በክልል ያሉ መምህራን ውዝፍ ክፍያቸው እስከ ግንቦት 15 ካልተከፈለ ስራ የማቆም አድማ ድረስ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስዱ አስታውቀዋል፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር ሚንስትር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ ባለፈው ሳምንት ያወጡትን ደብዳቤ ተከትሎ የገቢዎች እና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር እና የክልል ገቢዎች ቢሮ ህገወጥ ነው በማለታቸው እየተሰበሰበ እንደሚገኝ አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ ሰምታለች፡፡
ከሐምሌ 2011 ጀምሮ የቀረባቸውው ታስቦ እንዲከፈላቸው የተፈቀደው የደሞዝ ማስተካከያ እስከ አሁን ድረስ ለክልሎች አልተከፈልም፡፡ የክልል የትምህርት ቢሮዎች ከክልል አስተዳደር፣ የክልል ፋይናንስ ቢሮ እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የማስተካከያ ክፍያው የሚፈፀምበት አግባብ እንዲመቻች ባለፈው ሳምንት ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር) ጠይቀው ነበር፡፡ በአገራችን የተለያዩ ክልሎች የሚገኙ መምህራን የዘጠኝ ወር የተጠራቀመ የደሞዝ ጭማሪ (JEG) መንግስት ቃል በገባልን አልተከፈለንም ማለታቸው ይታወሳል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች አፋር፣ ሶማሌ፣ደቡብ በተወሰኑ አካባቢዎች የደመወዝ በወቅቱ አለመከፈል፣ የደረጃ ዕድገት ለተከታታይ አመታት አለመሰጠት ችግሮች በስፋት እየተነሱ ይገኛሉ።
አስቻለው ጌታነህ የባህርዳር ከተማ አስተዳደር የግል ትምህርት ቤቶች መምህራን ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ በበኩላቸው፣ እኛ እንደ ማህበር ለመምህራን ጥያቄዎች ምላሽ ለማሰጠት የቆምን ሲሆን ከላይ ያሉት ማህበር ማለትም በከተማ አስተዳደሩ ስር ያለው መምህራን ማህበር እና የአማራ ክልል መምህራን ማህበር ተገቢውን አገልግሎት በመስጠት እያገዙን አይደለም ብለዋል፡፡ ይልቁንም ቅሬታዎችን ይዘን በምንሄድበት ወቅት የማንገላታት እና ለመምህራን የሚሆን መተዳደሪያ መመሪያ እንደሌላቸው ይነግሩናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በክልሉ ያሉ መምህራን የቤት መስሪያ ቦታ፣ የጥቅማጥቅም አገልግሎቶች መከበር፤ የውዝፍ ክፍያዎች አለመከፈል፣ በሚያስተምሩበት የትምህርት ክፍለጊዜ ልክ ገቢ ያለማግኘት፣ በዝውውር ወደ ማይፈልጉበት ቦታ መመደብ እና የሴቶች የወሊድ ፍቃድ በተመለከተ ችግሮች እንዳሉባቸው አስቻለው ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል፡፡ አበራ ጣሰው የአዲስ አበባ የግል ትምህርት ቤቶች ማህበር ፕሬዘዳንት በበኩላቸው ማህበሩ መስራት የሚችለው አጠቃላይ የመምህራን ቅሬታ ሲሆን ለቤት መስሪያ የሚሆን ቦታ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጥያቄ አቅርበን ምላሽ እየጠበቅን ነው ብለዋል፡፡
አበራ አክለውም ክልሎች በተቀጠሩበት ትምህርት ቤት የሚስማሙበት ውል መሰረት ያደረገ የክፍያ እና የጥቅማ ጥቅም መከበር ይኖርበታል፡፡ ማህበሩም የግለሰቦች ቅሬታ ሲኖር ከትምህርት ቤቶቹ ጋር ያለውን ውል በማየት እንዲስማሙ መንገዶችን ያመቻቻል ብለዋል፡፡ ለዚህም ደግሞ በአዲስ አበባም ሆነ በክልል ያሉ መምህራን ቅሬታቸውን ቢያደርሱን ከጎናቸው እንሆናለን ብለዋል፡፡
መምህራን የሚገባቸውን ጥቅማ ጥቅም እና የደሞዝ ጭማሪ በተገቢው መንገድ እያገኙ አይደለም ሲል በአማራ ክልል የሚገኘው ለስድስት ዓመት በመምህርነት ያገለገለው ለአዲስ ማለዳ ቅሬታ ያቀረበው ስመኘው እማኙ ነው፡፡ ስመኘው በበለሳ ወረዳ ሀሙሲት ትምህርት ቤት የሚያስተምር ሲሆን በክልሎች ላይ የውዝፍ ክፍያ ካልተከፈላቸው ግለሰብ መካከል አንዱ ነው፡፡ ከዝውውር ጋር በተያያዘ የሚጠይቁት ጥያቄ በተገቢው መንገድ የሚያስተናግድ አካል እንደሌለ አክለው ገልጸዋል፡፡
የመንግስት ሰራተኞች የሰራንበትን የ9 ወር ባክ ፔይመንት መንግስት መጀመሪያ ይቅርታ ጠይቆ እንዲከፍለን እንፈልጋለን በማለት ቅሬታቸውን በአማራ ክልል ያሉ መምህራን ለአዲስ ማለዳ አቅርበዋል። መምህራን አሁን ያለውን የወቅቱን ሁኔታ መንግስትም ሆነ ከላይ እስከ ታች ያለው አመራር በትምህርቱ ዘርፍ ያለውን ጫናም ሆነ ያለውን የኑሮ ውድነት በሚገባ ያውቀዋል፤ ስለሆነም መንግስት ምንም አይነት ምክንያት ወይም ሰበባሰበብ ሳይፈጥር ብራችንን በቶሎ ይክፈል ካለበለዛ ግን ስራ የማቆም አድማ እስከማድረግ እንደርሳለን ማለታቸውን ሰምተናል።
በተጨማሪም፣ ከአማራ ክልል የደረሰ ቅሬታ ውስጥ መንግሥት የክልል መምህራንን ከአዲስ አባባ መምህራን ጋር በእኩል ለምን አያተናግድም፣ ውዝፍ ክፍያ ለአዲስ አባባ መምህራን ከፍሎ ለክልሎች መክፈል አለበተ፣የመምህራን ከካሳ ነፃ የሚሰጠው ቦታ የአሰራር ድክመትና ውስንነት አለበት፤ ወቅቱን ያገናዘበ የመምህራን የደመወዝና ሌሎች ጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎች በአፋጣኝ መልስ ይሰጣቸው፣ አዲስ አበባ መምህራን የሚከፈላቸው የቤት ክፍያ በክልል፣ ዞንና ወረዳዎች ላይ ለሚሰሩ መምህራንም መከፈል አለበት፤ የቲቶሪያል ትምህርት ክልሎች ላይም ክፍያ ሊኖረው ይገባል፤ የሚሉ ጥያቄዎችን ለአዲስማለዳ አቅርበዋል፡፡
አዲስ ማለዳ ጥያቄውን ለትምህርት ሚኒስቴር ያቀረበች ሲሆን፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቅሬታዎቹ እንደደረሱት አረጋግጧል፡፡ ለዚህም መፍትሄ ያለውን በሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር) በኩል የውዝፍ ክፍያ እንዲከፈል ወስኗል፡፡ በተጨማሪም ቅሬታዎችን በክልሉ ትምህርት ቢሮ መፍታት እንደሚችሉ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል፡፡
ቅጽ 3 ቁጥር 132 ግንቦት 7 2013


