የእርዳታ ምግብ የጫኑ 500 ተሽከርካሪዎች ትግራይ መድረሳቸው ተገለጸ

0
857

አስቸኳይ የእርዳታ ምግብ የጫኑ 500 ተሽከርካሪዎች ትግራይ መድረሳቸውን የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስታወቀ። የእርዳታ ምግቡን የጫኑ ተሽከርካሪዎቹ ከሱዳን ነው ወደ ትግራይ የገቡት።
በክልሉ በተደረገው ውጊያ ለተጎዱ 2.1 ሚሊዬን ዜጎች የምግብ እርዳታዎችን ለማድረስ በማሰብ እየሰራ መሆኑን ያስታወቀው የዓለም ምግብ ፕሮግራም ፣ ሌሎች ተጨማሪ 500 የእርዳታ ምግቦችን የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ክልሉ ለመግባት በጉዞ ላይ ይገኛሉ ብሏል።
ድንበር ዘለሉን ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ላሳየው ትብብር የሱዳን መንግስትን ያመሰገነው የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ የሱዳን ማስተባበሪያ እስካሁን ከ20 ሺ ሜትሪክ ቶን በላይ ምግብ ለማቅረብ መቻሉንና ተጨማሪ 25 ሺ ሜትሪክ ቶን የእርዳታ ምግብ በመጓጓዝ ላይ መሆኑን አስታውቋል።
4.5 ሚሊዮን የሚደርሱ የትግራይ ክልል ነዋሪዎችን ጨምሮ ከ16 ሚሊዮን በላይ ሕዝቦቿ የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ኢትዮጵያ ፣ የተባበሩት መንግስታት 65 ሚሊዮን ዶላር መልቀቁም ተገልጿል።
ይሁን እንጂ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ተጨማሪ ፈንድ እና ሰላማዊ እና ያልተገደበ ተደራሽነት እንደሚያስፈልጋቸውም ነው የዓለም ምግብ ፕሮግራም ያስታወቀው።
የኢትዮጵያ መንግስት በቅርቡ በሰጠው መግለጫ ፣ ከዚህ በኋላ ከትግራይ ክልል አጠቃላይ የቆዳ ስፋት ውስጥ በ14 በመቶው ብቻ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
ቀሪው 86 በመቶ የዓለም ምግብ ፕሮግራምን ጨምሮ በሌሎች ዓለም አቀፍ እርዳታ ሰጭ ተቋማት እንደሚሸፈን ብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ በወቅቱ ገልጸዋል።
እስካሁን በክልሉ በመደረግ ላይ ካለው ሰብዓዊ ድጋፍ 70 በመቶ የሚሆነው በኢትዮጵያ መንግስት የሚሸፈን ነው መባሉ የሚታወስ ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 132 ግንቦት 7 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here