የአዕምሮ ህሙማን ወር “የአዕምሮ ህመምን ታክሞ ውጤታማ ኑሮ መቀጠል ይቻላል”

0
1039

አዲስ አበባ ተወልደው ልጅነታቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ አሳልፈዋል። ገና ተማሪ እያሉ ወደ አውሮፓ ተጉዘው 4 አመታትን እየተማሩ አሳልፈዋል። የአውሮፓ ቆይታቸው ከለመዱት የአገራቸው ኑሮና አስተሳሰብ በጣም ስለተራራቀባቸውና ከወዳጅ ዘመድ ተነጥለው ስለቆዩ ድንገት የስሜት መዋዠቅ በሽታ ገጥሟቸዋል። ህክምና ጤንነታቸውን ሊመልስላቸው ባለመቻሉ ወደናፈቋት አገራቸው ተመልሰው ትምህርታቸውን በመከታተል እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ድረስ በከፍተኛ ውጤት አጠናቀዋል። የሥራ አለምን ባንክ በመስራት ጀምረው በተለያዩ ግብረሰናይ ተቋማት በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች አገራቸውን አገልግለዋል። የግል ታሪካቸውን መሰረት አድርገው የአዕምሮ ህሙማንን ለመርዳት ስራቸውን ትተው ግብረሰናይ ተቋም መስርተው በፕሬዝዳንትነት እያስተዳደሩት ይገኛሉ። እሌኒ ምስጋናው ይባላሉ። የአእምሮ ጤና ወር በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ‹‹የአእምሮ ጤና ፍትሐዊ ባልሆነ ዓለም›› በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ይገኛል። ይህንንም በማስመልከት የአዲስ ማለዳው ቢኒያም ዓሊ ከእሌኒ ምስጋናው ጋር ቆይታ አድርጓል።

ስለአስተዳደግዎ ትንሽ ቢነግሩን?
እሌኒ ምስጋናው በላቸው እባላለሁ።የአዕምሮ ህክምና አገልግሎት ተጠቃሚዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ነኝ። የአዕምሮ ህመም ታማሚ ነኝ። ከአዕምሮ ህመም ጋር መኖር ከጀመርኩ ረጅም ጊዜ ሆኖኛል። ከ14 አመቴ ጀምሮ ነው የ‹ባይ ፖላር ዲስኦርደር› ወይም የስሜት መዋዠቅ በሽታ ያጠቃኝ። በአጋጣሚ አጎቴ ውጭ አገር ነበር የሚኖረው፤ ቤልጀም እሱ ጋር ለትምህርት ሄጄ ከቤተሰብ ከአገር በመራቄ ብዙ ችግር ገጥሞኝ ነበር። በዛ እድሜዬ ከማውቃቸው ተነጥዬ በመሄዴ ‹ካልቸራል ሾክ› ወይም ባህላዊ ድንጋጤ ስለተፈጠረብኝ ተቸግሬ ነበር።

እኔ ሳድግ በጠንካራ ክርስቲያናዊ ኃይማኖት በመታነጽ ስላደግኩ እዛ ስሄድ ብዙ ነገሮች ተደበላልቀውብኝ ነበር። ኃይማኖት የሌላቸው ማሕበረሰቦች ውስጥ ሳልዘጋጅ በቀጥታ በመቀላቀሌ ድንጋጤዬ ከፍተኛ ነበር። ለመላመድ የተወሰነ ያህል ሞክሬ አልቻልኩም። ለ4 አመት ከግማሽ ያህል ጥሬ ሳይሳካልኝ ቀረሁ። ከዛ ጊዜ በኋላ ከፍተኛ የአዕምሮ መቃወስ አጋጥሞኝ ለ3 ወር ያህል ሆስፒታል ተኝቼ ነበር። በኋላ ላይ ግን ወደ አገሯ ብትመለስ ይሻላታል ተብዬ እንድመለስ ተወሰነ። ወዲያው እናቴ እዛው መጥታ ይዛኝ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰች።
ኢትዮጵያ ከተመለስኩ በኋላ ትምህርቴን ለአንድ አመት ካቋረጥኩኝ በኋላ ሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት ገባሁ። ኹለተኛ ደረጃ ትምህርቴን እዛው ጨርሼ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ለ4 ዓመት ተምሬ የመጀመሪያ ዲግሪዬን አገኘሁ። ከዛ በኋላ ለ7 አመታት የመንግስት ባንክ በሆነው ንግድ ባንክ አንዋር መስጊድ ቅርንጫፍ ውስጥ አገልግያለሁ። ቀጥሎ በዋናው መስሪያ ቤት አለም አቀፍ የባንኪንግ ክፍል ውስጥ የእቅድ ባለሙያ ሆኜ ስሰራ ነበር። እድገት አግኝቼ ማርኬቲንግ ኦፊሰር ሆኜ፣ ፐሮዳክት ዴቨሎፕመንት ዲቪዥን ውስጥ ተዘዋውሬ ስሰራ ቆይቻለሁ።

ውስጤ የሚያተኩረው ከገንዘብ ይልቅ ማሕበረሰቡ ጋር ስለነበር የምወደውን፣ ሰው የማገልገል ባህሪዬን ለማዳበር ማሰብ ጀመርኩ። ያለሁበት የስራ ዘርፍ ከኔ ባህሪ ጋር የማይሄድ መሆኑን ዘግይቼም ቢሆን ተረዳሁ። በዚህ ምክንያት እንደፍላጎቴ መንግስት እንዲያስተምረኝ በባንኩ በኩል ሞከርኩኝ። በመስሪያ ቤቱ ውስጥ በአገልግሎት ዘመን የሚበልጡኝ ተመሳሳይ ፍላጎት የነበራቸው ስለነበሩ እድሉን ሳላገኝ ቀርቻለሁ። በዚህ ምክንያት ስራዬን ሙሉ በሙሉ ለቅቄ በቀኑ የትምህርት ክፍለ ጊዜ የሶሺዮሎጂ ዲፓርትመንትን ተቀላቅዬ ተማርኩኝ።
ለ2 አመት ያህል ከተማርኩ በኋላ በጥሩ ውጤት ትምህርቴን አጠናቀኩ። መመረቂያ ፅሁፌን የሰራሁት መስማት በተሳናቸው ዙሪያ ሲሆን፣ ማሕበራዊ ኑሯቸውና ሰው ስለእነሱ ያለው አመለካከት በአዲስ አበባ ምን እንደሚመስል ያሳየሁበት ነበር። ጥሩ ውጤት ያገኘሁበት ስለነበር በላምበርት አካዳሚክ ፐብሊሸሮች ታትሞ ለንባብ ቀርቧል። ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ ‹ሴፍ ዘ ችልድረን› ወደተባለ አንድ ለትርፍ ያልተቋቋመ ግብረሰናይ ድርጅት ውስጥ በ1ሺህ ዶላር ተቀጥሬ ገባሁ። ለአንድ አመት ያህል በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ካገለገልኩ በኋላ ኮንትራቴ ሲያልቅ ስራውን ለቅቄያለሁ።

የተወሰነ ጊዜ ስራ ፍለጋ ላይ ከቆየሁ በኋላ አገር በቀል ግብረሰናይ ድርጅት ውስጥ ለመግባት ችያለሁ። AFSR የሚባል ድርጅት ውስጥ የማሕበራዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ሆኜ አገልግያለሁ። ከዛ በኋላ ተመሳሳይ ተቋም ውስጥ ገብቼ ሰርቻለሁ። ይህኛው ድርጅት ሴቶችን ለማብቃት የሚሰራ ስለነበር የፕሮጀክት አስተባባሪ ሆኜ ለ2 አመት ያህል ውጤታማ ስራ ሰርቻለሁ። ቀጥዬ International Rescue committee ውስጥ ገብቼ ለ3 አመት ያህል በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ላይ ስሰራ ቆየሁ። በኋላ ላይ የአዕምሮ ጤና ጉዳይ ልቤ ውስጥ የነበረና ሁሌም የሚያሳስበኝ ጉዳይ ስለነበር፣ እንዲሁም ከእግዚአብሄር የተሰጠኝ ተልዕኮ አድርጌ እወስደው ስለነበር ሙሉ ጊዜዬን መስጠት እንዳለብኝ ወሰንኩ። የነበርኩበትን ስራዬን ለቅቄ ከመሰል ጓደኞቼ ጋር ሆነን አሁን በፕሬዝደንትነት የምመራውን ድርጅት መስርተናል። የአዕምሮ ህክምና አገልግሎት ተጠቃሚዎች ማሕበርን አሁን በሙሉ ጊዜዬ እያገለገልኩ እገኛለሁ።

ከአዕምሮ ህመም ጋር የተገናኘ ድርጅትን ያቋቋሙበት ምክንያት ምንድን ነው?
ከግሌ ምክንያት ሌላ ወደዚህ ዘርፍ እንድገባ ያደረገኝ አሜሪካ አገር እህቴን ልጠይቅ ለ3 ወር ሄጄ ያስተዋልኩት ነገር ነው። bipolar disorder የተባለ በዚህ ችግር የተጠቁን ያሰባሰበ የመረዳጃ ማሕበር ውስጥ ገብቼ ነበር። በየሳምንቱ እየተገናኘን የምናካሂደው ስብሰባ ነበር። በህመሙ የተጠቁ ሰዎች እርስ በርስ የሚደጋገፉበት መድረክ ነው። ያንን የመደጋገፍ ጥበብ በማየቴ እጅግ ተደንቄ ነው ወደእዚህ የመጣሁት። ይህ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢጀመር ትልቅ ጥቅም ሊሰጥ ይችላል የሚል ከፍተኛ እምነት አደረብኝ። በግሌ ከደረሰብኝ ህመም በተጨማሪ ይህ አጋጣሚ ከማውቃቸው ወዳጆቼ ጋር ሆኜ ድርጅቱን እንድመሰርት አድርጎኛል። የአዕምሮ ክብካቤ የሚባል አንድ ግብረሰናይ ድርጅት ነበር፣ ሥራቸውን እንደኛ ላሉ አገልግሎት ሰጪዎች የማስተላለፍ እቅድ ስለነበራቸው ጥሩ አጋጣሚ ተፈጥሮልናል። የቦርዱ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር አታላይ በዘርፉ አንጋፋ ባለሙያ በመሆናቸውና የረጅም ጊዜ ትውውቅ ስላለን፣ እንዲሁም የአጠቃላይ ገባኤው አባል በመሆኔ በስብሰባ ወቅት ሀሳቡን ሳካፍላቸው ወደዱት። የእነሱም ፍላጎት መሆኑን ከገለጹ በኋላ ወደ ምዝገባው ነው የሄድነው። በዛ መንገድ ማህበሩ ተመስርቶ ወደ ስራ ሊገባ ችሏል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ስለአዕምሮ ህሙማን ያለው አመለካከት ምን ይመስላል?
በጣም አሉታዊ አመለካከት መኖሩን እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል። የአዕምሮ ታማሚ ምንም አይነት ውጤታማ ኑሮ መኖር የማይችል ተደርጎ ይወሰዳል። እንደተረገመ፣ እግዚአብሔር እንደተቆጣውና ፊቱን እንዳዞረበት ተደርጎ ይታመናል። ህሙማኑ አደገኛ እንደሆኑና መጠንቀቅ እንደሚገባ አብዛኛው ሕብረተሰብ ያምናል። የእኛ ማኀበር ይህን የመሳሰሉ አሉታዊ አመለካከቶችን የማስተካከል ሥራን ይሰራል።

አሉታዊ አስተሳሰቡ በምን ምክንያት እንደመጣ ይታወቃል?
ይህን ለማወቅ ሰፊ ጥናት ይፈልጋል። በመስኩ ያጠኑ ቢመልሱት የተሻለ ነው ብዬ አምናለሁ። እንደ አንድ የአዕምሮ ታማሚ የምረዳው ነገር ቢኖር፣ ስለታማሚዎች ያለ አመለካከት መጠኑ ይለያይ እንጂ በዓለም ሁሉ ያለና ተመሳሳይ ነው። አንዳንድ አገራት በትምህርትና በተለያዩ መንገዶች ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በሰፊው በመሥራታቸው የተሻለ ለውጥ አላቸው። ሌሎች አሁን ሰፊ ሥራ እየሠሩ ስለሆነ የተወሰነ የተሻሻለ ነገር አለ። እኛ አገር ግን ምንጩ ምንድን ነው የሚለውን ለጊዜው በቂ ጥናት ስላላደረግን ትክክለኛውን ነገር አሁን መናገር ይከብዳል።

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአገራችን የአዕምሮ ህመም ያለባቸውን ዜጎች ወደ ውጭ አለማውጣት፣ የመደበቅና ወደ ህክምና ተቋማት ያለመውሰድ ነገሮች ይስተዋላሉ። አሁን እየተሻሻለ ነው ይላሉ?
አዎ ልዩነት አለ። እኔ እራሴ ታምሜ ከቤልጀም ከመጣሁ ወዲህ በጣም ውሱን ቦታዎች ብቻ ነበር አገልግሎቱ የሚሰጠው። አሁን ግን ጠቅላላ ሆስፒታሎች እራሳቸው እንደ አንድ ህክምና ክፍል የአዕምሮ ህክምና አገልግሎትን እየሰጡ ነው። አዲስ አበባ ላይ፣ ዋና ዋና ከተሞች ላይ፣ እንዲሁም በገጠሩም ደግሞ አገልግሎቱን በማስፋት የአዕምሮ ጤና አገልግሎትን ስፔሻሊስት ባልሆኑ ሐኪሞች እና ሌሎች ሐኪሞች የተወሰኑ ስልጠናዎችን ወስደው የአዕምሮ ጤና ሕክምና ላይ እነዚህን ሰዎች በማብቃት እስከ ወረዳ የወረደ ስርዓት ተዘርግቶ ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ነው።

የአዕምሮ ህሙማን በሕብረተሰቡ ውስጥ ከሚገጥሟቸው ችግሮች የተወሰኑትን ይጥቀሱልን?
አሉታዊ አመለካከቱ ለብዙ ተግዳሮቶች መንስዔ ይሆናል። የአዕምሮ ህመም ታማሚ ውጤታማ ኑሮ መኖር አይችልም የሚል አመለካከት በአብዛኛው ስላለ የትምህርት እድልንም የሥራ እድልንም ዉጤታማ ኖሮ ለመኖር የሚያስችል ግብዓቶችን የማቅረብ ተግዳሮት አለ። እኛ አገር አንድ የአዕምሮ ታማሚ ቤቱ ዝም ብሎ እንዲቀመጥ ነው አብዛኛው የሚጠብቀው። ግን አዕምሮ እንደማንኛውም አካል ክፍለ ህመም ሊታመም ይችላል። አዕምሮም የሰውነት ክፍል ነው እንደ ልብ እንደ እግር ይታመማል። በሚታመምበት ጊዜ ውጤታማ ህክምና አለው። የአዕምሮ ህመምን ታክሞ ውጤታማ ኑሮ መቀጠል ይቻላል ነው የማሕበራችን ዋና መልዕክት።

በግል ከተቋቋሙ ማኅበራት ውጭ ችግሩን ለመቅረፍ ከሕግ አኳያም ሆነ ከማስተማርና ቤሰቦችን ከመደገፍ አኳያ በመንግሥት የተደረጉ ሥራዎች አሉ?
አዎ፣ እንዳጋጣሚ ሆኖ አሁን የጤና አዋጅ እየተረቀቀ እና ሀሳብና አስተያየት እየተሰጠበት ይገኛል። የአዕምሮ ጤናም የተወሰኑ አንቀጾች አሉት። እዛ ላይ ዋና ዋና የአዕምሮ ህክምና አገልግሎቶችን የሕግ ማዓቀፍ ለመስጠት በጣም በትጋት እየተሠራ ነው የሚገኘው። የእኛም ማኅበር ረቂቁን አይተን ከአገልግሎቱ ተተቃሚዎች አንጻር ገንቢ አስተያየት ለመስጠት ሞክረናል ለሕዝብ ዉይይት ይፋ በሚያደርጉበት ጊዜ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ አስተያየት ለመስጠት እድል ያገኛሉ።

ሕብረተሰቡን ከማስተማር አኳያስ ምን ታስቧል?
ሕብረተሰቡን ከማስተማር አኳያ አንድ ማሳያ የሚሆነው፣ የአእምሮ ሕክምና አገልግሎት ተጠቃሚዎች ማኅበር እንዲመሰረት በመንግሥት ድጋፍ መደረጉ፣ ሕጋዊ በሆነ መንገድ እንድንንቀሳቀስ ቢሮም ተከራይተን እንደማንኛም ድርጅት በነጻነት አገልግሎቱን እንድንሰጥ እድሉ መመቻቸቱ እንደ ማሳያ ይሆናል። ሕብረተሰቡን ከማስተማርም አንጻር መንግሥት የአዕምሮ ጤና ላይ ለመሥራት ዝግጁ እንደሆነ ያለውን ቁርጠኝነት አሳይቶናል። ምክንያቱም በታሪካችን እንደምናየው ሕብረተሰባችን ባብዛኛው በታሪክ እና ምሳሌዎች ነው ብዙ ጊዜ ውጤታማ የባሕሪ ለውጥ የሚያመጣው። ስለዚህ ማሕበረሰቡ ጋር ያሉትን ታሪኮች ግልጽ ስናደርግ፣ ከአዕምሮ ህመም ጋር ውጤታማ ኑሮ የሚኖሩ ግለሰቦችን ታሪኮች ይፋ ስናደርግ መንግስትም የሚያግዘን አካሄድ እንዳለ እናስባለን።

ድርጅታችሁ አሁን ላይ ምን ሥራዎቸን እያከናወነ ነው?
ድርጅቱ ከተቋቋመ ገና ኹለት አመታት ነው የሆነው። አስካሁን በአብዛኛው ስንሠራ የቆየነው አስተዳደራዊ ሥራዎችን ነው። እራሳችንን የማስተዋወቅ፣ የጤናው ዘርፍ ውስጥ እራሳችንን የመፈለግ፣ ግንኙነቶችን መፍጠርና አብረን ልንሰራቸው የሚችሉ ባለ ድርሻ አካላትን የመለየት ሥራ እየሰራን ግብዓቶችንና ጥናቶችን ስናደርግ ቆይተናል። አሁን እነዚህን ሥራዎች ስለጨረስን በተሻለ አቅማና ዝግጁነት ቢሮም ተከራይተን ሙሉ በሙሉ ሥራችንን ጀምረናል።

ለወደፊት ለመስራት የምታቅዷቸው ሥራዎች ምን ላይ ያተኩራሉ?
ወደፊት ዓላማች ትልቅ ነው። ነገር ግን የገንዘብ አቅም የለንም፤ የገንዘብ ገቢያችን ከአባሎቻችን የምናገኘው ስለሆነ አቅማችን አናሳ ነው። ዓላማችንን ተረድቶ የሚደግፈን አካል ከተገኘ ወደ ፊት የአዕምሮ ህመም ውጤታማ ህክምና እንዳለውና በአገራችን በአዕምሮ ህመም ላይ ያለውን አመለካከት ሥር ነቀል ለውጦችን ለማምጣት ሥራ ጀምረናል። በዓለማችን ላይ በዋናነት የአዕምሮ ህመምን ለማስቀረት መከላከል ላይ እንሰራለን። ልጆች ላይ፣ ትምህርት ቤቶች ላይ ችግሩ ሳይከሰት ቅድመ መከላከል ላይ እንሰራለን። በተጨማሪም አኗኗር ላይ፣ የሕይወት ዘይቤና የሕይወት ፍልስፍናችንን ጭምር ጥሩ የሚባል አቅም እንዲኖረን የመከላከል ሥራ እንሰራለን።

በሌላ በኩል ደግሞ ከቀድመ መካላከል አልፎ የሚከሰቱ የአዕምሮ ህመሞችን እንዴት ማከምና ማዳን እንደሚቻል እንሰራለን። ከዚህ ባለፈም የአዕምሮ ህመምተኞችን ህመማቸውን ተረድቶ ማግኘት የሚገባቸውን አገልግሎት እንዴት ነው መሥጠት የሚቻለው የሚለውን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሥራት የመከታተል ሥራ እንሰራለን።

ይሄ ወር የአዕምሮ ህሙማን ወር እንደመባሉ እንዴት ነው የሚታሰበው?
ግንቦት ወር ለእኛ ለማኀበራችን ትልቅ ወር ነው። ምክንያቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ ግንቦት ወር የአእምሮ ህሙማን ጤና ላይ ሥራ እንድንሰራበት የተሰየመ ወር ነው። እንደ ማኅበር ግንቦት ወር ለእኛ ያለንን አቅም አጠራቅመን ሥራዎችን የምንሠራበት ወር ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የአዕምሮ ህሙማን ላይ ትኩረት ተደርጎ የሚሰራበት ወር ነው። እኛም በአገራችን ጥሩ አቅም ፈጥረን የግንዛቤ ሥራ የምንሠራበት ወር ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 132 ግንቦት 7 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here