በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ፣ ሊሙ ገሊላ እና ጊዳ አያና ወረዳ በነበረው የጸጥታ ችግር የተፈናቀሉ አርሶ አደሮችና ነጋዴዎች ከገጠር አከባቢዎች ያመረቱትን የሰብል እህል ጭነው ሲንቀሳቀሱ መዘረፋቸውን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ። በኹለቱ ወረዳዎች ከዚህ በፊት በነበረው የጸጥታ ችግር ቤት ንብረታቸውን ጥለው የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች፣ ትተውት የሸሹትን እህል ጭነው አሁን ላይ ወደሚኖሩበት አካባቢ በማጓጓዝ ላይ እያሉ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል መለዮ በለበሱ ግለሰቦች ተዘርፈናል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን ገልጸዋል። ከአርሶ አደሮች እህል ገዝተው ወደ ከተማ ለንግድ በማጓጓዝ ላይ ያሉ ነጋዴዎችም እስከ መኪናው ንብረታቸውን እንደተቀሙ ተናግረዋል።
ከገጠር ቀበሌዎች ወደ ከተማ በመጓጓዝ ላይ በነበሩ ተሽከርካሪዎች የጫኑትን እህል ጨምሮ በመንገድ ላይ የታገቱትና የተወሰደባቸው፣ የክልሉን ልዩ ሀይል መለዮ በለበሱ ግለሰቦች “ሕገወጥ እና የተዘረፈ ንብረት ነው” በሚል ሰበብ መሆኑን አርሶ አደሮቹና ነጋዴዎቹ ጠቁመዋል። የነጋዴዎችና የአርሶ አደሮችን እህል የጫኑ ተሽከርካሪዎች እህሉን ዘርፈዋል ብለው ካገቱት አካላት የብር ክፈሉ ጥያቄ እንደቀረበላቸውም ጠቁመዋል። ከታገቱት ተሽከርካሪዎች መካከል የአንዱ ሹፌር ብር ከፍሎ እህሉንም መኪናውንም መውሰድ እንደሚችል ተነግሮት ብር ቢከፍልም መኪናውና እህሉንም ማግኘት እንዳልቻለ አዲስ ማለዳ ሰምታለች። በዚህም ሹፌሮችና ነጋዴዎች ለህይዎታቸው በመስጋት ንብረታቸውን ከእነመኪናው ትተው ለመሸሽ እንደተገደዱ ጠቁመዋል።
በሕገወጥ ሰበብ የተወሰደን የነጋዴዎችና የአርሶ አደሮችን ንብርት ለማስመለስ በተለይ ነጋደዎች የንግድ ፈቃዳቸውንና የገዙበትን ማስረጃ ቢያቀርቡም ንብረታቸውን ማግኘት እንደልቻሉ ነው የገለጹት። ንብረታቸው ከተወሰደባቸው ነጋዴዎች አንደኛው ሕጋዊ ነጋዴ መሆኑን ማስረጃ እንዲያቀርብ ተጠይቆ ማስረጃውን በሚያቀርብበት ጊዜ ለእስር እንደተዳረገ ተመላክቷል። አርሶ አደሮቹ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ከሆነ በተፈጠረው ችግር ጥለውት የሸሹትን እህል ለመጫን የተገደዱት በአቅራቢያው ከሚገኙ አከባቢዎች በሚወጡ ግለሰቦች ንብረታቸው እየተወሰደ በመሆኑ ነው ብለዋል።
ከገጠር ቀበሌዎች በመጓጓዝ ላይ እያለ ተዘርፏል የተባለው እህል መጠን እስከ 800 ኩንታል እንደሚደርስ ተጠቁሟል። አርሶ አደሮች ያመረቱትን፣ ነጋዴዎች ከገበሬዎች የገዙትን እህል መነጠቃቸውንና ፍትሕ ማጣታቸውን በመግለጽ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ችግራቸውን ተረድቶ በአስቸኳይ ንብረታቸውን እንዲያስመልስላቸው ጥሪ አቅረብዋል። አዲስ ማለዳ ጉዳዩን ለኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ አስረድታ የቀረበውን ጥያቄ እንደሚያጣሩና ችግሩን እንደሚፈቱ ለጋዜጣዋ አረጋግጠዋል። ኮሚሽነሩ አክለውም የነጋዴዎችና አርሶ አደሮች ንብረት በማንኛውም አካል እየተነጠቀ ከሆነ እንደሚጣራ ገልጸው፣ ችግሩ የተፈጠረባቸውን ቦታዎች እንደሚከታተሏቸው ጠቁመዋል።
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ጊዳ አያና ወረዳ የታጠቀ ኃይል ባደረሰው ጥቃት ቤት ንብረታቸው የተቃጠለባቸው ዜጎች ከኹለት ሳምንት በላይ መንገድ በመዘጋቱ በረንዳ ላይ ወድቀው ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸውን ለአዲስ ማለዳ መዘገቧ የሚታወስ ነው። ይሁን እንጅ መንገዱ ለአንድ ቀን ከተከፈተ በኋላ በድጋሚ መዘጋቱን አዲስ ማለዳ ሰምታለች። በአከባቢው ሕገ ወጥ ተግባራት እየተባባሱ ቢመጡም ቸግሩን የሚያስቆም የመንግሥት የጸጥታ አካል አለመኖሩ ተጠቁሟል። መከላከያ ሚኒስቴር በአካባቢው ያለውን የጸጥታ ችግር አረጋግቻለሁ ቢልም፣ ኗሪዎች የመከላከያ ኃይል በቦታው ላይ እንደሌለ ጠቁመዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 132 ግንቦት 7 2013



