባቸው ክልሎች እና በከፊል ክፍያ በተፈጸመባቸው ቦታዎች የሚገኙ አስፈጻሚዎችን ክፍያ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት እንደሚጠናቅቅ ገልፀው በሂደቱ ለተፈጠረው መጉላላት አስፈጻሚዎችን ቦርዱ ይቅርታ ጠይቋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 131 ሚያዚያ 30 2013



