የብርቱ እናትነት ተምሳሌት – ዘሚ የኑስ

Views: 9

የእናቶችን እንባ የተመለከቱ፣ ድምጽ አልባውን የልጆችን ስቃይ ያዳመጡ ሴት ናቸው፣ ገበያ ወጥቶ ‹ልጄን የማስርበትን ሰንሰለት ስጡኝ› ብሎ የመግዛትን ሕመም ተረድተውታል፤ ይህም በተለይ ኦቲዝም ያለበት ልጅ ለወለዱ እናቶች ቁስል እንደሆነ ደጋግመው ይናገራሉ። የቆሙበትን ቦታ ተረድተው፣ ምንም ሆነ ምን ብቻ ለምክንያት መሆኑን ተቀብለው ነገሮችን በአግባቡ ለማስኬድ ከሚጥሩ ጥቂት ሰዎች መካከል ሊጠቀሱ ይችላሉ፤ የኒያ ፋውንዴሽን መሥራች፤ ዘሚ የኑስ።

በርካታ ኦቲዝም ያለባቸውን ልጆች ይዞና ወላጆቻቸውንም እያገዘ የሚገኘው ኒያ ፋውንዴሽን ከ18 ዓመት በፊት ገደማ ነበር ሕጋዊ እውቅናን አግኝቶ ሥራውን የጀመረው። ወጣቶች ላይ በመሥራት አሃዱ ያለውን እንቅስቃሴ በኦቲዝም ላይ አጠናክሮ ቀጥሎበታል። ብዙዎችም ፋውንዴሽኑን ስለዚህ ተግባሩ ያውቁታል።
ኒያ ፋውንዴሽን በአሁኑ ሰዓት ብርቱ የሚባል አቅም ባይኖረውም በአባላት ትንሽ መዋጮ፣ በጥቂቶች ድጋፍ፣ በብዙዎች ተስፋና በዘሚ ጽናት እርምጃው አልተገታም። በቅርቡም ከዓመታት በኋላ ሰፋ ያለ ማዕከል መገንባት የሚቻልበትን ስፍራ ተረክበው ግንባታው ሊጀመር ዋዜማው ላይ ተደርሷል። ይህ ጉዞ ስኬት ለይ ደርሶ፣ ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች ያለሃሳብ፣ ወላጆቻቸውም ያለጭንቀት እንዲኖሩ የሚያስችለው ማዕከል ተገንብቶ ማለቁን ማየት የዘሚ ሕልምና ምኞት ሆኗል፤ ወደዛም ለመገስገስ አሁንም እረፍት የላቸውም።

በአጋጣሚ አዲስ ማለዳ ለዚህ ቃለመጠይቅ ከዘሚ ጋር የተገናኘችው በተወለዱበት እለት ሰሞን ነው፤ ጥቅምት 6 መዳረሻ። እንደውም ‹‹የጥቅምት አበባ›› የሚለው ሙዚቃ ለእኔ ሳይሆን አይቀርም የተዜመው ይላሉ። እንደ እናትነት አንቱታን አስጥለው፣ በትህትና እና በጨዋታ አዋቂነት በተዋዛ አነጋገር፤ ከተጣበበ ጊዜያቸው ላይ ቀንሰው፣ ከሥራቸው ባሻገር ስላለ ማንነታቸው ከአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ጋር በነበራቸው ቆይታ አንስተዋል።

አዲስ ማለዳ፤ ዘሚ የኑስ እና ሳሞራ የኑስ…የስም መመሳሰል ነው ወይስ እህትና ወንድም ናችሁ?
ዘሚ የኑስ ሳሞራ የኑስ ሆነ እንጂ፣ እኔ ወንድሜ ነው ብዬ አላውቅም፤ ሰሞራ የኑስም ወንድሜ አይደለም። ነገር ግን ብዙ ሰዎች የሳሞራ የኑስ እህት ነው የሚያደርጉኝ። አንዳንዶቹ እንደውም በእርግጠኝነት ነው የሚናገሩት። ‹‹ወንድምሽ ነው?›› ወይም ‹‹እህቱ ነሽ?›› ብለው አይጠይቁኝም፤ ወንድምሽ አግንቼው ብለው ጨዋታ ይቀጥላሉ። ቁርጥ እርሱን ነው የምትመስይው የሚሉኝም አሉ። ግን የስም መመሳሰል ነው እንጂ እህቱ አይደለሁም፤ ወንድሜም አይደለም።

በዚሁ ከተነሳ አይቀር የዘሚ አስተዳደግና ልጅነት እንዴት ነበር?
ዘሚ የተወለደችው አዲስ አበባ ነው። እንደ አብዛኛው የአዲስ አበባ ህጻን ከመካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ሠርቶ አዳሪዎች የተወለደች ግን በጥሩ ያደገች፤ እናትና አባቷ ለአንድ ልጅ የሚገባውን ሁሉ እየሰጡ ያሳደጓት፣ ካቴድራል ትምህርት ቤት የተማረች፣ ደስተኛ እና ራሷን የሆነች ልጅ ናት።

ራሷን የሆነች ልጅ ስል ከልጅነት ጀምሮ ማንንም አልከተልም። አዳዲስ ፈጠራዎች ራሴ እፈጥራለሁ፣ መልበስ የምፈልገውን በራሴ ዲዛይን እለብሳለሁ። በዚህ አባቴ በጣም ነው ይደግፈኝ የነበረው፤ ራስሽን ሁኚ ይለኝ ነበር። እናቴ ግን በዚህ ትንሽ አትስማማም። በጣም ጠንካራ እናት ነበረችኝ። ለምሳሌ ልብስሽ አጠረ ብላ ትጥላለች። ግን ጥሩ ነው ያደኩት፤ ልጅነቴንም ተጠቅሜአለሁ። በዝናብ መደብደቡ፣ ጭቃ እና ጎርፍ ላይ መጫወት፣ ተልኬ ስወጣ ጠፍቼ ጓደኞች ጋር መሔድ፤ ያላሳለፍኩትና የማላውቅበት ከእኩዮቼ ጋር መጣላትና መደባደብን ነው።

ትምህርትስ እንዴት ነበር? ወጣትነት?
ጎበዝ ተማሪ ከሚባሉት አልነበርኩም (የደረጃ ተማሪ የሚባሉት) መካከለኛ ተማሪ ነኝ። ነገሮች ይገቡኛል ግን አይገቡኝምም። ከልጅነቴ የቀለም ሰው አልነበርኩም። ምንአልባት የተማርኩበት ዘይቤ ለእኔ የሚሆን አልነበረም። ወደ አርት አደላ ነበር፣ ለማህበራዊ ሳይንስ አደላለሁ። የቀለም ትምህርት ላይ ብዙ ትኩረት አልሰጥም፤ ትኩረት አለመስጠትም ሳይሆን ፍላጎቱ አልነበረኝም። ከዛ ግን በለጋ እድሜ ነው ወደ ውጪ የወጣሁት። እስከ 17 ዓመቴ አገሬ ቆይቼ ከዛ በኋላ ጣልያን አገር ሔድኩኝ፤ እስከ 22 ዓመቴ ድረስ ጣልያን ነበርኩ።

እዛ በተለይ መጀመሪያ ላይ በናፍቆትና በመወዛገብ የተሞላ ነበር፤ የእኛ ባህል ከሌላ ባህል ጋር የተጋጨብኝ ጊዜ ነው። ብቸኝነት የተሰማኝ፣ ናፍቆትም የነበረኝ ጊዜ ነው። እድሜዬ ገና ወጥቶ መማሪያ ነበር፤ እዚህ ቤተሰብ ላይ ቀብጠሸ አዛ ራስን ማስተዳደር የሚኖርብሽ ጊዜ ነው። ሆኖም ቆንጆ ጊዜ ነው፤ የጣልያን አገር ሕይወቴን በጣም የምወደው ነው።

ከዛ ወደ አሜሪካ አቀናሁ፤ እዛም ራሱን የቻለ የሥራና የልፋት ሌላ ሕይወት ነው። በእርግጥ ጣልያን አገር ሆኜም ከልጅነቴ ጀምሮ በጣም ሠራተኛና ኃላፊነት የምወስድ ሰው ነኝ። በ19 ዓመቴ በጣም ኃላፊነት ያለበት ቦታ ላይ ነበር የምሠራው። ብዙ ጉዳይ ትከሻዬ ላይ ነበር። አሜሪካም እንደዚሁ ሥራ ውስጥ ነበርኩ። ሕይወት ያስተማረኝ ራሴን ያስተማርኩ ሰው ነኝ። በዛ ደግሞ እጅግ ደስተኛ ነኝ።

ምክንያቱም ራሴን ሆኜ መኖር የምመርጥ ሰው ነኝ። ራሴን ሆኜ፣ ራሴን አስተምሬ፣ ራሴን አስተካክዬ፣ ራሴን አግዤ፣ ራሴን ይቅርታ ብዬ፣ በሁሉ ነገር እኔን ሆኜ መኖር እና መሞት የምፈልግ ሰው ነኝ።

ባህር ማዶ የመሔድ እድሉ እንዴት ተገኘ ወይም የሔዱበት ምክንያት ምን ነበር?
እኔ ውጪ አገር መሔድን እንደ እድል የምቆጥር ሰው አይደለሁም። ያኔም ስሔድ በግድ ነው የሔድኩት። ያኔ በእኔ እድሜ የነበሩ ልጆች የሚገደሉበት ዘመን ነበር፣ ብዙ ጓደኞቼን አጥቻለሁ። ጊዜው የምትደበደቢበት፣ የምትደፈሪበት ዘመን ነበር፣ ወጣትነት ራሱ አስፈሪ የሆነበት፣ ክፉ ነገር ያየንበት ጊዜ ነው። እና ምርጫ ስላልነበረኝ ተገፍቼ ነው የወጣሁት። እህቴ ጣልያን ስለነበረች፤ አልሔድም እያልኩ ነበር ብዙ ስጠብቅ የነበረው፤ አገር አለኝ ለምንድን ነው የምሔደው፣ እዛ ስሔድ ለእረፍት (ቫኬሽን) ነው የምሔደው የምል ሰው ነበርኩ።

እና ለእኔ ወደ ውጪ መሔድ እንዳልኩት እንደ እድል ሆኖልኝ አይደለም የሄድኩት። አገሬን ባህሌን በጣም ነው የምወደው፤ እዚህ መሆንን እፈልግ ነበር። ነገር ግን የነበረው የአገራችን ሁኔታ አስገዳጅ ሆኖ ነው። መሔዱም ቀላል አልነበርም። በዛም በዚህም ተብሎ ችግረኛ ነን በሚልና እህቶቼን ወጥቼ ማገዝና ማስተዳደር አለብኝ ብዬ የመውጫ ቪዛ ለማግኘት ለምኜ ነው፤ የውጪ ጉዳይን የማውቀው በዛ ነው። እዛ እየሄድኩ ለምኜ ነው ዋስ ተጠርቶ እንደምመለስ ተብሎ ነው የወጣሁት።

የውበት ሙያ ሥራ ውስጥ ተሳትፎ አድርገዋል፤ ለጥበብ አለኝ ያሉት ፍቅር ነው ከውበት ጋር ያገናኘዎ?
አርት ስለምወድ ነው ወደ ውበትና ፋሽን የገባሁት። ውበት ለእኔ ያውም ሰው ላይ የሚሠራ ትልቅ አርት ነው ብዬ ነው ያሰብኩት። በጣም ደስ እያለኝ እሠራ ነበር፤ ስለምወደውም ነው መሰለኝ ጎበዝ ነበርኩ። በሱ ጥሩ ሠርቻለሁ፤ አሁንም ውስጤ አለ። ፈጠራ ላይ ጥሩ ነኝ፣ ጥሩ እይታም አለኝ። እዛ ላይ ብዙ ሠርቻለሁ፣ ብዙም ተምሬበታለሁም።

እንዳልኩት ከተፈጥሮና ከአካባቢዬም ከሁሉም ነው የምማረው። ውበት ላይ ሲሠራም ከብዙ ሰው ጋር መገናኘቱ አለ። ለእኔ ዓላማዬ ፀጉር መሥራትና ገንዘብ መውሰድ አልነበረም፤ ከሱ ባሻገር ከሰዎች ጋር ስገናኝ፣ ሳወራ፣ ስማር ደንበኛ የሳይኮሎጂ ትምህርት ነው ያገኘሁት። እና በጣም ነው የምወደው። እሱንም ሠርቼ ኖሬበታለሁ።

በውጪ አገር የውበት ሳሎን ከፍተው ነበር?
ከአምስት ዓመት በላይ በራሴ የውበት ሳሎን ሠርቻለሁ። ኒያና የውበት ሳሎን ይባል ነበር። ሥራ የበዛበት ሳሎን ነበር፣ ከዛ በፊት ግን አራት አምስት ቦታዎች ላይ ሠርቻለሁ። በነዛ ቦታዎች ለመሥራት የፈለኩት ከተለያዩ ቦታዎች መማር ስለምፈልግ ነው። ለምሳሌ ጥቁሮች የሚበዙበት ቦታ ላይ ስትሠሪ የእነርሱን ባህሪ፣ ሕይወት ታውቂያለሽ፣ ሥራሽ ነውና ደግሞ ፍላጎታቸውን ስትረጂ በይበልጥም ሙያውን ትማሪያለሽ። ነጮች ጋር ስትኖሪም እንደዛው፤ ሚክስድ የሆኑ፣ ኢራኖችም በተመሳሳይ። ፊልም አክተሮችና ዘፋኞች የሚባሉት ያሉበት ጋር ሲኮን ደግሞ የሆሊውድን ዓለም ታውቂዋለሽ። እና ከብዙ ሰው ጋር ያገናኛል።

ፋውንዴሽኑ መጠሪያው ኒያ ነው፤ የውበት ሳሎኑ ስም ደግሞ ኒያና፤ የቃሉ ትርጉም ምንድን ነው?
ይህን ቃል መጀመሪያ የተጠቀምኩት ሎሳንጀለስ የውበት ሳሎኑን የከፈትኩበት ጊዜ ነው። ኒያና ራሴ የፈጠርኩት ቃል ነው፤ መነሻው ግን ኒያ የሚለው ቃል ነው። ኒያ ማለት መልካም ምኞት፣ መልካም ሃሳብ፣ መልካም ርዕይ፣ መድረሻ እንዲኖረው የምትፈልጊ ግን በመልካምነት የምትነሺበት ነው። ኒያ ብሎ መጥፎ ነገር የለም።
ለምሳሌ ኒያዬ ውበት ላይ መሥራት ቢሆንም ኒያዬ ግን ጸጉርና ፊት መሥራት ብቻ ሳይሆን ከዛ ባሻገር ነው። ኒያና ስንል ከምትሠሪው ነገር ከምትፈልጊው ነገር ባሻገር ነው። የምትፈልጊው ነገር ረጅም ነው፣ ጥሩ መድረሻ ያለው ርዕይ ነው። አንድ ነገር ስትሠሪ ለምሳሌ አንቺ ጋዜጠኛ ነሽ፣ ዝም ብሎ ጋዜጠኛ ለመሆን አይደለም። ምንድን ነው ማስተላለፍ የምትፈልጊው፣ ከዛስ ከተጻፈስ በኋላ፣ ቀጥሎ የሚመጣ ብዘ ነገር አለው። እና በኒያ ነው የምሠራው ትያለሽ። ይህ በቁርዓንም፣ በመጽሐፍ ቅዱስም ያለ ነገር ነው። በኒያ ጹሙ፣ ኒያ ይኑራችሁ፣ መልካም ነገር ለመሥራት ኒያ ይኑራችሁ ነው ነገሩ።

አንዱ ይሄ ሲሆን ሌላው እናቴ ሁሌም ይህን ትለን ነበር። ያለ ኒያ ምንም ነገር የለም ትለናለች። ኒያ አላችሁ፣ ኒያችሁን አዳምጡ፣ ኒያችሁን አድርሱ፣ በኒያ ጀምሩ ትላለች ሁልጊዜ። ያ ለስኬት ምስጢር ነው። ደስተኛ ሆኖ ለመኖር፣ ቀጥሎም ሕይወት አለ ብለሽ የምታምኚም ከሆነ ለሱም መነሻ ነው፤ እና የእናቴ ማስታወሻም ነው፤ እናቴንም ለማስታወስ ስል ኒያ አልኩ። ግን ‹ና›ን ጨመርኩባት፤ አንድም ለማጣፈጥ ነው፤ ኒያ አጠረችብኝና ኒያና አልኩት።

ኒያና ሲባል በትግረኛ የእኛ እንደማለት ነው። ሳላስበው ደግሞ በኦሮሚያ ‹ወደፊት እንገስግስ› ማለት ነው። አሁን ደግሞ ስሰማ በአላባም ኒያና የእኛ ማለት ነው። በኒያ ስለተጀመረ ትርጉሙ ሁሉ ቆንጆ ነው። እኔም ከዛ ውስጥ አልወጣም፤ ፋውንዴሽናችን ኒያ ነው፤ ሥራችን ኒያና ነው።

ብዙ ጊዜያቸውን በሥራ የሚያሳልፉ ሴቶች ለትዳር ይዘገያሉ፣ በትዳርም አይቆዩም የሚል አመለካከት አለ። እርስዎ ጋር እንዴት ነው?
ትዳር ላይ ማግባት ባለብኝና በምፈልግበት ጊዜ፣ በእኔ ዘመን ጥሩ ነው በሚባልበት እድሜ ነው ያገባሁት፣ 26 ዓመቴ አካባቢ። ግን አንቺ ሥራሽ ላይ ስትሮጪ፣ ይህን ያንን እሠራለሁ ስትይ ቀናት ሊዘገዩ ይችላሉ። ወይ ደግሞ ትዳር ውስጥ ተገብቶም መለያየትና ፍቺ ይታየል። ምክንያቱም ሕይወት አለሽ፣ ቁጭ ብለሽ አትጠብቂም። ኹለት ሲኮን የሚከብዱ ነገሮች አሉ። ይህን መምከሬ አይደለም፤ ግን እውነታው ነው።

ያገባሁት እንዳልኩት በወጣት እድሜዬ ነው። ልጆች እፈልግ ስለነበር ወለድኩ። ከዛ ግን እኔ እዚህ እሱ እዛ ሆነን ነበር የምንኖረው፣ ይህም ወደ መለያየት ይወስዳል፤ ሳታውቂውና ሳትፈልጊው። ምክንያቱም ሌላ ዓላማ ይያዛል። እኔ አሁን ከትዳር ባሻገር ብዙ ወጣቶች ላይ መሥራት፣ የራሴን ሥራዎች መሥራት፣ ኦቲዝም ያለባቸውና የተጎዱ ልጆች ላይ መሥራት (ከድሮም እዛው ውስጥ ነበርኩ) ነው የምፈልገው። ይህ ሁሉ ቅድሚያውን ስለሚወስድ ነው።

ኒያ ፋውንዴሽን እንዴት ተመሠረተ?
በኒያ ፋውንዴሽን የምንሠራው ኦቲዝም ላይ ብቻ አይደለም። ከኦቲዝም በፊት ወጣቶች ላይ ብዙ ሠርተናል። በተለይም የተቸገሩ ወጣቶች ላይ፣ ሴተኛ አዳሪ ሆነው የሚተዳደሩ ሴቶች ላይ፣ ችግር ላይ ያሉ ወንዶች፣ ምክር፣ ሥራ… ብቻ ሰው የሚፈልጉ ወጣቶች ላይ ብዙ ሠርተናል። ከዛ ነው ወደ ኦቲዝም የገባነው።

ሲመሠረት ወጣቶች ላይ ብቻ ነው፤ ኦቲዝም የሌለባቸው፤ ከዛ ኦቲዝምን አካተትን። እናቶች ላይ እንሠራለን። ማተኮር የምንፈልገው የልዩ ፍላጎት ልጅ የሚያሳድጉ እናቶች በተለይ ከአእምሮ ጋር በተያያዘ ኦቲዝም ይሁን ወይ የአእምሮ እድገት ውስንነትም ቢሆን ብቻ ችግር ያለበትን ልጅ ማሳደግ ቀምሰን አይተነዋልና፤ በቅርበትም ችግራቸውን ስለምናውቅ ከእነርሱ ጋር መሥራት አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘነው ነው።

ከጀመርን ብዙ ዓመት ነው። ሕጋዊ ፈቃድ ተሰጥቶና በበጎ ሥራ ኤን ጂ ኦ ላይ ፋውንዴሽኑን አቋቁመን ስንሠራ ሚያዝያ ሲመጣ 18 ዓመታችን ይሆናል።

በአንዳንድ ሰዎች ሕይወት የሚያልፉ አጋጣሚዎች ለሌሎች እንዲተርፉ ምክንያት ይሆናቸዋል። ከዚህ አንጻር በዘሚ ሕይወት የተፈጠረው ነገር ለሌሎች ብዙዎች ተስፋ ምክንያት ሆኗል። ይህን እንዴት ያዩታል?
መውቀስ አይሁንብኝና መጀመሪያ ላይ ከቤተሰቤ ጀምሮ ህብረተሰቡን፣ መንግሥትን፣ አስተማሪዎችን ሁሉ ያማረርኩበት ጊዜ አለ። ለምን አልነገሩኝም፣ ለምን አላስተማሩኝም፣ ለምን ሁላችንም እንዲህ ዓይነት ልጅ ልንወልድ እንደምንችልና ችግር ሊያጋጥመን እንደሚችል አላስተማሩኝም አልኩኝ።

ይህ ስሜት የተሰማኝ በሕይወቴ ኹለት ጊዜ ነው። መጀመሪያ እናቴ ስትሞት ነው፤ የእኔ እናት የምትሞት አይመስለኝም ነበር። ያኔ ጣልያን ነበርኩ። የእናቴ ሞት በጣም አስደነጋጭ ነበር። የጓደኞቼ እናቶች በልጅነታው ሲሞቱ አይቻለሁ፤ የእኔ እናት ግን የምትሞት አይመስለኝም ነበር። ትልቅ ድንጋጤ ነበረኝ፤ ወደ ጤናዬ መመለሴም እድለኛ ነኝ።

ኹለተኛው ደግሞ የልጄ ነው። ትልቅ ድንጋጤ፣ ፍርሃት፣ ለቅሶ፤ ዓለም ያበቃ ነው የመሰለኝ። ‹‹እንዴት የእኔ ልጅ!?›› አልኩኝ። እንዴት እንዲሁ እኔ ላይ ሆነ ብዬ፤ የእኔ ጥፋት ነው ያደረኩት። ያንን ለመቀበል ረጅም ጊዜ ነው የፈጀብኝ። ያ የሆነው ስላላስተማሩኝ ስላልነገሩኝ ነው። ዘሚ አንቺም እንዲህ ዓይነት ልጅ ልትወልጂ ትችያለሽ። በሌላ መልኩ ስናድግ አንቺ ከማንም አትበልጪም ነው። እናቴ እንደዛ ትለን ነበር፤ ከማንም አትበልጡም ተነሱ ሥሩ፣ እናንተ ዛሬ ደኅና ስለሆናችሁ ሌላው ከእናንተ ያንሳል ማለት አይደለም የምትለን ነገር ነበር፤ ብዙ አስተምራኛለች፤ ግን በሥራና በመሳሰለው ነው። በእንደዚህ አላየሁት። ወይም መማር አልነበረብኝና በተፈጥሮ የሚቀሰም ከሆነ አላውቅም፤ ግን ከባድ ነበር።

ለተወሰነ ጊዜ ማልቀስና ማዘን ነው። ዓለም የተገለበጠብሽ ሰው ሁሉ የጠላሽ ነው የሚመስልሽ። መሞት ሁሉ ትፈልጊያለሽ። ወደፊት መሔድ የምትችይ አይመስልሽም። ስናድግ የተነገረን እብድ እየተባልን ነው። ልጇ’ኮ እብድ ነው፣ በሽተኛ ነው እየተባለ ነው የምንሰማው። እና እብድ ወለድኩ ወይ እኔ፣ የምወደው ልጄ እብድ ሆነ እያልኩ እኔ ራሴ ተጨንቄ ነበር።

ከዛ ግን ትዝ የሚለኝ ‹እንዴ!› ማለት ጀመርኩ፤ ለምን እኔ አልሆንም አልኩኝ። ይሄ ነገር በዓለም ላይ መሆን ካለበት መሆን አለበት ነው። እንዲህ ዓይነት ልጆች ይወለዳሉ፣ ረጅም ሰው አጭር ሰው፣ ጥቁርና ቀይ፣ ሴትና ወንድ ሆኖ ሰው እንደሚፈጠረው ሁሉ፤ እንዲህ ዓይነት ነገሮችም ሊኖሩ ይችላሉ። እና እኔ ማን ነኝ እንዲህ ዓይነት ልጅ የማልወልደው ማለት ጀመርኩኝ፤ ያኔ ነው ደኅና የሆንኩት።

ይህን ሥራ የምሠራውም ለምንድን ነው፤ እኔ ያለፍኩት እጅግ በጣም ከባድ ነገር ነው። ሌሎች በዚህ እንዲያልፉ አልፈልግም። ቢያንስ ማስተማር አለብኝ። እንዲህ ዓይነት ልጅ መውለድ የዓለም መጨረሻ አይደለም። መርጠሸ አይደለም የምትወልጂው፣ ይሄ ነው ጥሩ ይሄ ነው መጥፎ ማለት አትችይም። እናትነት ደግሞ በተለይ የሚታየው እንዲህ ሆነህ ስለመጣህ አንተን አልፈልግም/አንቺን አልፈልግም የምትይው መሆን የለበትም። ምንም ይምጣ ምንም ልጅሽ ነው፣ እና ያንን የተቀበልኩበት ጊዜ ነው።

ልጄን ሳልቀበለው ቀርቼ አላውቅም። አንዴ ብቻ የፈራሁበት ጊዜ ነበር፤ ሰይጣን ነው ያሉኝ ጊዜ። ሰይጣን ይዞታል፣ ሰይጣን ሰይጣን ከብዙ ቦታ ሲባል ሳየው የእውነት ውስጡ ያለ መስሎኝ መፍራት ጀመርኩ፤ ሌሊት ምን ያደርገኝ ይሆን ብዬ። በኋላ ግን ያወኩትና ለራሴም የነገርኩት አላወቁትም እንጂ እልም ያለ መልዐክ ነው እንጂ የምን ሰይጣን ነው ማለት ጀመርኩ።

እና እኔም ራሴ ስለ ኦቲዝም ሰምቼ አላውቅም። ሲደርስብኝ አንድ የእኔን አየሁት እንደ እናት ያለፍኩበትን፤ ብቸኝነቴን። ሀኪሞች አያውቁልሽም፣ አገር አያውቅልሽ፤ ህብረተሰብ አያውቅልሽም፣ እንዴት ብቸኝነት እንደሚያጠቃ ልነግርሽ አልችልም። ለማን ነው የሚነገረው፤ ማን ጋር ነው ኡኡ የሚባለው፣ እባካችሁ ልጄን አድኑልኝ ብትይ የሚሰማ የለም። ያ ለወላጆች ምን ያህል ክፉ እንደሆነ። እንደገና ሌሎች ልጆች ታስረውና ብቸኛ ሆነው፤ ባይናገሩም አታድኑንም ወይ እኛስ መጫወት እንፈልግም ወይ፣ እኔስ ማን አለኝ ሲሉ ድምጻቸው ይሰማኛል።

እና እነዚህን ልጆች ሳይ ይቅርብኝ አልኩኝ። ሌላ ሥራ ውስጥ ነበርኩ፤ ሀብታም ሆኜ ህንጻ ሰርቼ የሚል ህልም ነበረኝ። እና የትኛው ነው የሚሻለው አልኩኝ። የእኔ ጥሪዬ ይሄ ነው ማለት ነው፤ እግዚአብሔር ይህን ልጅ የሰጠኝ ለምክንያት ነው፤ ይህንን ደግሞ እየነገረኝ ዝም ማለት አልችልም፤ ስለዚህ ይህን ነገር መሥራት አለብኝ፤ ሕይወቴ ይሄ መሆን አለበት ብዬ ጀመርኩ።

ለነገሩ በቀላል የሚሠራ መስሎኝ ነበር፤ በጣም ከባድ ነው። አሁንም ዛሬ ድረስ የምትደነግጪበት፣ የምትፈሪበት ሁኔታ አለ። በእኛ አገር ሁኔታ ሁሉም አንቺ ላይ ይጫናል፤ አደራህን እያልሽ ነው የምትኖሪው። ግን ደስ የሚል ስቃይ ነው።

ስለመጀመሪያ ልጅሽ ብዙ ጊዜ አይነሳም፤ እስቲ ስለእሱ እናንሳ። ማን ይባላል፤ ከወንድሙ ጋር ቅርርባቸው እንዴት ነው?
ይህን ጥያቄ ብዙ ሰው አልጠይቀኝምና አመሰግናለሁ። ያም ልጄ ነው፤ ብዙ ሰው የሚያውቀው ኹለተኛውን ልጄን (ጆጆን) ነው፤ እኔም ካልተጠየቁኩ ስለማልናገር ነው። ቢላል ይባላል። በጣም በጣም ግሩም ልጅ ነው። እርሱ ኦቲዝም የለውም። ከወንድሙ ጋር በጣም ፍቅር ናቸው። እኔ ማዳላት የለብንም ብዬ አምናለሁ። በልጆችም ይሁን በጓደኛና በሰው መካከል ማዳላት የለብንም። የተዳላበት ሰው ምን ያህል ሊከፋው እንደሚችል አስባለሁ። የትም ስሔድ ሰዎች እንዳይገለሉ አስባለሁ። እና በጣም እጠነቀቃለሁ።

እና እንዳላዳላ ከማሰብ ብቻ አይደለም። ፍቅሬም እኩል ነው። ሌሎች ሰዎች እንዴት እንደሚያደርጉት አላውቅም፤ ለአንዱ የበለጠ እንደሚያደሉ፤ ለእኔ ግን ኹለቱም እኩል ናቸው። ምንአልባት ኹለተኛው የበለጠ ትኩረቴን ስለሚፈልግ እሰጠው ይሆናል ነው። በተረፈ ግን ቢላል እንዳልኩት ግሩም ልጅ ነው። ከልጄ ጋር እንግባባለን፣ አንድ ዓይነት ቋንቋ ነው የምናወራው፣ ስለዚህም ደስ ይለኛል። ያሳደግኳቸውም እዚህ ነው፤ ያንንም ያደረኩት አውቄና ፈልጌ ነው፣ ባህላቸውን አውቀው እንዲያድጉ ስለምፈልግ ነው። በእርሱም በጣም ደስተኛ ነኝ።

ኒያ ፋውንዴሽን በተለይም ከኦቲዝም ጋር በተገናኘ አዲስ ማዕከል እንደሚያስገነባ ተነግሮ ነበር፤ ምን ደረሰ?
አጋጣሚ ሰርቬይ የተጀመረው ሰሞኑን ነው። ማዕከሉን ለመገንባት ቦታ ለማግኘት 12 ዓመት ያህል ቆይተናል፣ 12 ዓመት። ረጅም ጊዜ ወስዷል። ማዕከሉ ታድያ ሁለገብ አገልግሎት የሚሰጥ ነው። ልጆች እንደልባቸው የሚጫወቱበትና የሚንቀሳቀሱበት እንዲሁም የሚማሩበት ነው የሚሆነው።

ለምሳሌ አንዳንድ መዋኛ ያለባው ቦታዎች ልጆቻችንን ይዘን ለዋና ስንሔድ እሺ ብለው አይቀበሉንም፣ ይከለክላሉ። ስለዚህ እስኪጨልምና ሰው እስኪወጣ መጠበቅ ያስፈልጋል። ቁስል አለብን፤ ተረድቶ የሚቀበል የለም። ትምህርት ቤትም ይረብሻል ብለው አይቀበሉም፣ ቢቀበሉም ቆይተው ያባርራሉ። እነዚህ ልጆችም ልጆች ናቸውና መጫወት ይፈልጋሉ፤ መማር አለባቸው። መጫወቻ ቦታዎች ደግሞ የሉም፤ ያሉት ቦታዎች ስትሔጂ መኪና አለ ሰው አለ ብለሽ ተጨንቀሽ ነው። እንዲህ ያሉ ነገሮችን የሚያሟላ ማዕከል ነው የሚሆነው።

ኦቲዝም ላይ ብዙ ተሠርቷል፣ ብዙ ተብሏል ግን የተባሉት ችግሮች አሁንም አሉ። ግንዛቤ እስከሁን እንዴት ሳይዳረስ ቀረ?
ሰው ከፈለገ ይሰማል፤ ካልፈለገ አይሰማም። እናይሻለን ይሉኛል፤ ግን እስቲ ምን እንደተባለ ትኩረት የማይሰጡ አሉ። ራድዮን የማይከፍቱት እንዴት ይሰማሉ። እርግጥ ነው መጀመሪያ ከነበረው እጅግ በጣም ሔደናል። እንደውም እንደ ኦቲዝም የታወቀ የለም። ሁሉም ሰው ኦቲዝምን ያውቃል ብዬ አስባለሁ። ግን ደግሞ ገና ብዙ ይቀረናል። ለምን፤ ኦቲዝም በሚያስደነግጥ ሁኔታ እጅግ በጣም እየበዛ ነው።

በመንግሥት በኩል የሚመለከታቸው የሚባሉ አካላት ምን ያህል ሥራቸውን ሠርተዋል ማለት ይቻላል?
የሚመለከታቸው ሁሉም ናቸው፤ ሁሉም ይመለከተዋል። አንዳንዴ ሁሉም ስንል ሰዎች የተለመደ ሊያደርጉት ይችላሉ። ግን ሴቶችና ሕጻናት ይመለከተዋል፣ ጤና ሚኒስቴር ይመለከተዋል፣ ትምህርት ሚኒስቴር ይመለከተዋል፣ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ጉዳይ ላይ ያሉት ይመለከታቸዋል፤ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ይመለከተዋል፤ ሁሉም ይመለከታቸዋል።

ለምን መሰለሽ፤ የተያያዘ ስለሆነ ነው። ስለህጻናት እና ወጣቶች እየተወራ እነዚህን ልጆች መተው አይቻልም። ስለኦኮኖሚ እያወሩ እነዚህን ልጆች መተው አይቻልም። እንዴት አድርገው ነው እናት እና አባት ሥራቸውን የሚሠሩትና ስለአገር እድገት የሚወራው። አንድ ሰው ልጅ ካለው ልጁን ትምህርት ቤት ልኮ ነው ሥራውን የሚሠራው። ያ ካልሆነ እንዴት ይሠራል። እነዚህን ልጆች ቸላ ብሎ ድህነት ቅነሳ እንዴት ይወራል። ጤና እንዴት ነው ሊኖረኝ የሚችለው ልጄን አስሬ ከሔድኩ። እነዚህን ልጆች ትምህርት ቤት ሳያካትቱ እንዴት ነው ስለ አካታችነት የሚወራው። የአንቺ ልጅ ትምህት ቤት እየሔደ ለምንድን ነው የእኔ ልጅ የማይሔደው። እኩል ልጅ ናቸው፤ እኩል ታክስ እንከፍላለን፤ እኩልም ዜጎች ነን። እኩል ልጆች ናቸው እነዚህም፤ በምን ምክንያት ነው የሚቀሩት።

እዛ ቦታ ላይ እንዲሠራ ተብሎ የተቀመጠ ሰው ለሁሉም ልጆች ነው እንጂ እነዚህን ልጆች አግልሎ እንዲሠራ አይደለም። ስለጤናም እንደዚሁ፤ ጤና ለሁሉም ሲባል እነዚህ ልጆች አካትቶ ነው እንጂ ሚዛን አሳጥቶ አይሆንም። ስለፋይናንስ በጀት ሲያዝ ፍትህ ያስፈልጋል፤ ለሁሉም ተደራሽ መሆን አለበት። አገሪቱ ደሃ ናትና ለእነዚህ ልጆች ምንም የለንም ማለት አይቻልም። ካለው ላይ ነው ለሁሉም ልጆች ማካፈልና ገንዘቡንም መመደብ።

ስለዚህ እኩል ለሁሉም እንዲደርስ ሁላችንም መቆም አለብን። ሁሉም ሰው እንደሰው ከታየ፤ አንድ ሰው ትምህርት ቤት የሚሔደው የማይችለውን እንዲችል ነው፤ ያላወቀውን ለማወቅ። እነዚህም ልጆች ትምህርት ቤት የሚሄዱት ያልቻሉትን እንዲችሉ፣ ያላወቁትን እንዲያውቁ ነው።

ለምሳሌ ሽንት ቤት መጠቀም የማይችል ከሆነ እንዲጠቀም ታስተምሪዋለሽ። የማይናገር ከሆነ እንዲናገር ማስቻል ነው። እንደ ሰው መታየት አለባቸው። ይሄ ዋናው ነገር ነው።

ጨለማ ቤት ውስጥ መቀመጥ የለባቸውም። እኛ ለሳምንት ምንም ሳናደርግና ምንም ሳንናገር ጨለማ ቤት ውስጥ ብንቀመጥ እንታመማለን። እነዚህ ልጆችም እንደልጅ መውጣት፣ መጫወት አለባቸው። ይህ ግን አልተደረገላቸውም። በተለይ በኃላፊነት የተቀመጡ ሰዎች ይጠየቁበታል። በእምነትም ጭምር። ምክንያቱም ኃላፊነት የተሰጣቸው ለሁሉም ነው። ህሊናቸው እንዲቆሰቁሳቸው ይገባል። በኃላፊነት እዛ ቦታ ላይ ተቀምጦ ካልሠራ ምን ሊያደርግ ነው የተቀመጠው። ይሰሙና እንዳልሰሙ ይሆናሉ።

እና አይገባቸውም፤ እንዲገባቸው ያስፈልጋል። ከ18 እና 20 ዓመት ልፋት በኋላ አሁንም የምለው አልገባቸውም፤ አይገባቸውም ነው። ይሄ ፍላጎት፣ ልጅ ምን ማለት እንደሆነ አልገባቸውም። የኔ ስቃይ ምን ማለት እንደሆነ የኔ ፍላጎት ምን እንደሆነ አልገባቸውም። ስለዚህ ወይ የሚገባውን ሰው እዛ ቦታ ላይ ማስቀመጥ አለባቸው።
ለምሳሌ ትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ ልዩ ፍላጎት ተብለው የሚቀመጡት አይገባቸውም፤ የሱ ልጅ ግን ትምህርት ቤት እየሄደ ነው። ለልዩ ልጆች ኃላፊ ሆኖ ግን ተቀምጧል። ስለእኔ ልጅ ካላገባው ምን ሊሠራ ወይም ምን ልትሠራ እዛ ቦታ ተቀመጠ/ ተቀመጠች። እንዲያውም የሚሻለው ብዬ የማስበው እንደ እኔ ዓይነት ልጅ ያላቸው ሰዎች (የማይናገር፣ ራሱን መከላከል የማይችል፣ ድምጹን ማሰማት የማይችል፤ አላደረክልኝም ብሎ ድንጋይ መወርወር የማይችል ልጅ) ወላጁ ኃላፊነት ቦታ ላይ መቀመጥ አለበት። የሚያውቀው። ምክንያቱም ለእነዚህ ልጆች ሊሠራ ይችላል። ልጆቹን የሚወክልልን ማለት ነው።

ለምሳሌ ዓይነ ስውራን ቦታ ይሰጣቸውና ተወካይ ለመብታቸው ይከራከራል። አካል ጉዳት ያለበት ለእኛስ ይላል። እነዚህ ልጆች ለእኛስ ማለት አይችሉም፤ ማን ይበልላቸው? የተቀመጡት ደግሞ አይሉላቸውም። ያለው ችግር በየቦታው የሚያሳዝን ነው።

ለኦቲዝም ብቻ አይደለም፤ ከኦቲዝም ውጪ ችግር ያለባቸው ልጆች አያቶች የሚሰቃዩትን ስቃይ…ምክንያቱም እናቶቻቸው እዚህ ኢኮኖሚው ስላልተመቻቸላቸው በየባህሩ የገቡት ማን ናቸው? በየአረብ አገራት ያበዱት እነማን ናቸው? እነዚህን ልጆች ጥለው የሄዱ ናቸው። ስለዚህ እነዚህን ልጆች የሚያሳድገው ማን ነው፤ አያቶች። በሌላቸው አቅም ተሸክመው ይዘው። እና ለእነሱ ሁሉ የሚቆም ሰው ያስፈልገናል። ያሉት ግን አልገባቸውም፤ አይገባቸውም።

ለአንድ ሳምንት ዘሚ ስልኳን አጠፋፍታ ጥፍት ብትል በጉዳዩ ላይ ያገባኛል የሚልና ስለልጆቹ የሚከራከር ሰው አለ ይሆን?
አሉ ብዬ አስባለሁ፤ ይኖራሉ። የእኔን ያህል የሚጮኹ ባይሆንም። አሁንኮ ስብሰባ ላይ ሌላ ነገር ልናገር እጄን ሳነሳ ኦቲዝም ልትል ነው ሲሉ ሰምቻለሁ፤ ኦቲዝሟ ሴትዮ ይሉኛል። ‹‹አየሃት ያቺ ሴትዮ አወቅካት?›› ሲባል፤ ኦቲዝሟ ሴትዮ የሚሉም አሉ።

እኔ ባልኖር የሚናገር የለም ሳይሆን የሚያሳዝነኝ የሰዎችን ተስፋ አጠፋለሁ ብዬ አዝናለሁ። መኖር የምፈልገው አንድም ለልጄ ነው፤ በዛም ላይ ለእነዚህ ልጆችና እናቶች ነው። ምክንያቱም ፊቴ እንኳ ትንሽ ከተከፋ እንዴት እንደሚደነግጡ። ተስፋቸው ሆኜ ስለሚያዩኝ ይደነግጣሉ፣ ይፈራሉ። አንዴ ታምሜ ነበርና ያኔ እንዴት እንደሆነ መናገር ይቸግራል። ተስፋቸውን አጨልምባቸው ይሆን ብዬ እሰጋለሁ። ፈጣሪንም አትውሰደኝ እስኪስተካከል፤ ይህን ቤት እስክሠራ ድረስ እለዋለሁ።

ምክንያቱም ይህን ቤት ከሠራን ቤቱ ራሱን ይችላል፤ ገቢ ስለሚኖረው። ከዛ በኋላም መለመን አያስፈልገንም። ቢያንስ ልጆች እዛ እየሄዱ ይማራሉ ወላጆች ይሠራሉ፤ ትንሽ ተስፋ ይሆናል ብዬ አስባለሁ። ተተኪዎች ይኖራሉ፤ ዘሚ ባትኖርም።

ጊዜያዊ እረፍት ቢወስዱ ማለቴ እንጂ እድሜና ጤና ይስጥልን፤ ሞትን ማንሳቴ አልነበረም፤ አይ! እሱንም ቢሆን እናወራለን። የወላጆች ግሩፕ አለን፤ እኔ ይህንን ጉዳይ አነሳለሁ፤ እውነታውን እንጋፈጥ ነው የምላቸው። እኔ ሳልኖር፣ ለዘለዓለም ነዋሪ አይደለሁም። ቀድሞ እንዳልኩት ስለልጄ ባስተማሩኝ እንዳልኩት አሁንም ማለት አልፈልግም፤ ስለዚህም ባስተማሩኝ አልልም። ማንም ነዋሪ የለም፤ እሞታለሁ፤ ለወላጆችም እነግራቸዋለሁ እንሞታለን። ስንሞት ግን ልጃችንን አዘጋጅተነዋል ወይ እላቸዋለሁ፤ እንዳበረታታቸው ነው። ስለዚህ እንድ ቀን እድሜ ሲሰጠን እንድንሠራበት ነው እላቸዋለሁ። ተመስገን ብለን እንሥራበት ነው፤ ልጄን ይህን አስተማርኩ እንድንል።

ለምሳሌ መብላት የማይችል ከሆነ እንዲበላ ቶሎ እናስተምረው፣ አንስነፍ። እኛ ስንሞት ቢያንስ ራሱ መብላት እንዲችል። ቆሻሻ ልጅ እንዳይሆን በደንብ አስተምሩት ምክንያቱም እኛ ሳንኖር የሚቀበለን ሰው ሁሉን ነገር የማይችል ከሆነ እንቢ እንዳይል፤ ወንድም እህትም ቢሆን ይሰለቻል። እንሥራ እንልፋ እላቸዋለሁ። እኔ ሁሌ የማስበው እኔ ሳልኖር እያልኩኝ ነው። ማዕከሉንም ሳይ፤ አሁን እየለመንኩ እከፍላለሁ። እኔ ሳልኖርስ? ራሱን ማስተዳደር አለበት።

ጆጆ አሁን ጎበዝ ነው። ንጽህናውን ይጠብቃል፣ ሻወር ይወስዳል፤ መብላት፣ ማብሰል ይችላል፣ ቤት ያጸዳል። ወንድሙ ጋር ወይም ሚስቱ ጋር ብቻ ማንም ጋር ብተወው ቢያንስ እቃ አጥቦ ያኖራል። ይህን መሥራት አለብህ እያልኩ አስተምረዋለሁ። እና ቢያንስ አጋዥ ነው ብዬ ከማሰብ ነው።

እናበቅ፤ በዚህ አጋጣሚ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ ይቻላል?
ኹለት ነገር ባነሳ ደስ ይለኛል። አሁን ባለንበት ሁኔታ ቁስል አለብን። በእኛ ችግር ሀብት መሥራት የሚፈልጉትን አንቀበልም። እናስተምርላቸኋለን እያሉ የማይገባ ገንዘብ የሚጠይቁ ሰዎች ተነስተዋል፤ በተለያየ መልኩ። ይሄ በቁስላቸን ላይ መነገድ ስለሆነ አንቀበለውም። የሚከፍሉ ሰዎችም መጠንቀቅ አለባቸው የሚለው አንዱ መልእክቴ ነው።

ኹለተኛ እኛ እየለፋን እየሠራን ነው። ሁሉም ሰው ቢያግዘን ደስ ይለኛል። በተለይም ይህን ቤት ለመሥራት ሁላችንም ብንረባረብ፣ ሁሉም ሰው በዓመት የአንድ ቀን ገቢያቸውን ባንክ ሄደው ኒያ ፋውንዴሽን ቢሉ አካውንት አለ፤ ቢስገቡልን ይጠቅመናል። እየመጣችሁ ጠይቁን ማለት እፈልጋለሁ።

ሌላው ኦቲዝም በጣም እየበዛና እየጨመረ ነው። ባይሆን ደስ ይለናል። ከሆነ ግን ሁሉም ሰው ተዘጋጅቶ መጠበቅ አለበት። ከሆነ ምንም ማድረግ ስለማይቻል ከአሁኑ መዘጋጀትና መቀበል፤ ልጄ ሰይጣን አለበት ሳይሆን መልዐክ ነው ብሎ ማመን ነው። ከሁሉም ሃይማኖት ያሉ የሃይማኖት መሪዎችም ልጆቹን ሰይጣን አለበት የሚለውን ቢተዉ ጥሩ ነው፤ ወላጆች እኔ አጋጥሞኝ እንደነበረው ልጆቻቸውን እንዳይፈሩ።

ቅጽ 1 ቁጥር 50 ጥቅምት 8 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com