የምርጫ 2013 ደኅንነትና ሰላማዊነት

0
709

ኢትዮጵያ ስድስተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ በርካታ የምርጫ ቅድመ ዝግጅቶችን ስታከናወን ቆይታ አሁን ላይ የምርጫው ቀን እየተቃረበ በምርጫ ዋዜማ ላይ ትገኛለች። ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚካሄደው የፊታችን ግንቦት 28/2013 በአገር አቀፍ ደረጃ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በድሬድዋ ከተማ አስተዳደር ሰኔ 5 እና ሰኔ 6/2013 እንደሚካሄድ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተገለጸው የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ያስረዳል።

ኢትዮጵያ ስድስተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ እንደመገኘቷ እና የምርጫ ጊዜው እየተቃረበ በመምጣቱ የምርጫ ሰላማዊነትና ደህንነት ትኩረት የሚፈልገ ጉዳይ መሆኑ አይቀርም። በምርጫ ወቅት የሰላምና ደህንነት ጉዳይ በቅድመ ምርጫ እና በድህረ ምርጫ ትኩረት የሚሻና የምርጫውን ውጤታማነት የሚወስን እንደሆነ ይገለጻል።

የምርጫ ደህንነት እና ሰላም ለምርጫ ውጤታማነት ጉልህ ሚና አላቸው ከተባለ፣ ምርጫ ሲታሰብ ደህንነቱ የተጠበቀና ሰላማዊ መሆኑ ለምርጫው ፍትሐዊነት፣ ተአማኒነት፣ አሳታፊነትና በአጠቃላይ የምርጫን አላማ ለማሳካት ትልቁን ቦታ መያዙ አይቀርም። ምክንያቱም ምርጫ ደህንነቱ የተጠበቀና ሰላማዊ ካልሆነ የዲሞክራሲ መስፈርት ያሟላ ምርጫ መሆን አይችልም።

የምርጫ ደህንነትና ሰላም በምርጫ ወቅት ሲታሰብ አንድን ምርጫ ደህንነቱ የተጠበቀና ሰላማዊ እንዳይሆን የሚደርጉት ምክንያች መኖራቸው አይቀርም። የምርጫን ደህንነትና ሰላማዊነት ከሚያስተጓጉሉ ጉዳዮች መካከል አሁን ላይ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል በየጊዜው እየተባባሰ የመጣው የዜጎች ግድያና መፈናቀል እንዲሁም የምርጫውን መካሄዱን የማይደግፉ አካላት የሚፈጥሩት መሰናክል ሊሆን እንደሚችል በዘንድሮው ምርጫ ደህንነትና ሰላም ላይ ብሔራዊ የመግባበት ፕሮጀክት ነድፎ የሚሰራው ዓለም አቀፍ ‹ሪቫይቫል› አገልግሎት የተባለ ድርጅት ይገልጻል።

ዓለም አቀፍ ሪቫይቫል አገልገፍሎት ሚያዚያ 22/2013 በስካይ ላይት ሆቴል “ሁሉን አካታች፣ በእውቀት ላይ የተመሰረተ፣ ብሔራዊ የመግባባት ውይይት” በሚል ርዕስ በምርጫ ደህንነትና ሰላማዊነት ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት አድርጎ ነበር።
በውይይቱ ለ6ተኛ ጊዜ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደውን ምርጫ ታሳቢ በማድረግ ኢንተርናሽናል ሪቫይቫል አገልግሎት ከዲሞክራሲና ምርጫ ኢንስቲትዩት (IDEA) ኢንተር አፍሪካ ግሩፕና (IAG) የአውሮፓ ኅብረት(EU) ጋር በመተባበር የብሔራዊ መግባባት ፕሮጀክት ቀርፀው እንቅስቀሴ መጀመራቸውን አስታውቀዋል።

ሁሉን አካታች፣ በእውቀት ላይ የተመሰረተ፣ ብሔራዊ የመግባባት ውይይት – All Inclusive, Knowledge Based National Dialogue-(የዚህ ፕሮጀክት ዓላማ ሲሆን) የሀገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አቅጣጫ ላይ ተጽዕኖ በሚያደርጉ አከራካሪ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት እንዲኖር በስካይላይት ሆቴል (Skylight Hotel, Addis Ababa) መድረኩን ማመቻቸቱን ኢንተርናሽናል ሪቫይቫል ሚኒስትሪ (IRM) ዳይሬክተር ሪቨረንድ ዳንኤል ጣሰው አስታውቋል።

በውይይቱ ላይ የአገልግሎቱ ዳይሬክተር እንደገለጹት፣ ሁሉን አካታች የሆነ በእውቀትና ምርምር ላይ የተመሰረተ ብሔራዊ የመግባባት ውይይት ማካሄዳችን ከምርጫ በፊት ያሉና ሊኖሩ የሚችሉ መራርነትና አደገኛ ግጭቶችን ማስወገድ የሚያስችል ዝግጅት ማድረግ ይገባል ብለዋል። የኢንተር አፍሪካ ግሩፕ ዳይሬክተር (IAG) የዚህ ስብሰባም ዓላማ የፕሮግራማችንን ግብና እሴቶቹን ለሁሉም ባለድርሻ አካላት በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ማስተዋወቅ እና ይሄም አንድ መግባባት ላይ መድረስ የሚቻልባቸውን ሁኔታዎች ማመቻቸት ቀዳሚው ነው ተብሏል።

ተቋሙ “የሃሳቦች ግብዓት ለብሔራዊ መግባባት” በሚል መነሻ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በአንድ መድረክ በማወያየት በምርጫ ወቅት የሚገጥሙ የደህንነትና የሰላም ችግሮችን መሻገር የሚያስችሉ የመፍትሔ ሀሳቦች እንዲንሸራሸሩ አድረጓል። በዚህም ፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ወቅት ስጋት የሚሆኑ የደህንነትና የሰላም ችገሮችን በመለየት ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ እንዲንቀሰቀሱ ተጠቁሟል።

በውይይቱ ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች በተጨማሪ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሬ ሌንጮ(ዶ/ር) የተገኙ ሲሆን፣ ምርጫ ሰላማዊና ፍትሐዊ ካልሆነ የምርጫ መስፈርት ያሟላ ምርጫ ሊባል እንደማይችል በመግለጽ፣ ምርጫ የግድ ደህንነቱና ሰላማዊነቱ የተጠበቀ መሆን አለበት ብለዋል።

የምርጫ ሰላማዊነትና ደህንነት በቅድመ ምርጫና በድህረ ምርጫ ወቅት ሊረጋገጥ ይገባዋል የሚሉት ነገሬ፣ ምርጫ በሂደቱ ደህንነቱ የተጠበቀና ሰላማዊ ካልሆነ ውጤቱም ጥሩ ሊሆን አንደማይችል ጠቁመዋል። አክለውም ምርጫ ከዴሞክራሲያዊነት በተጨማሪ አሳታፊ መሆን መቻል እንዳለበት ነው የጠቆሙት። ምርጫ አሳታፊና ደህነነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ደግሞ የመጀመሪያ ቅድመ ሁኔታ ሰላም መሆን እንደሚገባቀው ነገሬ ይገልጻሉ። በምርጫ ወቅት ሊፈጠሩ የሚችሉ የደህንነት ችግሮችን ለማስቀረት ምርጫ ከሂደቱ ጀምሮ በስሜት ሳይሆን በእውቀትና በምክንያታዊነት ላይ የተመሰረተ ሂደት መከተል እንዳለበት ነው የጠቆሙት።

ለዚህም አገሪቱ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ መገንዘብና ወቅቱ የሚፈልገውን ጥንቃቄ የተሞላበት የምርጫ ሂደትን መከተል ለምርጫው ውጤት መሳካት ትልቁን ሚና እንደሚጫወት ነው የተጠቆመው። ኢትዮጵያ የፊታችን ግንቦት 28/2013 የምታካሂደው ምርጫ በውስጥም በውጭም በገጠሟት ቸግሮች ተከባ የምታካሂደው መሆኑን ሁሉም በሂደቱ የሚሳተፉ ባለድርሻ አካላት ሊገነዘቡ እንደሚገባ ተመላክቷል።

በመንግሥት መጥቷል የተባለው ለውጥ “በጠንካራ መሰረት ላይ የተመሰረተ አይደለም” ያሉት ነገሬ፣ ይህኑ ተከትሎ በመርጫው ላይ ሊገጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ከወዲሁ ማሰብና መዘጋጀት ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል። አክለውም ምርጫ ከሂደቱ የሚገኝ ውጤት በመሆኑ መራጩ ህዝብ በስሜት ሳይሆን ማግኘት የሚገባውን እውቀት አግኝቶች እንዲመርጥ ማድረግ ይገባል ብለዋል። ለዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚጠበቅባቸውን ሚና ከወዲሁ መወጣት ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ሊቀመንበር(ዶ/ር) አብዱልቃድር አደም፣ በበኩላቸው ምርጫ 2013 በአንድ በኩል ተስፋ፣ በአንድ በኩል ስጋት ያጠላበት ምርጫ መሆኑን ጠቁመዋል። ለዚህም ምክንያቱ አገሪቱ ውስጥ ያጋጠመው የጸጥታ ችግር አንዱ እንደሆነ ጠቁመዋል። ይሁን እንጂ ምርጫውን በጥንቃቄ ማለፍ ያስፈልጋል ባይ ናቸው።

ነገሬ (ዶ/ር) በበኩላቸው ምርጫ ለስልጣን ሳይሆን ለሕዝብ አገልግሎት የሚደረግ ፉክክር ነው ብለውታል። “ሕዝብ በሌለበትና ሰላም በሌለበት ስልጣን የሚባል ነገር የለም” ያሉት ነገሬ በምርጫ ወቅትም ቢሆን ለሰላም ቅድሚያ መስጠት እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል። ሁሉም የአገር ባለቤት መሆኑን በመገንዘብ ምርጫው ሰላማዊ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ነፃና አሳታፊ እንዲሆን ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በውይይቱ ላይ “ደህንነት በምርጫ ወቅት በኢትዮጵያ” የሚል ሥያሜ የተሰጠው በ2013 ምርጫ ደህንነት ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ጸሑፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበት ነበር። በጥናቱ ላይ ከቀረቡት ሀሳቦች መካከል በምርጫ ወቅት በማኅበረሰብ ዘንድ የታፈኑ ድምጾች ሊፈነዱ እንደሚችሉ ይጠቁሟል። በዚህም በማኀበረሰብ ዘንድ ክፍፍል ሊፈጥር እንደሚችል ጥናቱ ያመላክታል።

አሁን ላይ በአገሪቱ በተለያዩ አከባቢዎች የተፈጠሩ የጸጥታ ችሮችን በየደረጃው የለየው ጥናቱ፣ በተለያየ ደረጃ የሚፈጠሩ የጸጥታ ችሮች በምርጫው ላይ ጥላ እንዳጠሉ ይገልጻል። ጥናቱ በቅድመ ምርጫና በድህረ ምርጫ ወቅት ሊገጥሙ የሚችሉ ትንበያዎችን አስቀምጧል። በቅድመ ምርጫ ወቅት የጸጥታ ችግር የሚፈጥረው የምርጫ ሂደት መሰናክል ሲሆን በድህረ ምርጫ ወቅት ደግሞ ከምርጫ ውጤት ጋር ተያይዞ ችግሮች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ይተነብያል።

በውይይቱ የተሳተፉት ሌላኛው ፖለቲከኛ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) ዋና ጽኃፊ አበበ አካሉ ምርጫ 2013 በተንቀለቀለ እሳት ውስጥ የሚካሄድ ምርጫ ነው ይላሉ። አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ በቅድመ ምርጫ ብቻ ሳይሆን በድህረ ምርጫ ወቅት ሊገጥሙ የሚችሉ ችግሮችን አስቦ መስራት ይገባል ብለዋል። በተለያዩ ምክንያቶች ከምርጫው የተገለሉ የፖቲካ ፓርቲ ደጋፊዎችና ሌሎችም የሚፈጥሩትን ችግር ከወዲሁ ማሰብ እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።
ከምንም በላይ ማንም ይሁን ማንም አሁን አገሪቱ የገጠማትን ችግር ለማለፍ ከምርጫ በላይ አገር ማስቀደም ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበት አበበ አሳስበዋል። ሁሉም ነገር ሊኖር የሚችለው አገር ስትኖር መሆኑንም ጠቁመዋል።

የምርጫ ደህንነትና ሰላማዊነት ላይ ችግር ሊፈጠሩ የሚችሉ ምክንያችን በመለየት የሲቪክ ማኅበራት፣ የማህበረሰብ አንቂዎች፣ ሚዲያዎችና ፓርቲዎች እጅግ ጥንቃቄ የተሞላበት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንሚገባ አበበ እንደመፍትሔ ሀሳብ አቅርበዋል።
በውይይቱ ላይ የቀረበው ጥናት ላይ የተገለጸው የመፍትሔ ሀሳብ የሚዲያ አካላት፣ ሰላም ሚኒቴር፣ መከላከያ ሚኒስቴር፣ የፌደራልና የክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች ኃላፊነታቸውን በትኩረት ሊወጡ እንደሚገባና ለምርጫው ልዩ ትኩረት አድርገው ቢሰሩ የተገመቱ ችግሮችን ማስቀረት እንደሚቻል ይጠቁማል።


ቅጽ 3 ቁጥር 131 ሚያዚያ 30 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here