ከሰኔ 14ቱ ምርጫ የተገለሉ አካባቢዎች ጉዳይ

0
961

ኢትዮጵያ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ በርካታ የቅድመ ምርጫ ሥራዎችን አከናውና የምርጫው የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች። ሥድስተኛው አገራዊ ምርጫ በኮቪድ-19 ምክንያት ከመደበኛ ጊዜው ተራዝሞ እዚህ መድረሱ የሚታወቅ ነው። ኢትዮጵያ ሥድስተኛውን አጠቃላይ ምርጫ የሚያሳልጥላት የገለልተኝነት ኃላፊነት የተሰጠውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደ አዲስ አቋቁማ ወደ ሥራ አስገብታለች። ይሁን እንጅ አዲስ የተዋቀረው ምርጫ ቦርድ፣ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ በታቀደለት የጊዜ ሰሌዳ ለማካሄድ አልቻለም። ለዚህም ምርጫ ቦርድ ቀድሞ አዘጋጅቶት በነበረው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የምርጫ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሳለጥ አለመቻሉን በምክንያትነት ገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሥድስተኛው አገራዊ ምርጫ ቀድሞ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የምርጫ ቅድመ ሥራዎችን መፈጸም ያልቻለው፣ በመንግሥት በኩል የሚጠበቁ ሥራዎች በጊዜው ባለመሰራታቸው እና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮችን እንደ ዋና ምክንያት አንስቷል። ቦርዱ የምርጫ ቅድመ ሥራዎችን በተያዘለት ጊዜ ለማሳለጥ ባለመቻሉ ግንቦት28/2013 ለማካሄድ ያስበውን ምርጫ ለማራዘም ተገዷል። በዚህም ምርጫው ሰኔ 14/2013 እንዲካሄድ ውሳኔ ማሳለፉ የሚታወስ ነው። ሥድስተኛው አገራዊ ምርጫ ከትግራይ ክልል ውጭ በሁሉም ክልሎች እንደሚካሄድ ቦርዱ ቀደም ሲል መወሰኑና በዚሁ መሰረት ሥራዎች እየሰራ መሆኑ የሚታወስ ነው። ይሁን እንጅ ምርጫው በሁሉም ክልሎች በተሟላ ሁኔታ ሰኔ 14/2013 ለማካሄድ እንደማይቻል ቦርዱ አስታውቋል።

የምርጫ ቅደመ ሥራዎች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ አለመጠናቀቃቸውን ተከትሎ፣ ሰኔ 14/2013 ምርጫ የማይካሄድባቸው የምርጫ ክልሎች እና የምርጫ ጣቢዎች እንዳሉ ቦርዱ ይፋ አድርጓል። በሰኔ 14/2013 የድምጽ መስጫ ቀን ምርጫ ከማይካሄድባቸው ቦታዎች መካከል በሰባት ክልሎች ውስጥ የሚገኙት የሚከተሉት ናቸው። በተጠቀሱት ምክንያቶች ምርጫ ከተራዘሙባቸው ክልሎች ውስጥ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመራጮች ምዝገባ ያልተጀመባቸው አራት የምርጫ ክልሎች ሲሆኑ፣ መተከል የምርጫ ክልል፣ ሺናሻ ልዩ የምርጫ ክልል ፣ ካማሽ የምርጫ ክልል እና ዳለቲ የምርጫ ክልል ናቸው።

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል በጸጥታ ችግር የመራጮች ምዝገባ ያልተጀመረባቸው አራት የምርጫ ክልሎች ሲሆኑ፣ ዘልማም የምርጫ ክልል፣ ሱርማ ልዩ የምርጫ ክልል፣ ዲዚ ልዩ የምርጫ ክልል እና ሙርሲ ልዩ የምርጫ ክልል መሆናቸውን ቦርዱ አስታውቋል። በሐረሪ ክልል በመራጮች ምዝገባ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ የተዛባ አሰራር የታየባቸው እንዲሁም ጉዳያቸው በሕግ የተያዘ ሦስት የምርጫ ክልሎች ሲሆኑ፣ ጀጎል ልዩ የምርጫ ክልልና ጀጎል መደበኛ የምርጫ ክልል፣ ጀጎል ዙሪያ እና ሁንደኔ የምርጫ ክልል ናቸው።

በሶማሌ ክልል የመራጮች ምዝገባ ሂደት ላይ አቤቱታ የቀረበባቸው እና በመጣራት ላይ ያሉና ምርጫ የማይካሄድባቸው 14 የምርጫ ክልሎች ሲሆኑ፣ አራቢ የምርጫ ክልል፣ ደግሃመዶ የምርጫ ክልል፣ ጎዴ የምርጫ ክልል ፣ ጂግጂጋ አንድ የምርጫ ክልል፣ ጂግጂጋ ኹለት የምርጫ ክልል፣ ቀብሪ-ደሃር ምርጫ ክልል፣ ቀላፎ የምርጫ ክልል፣ ዋርዴር የምርጫ ክልል፣ ፊቅ የምርጫ ክልል፣ ገላዲን የምርጫ ክልል፣ አይሻ የምርጫ ክልል፣ ኤረር የምርጫ ክልል እና ሽንሌ የምርጫ ክልል ናቸው። በአማራ ክልል በጸጥታ ችግር የመራጮች ምዝገባ ያልተጀመረባቸው ስምንት የምርጫ ክልሎች ሲሆኑ፣ ማጀቴ (ማኮይ) የምርጫ ክልል፣ አርጎባ ልዩ የምርጫ ክልል፣ ሸዋሮቢት የምርጫ ክልል፣ ኤፌሶን የምርጫ ክልል፣.ጭልጋ አንድ የምርጫ ክልል፣ ጭልጋ ኹለት የምርጫ ክልል፣ ላይ አርማጭሆ የምርጫ ክልል እና ድልይብዛ የምርጫ ክልል ናቸው። አብዛኛዎቹ በሰሜን ሽዋ ዞን ችግር የተከሰተባቸው ናቸው።

በኦሮሚያ ክልል በጸጥታ ችግር የመራጮች ምዝገባ ያልተጀመረባቸው ሰባት የምርጫ ክልሎች ሲሆኑ፣ ቤጊ የምርጫ ክልል (ምእራብ ወለጋ)፣ ሰኞ ገበያ ምርጫ ክልል(ምእራብ ወለጋ)፣ አያና የምርጫ ክልል(ምስራቅ ወለጋ)፣ ገሊላ የምርጫ ክልል(ምስራቅ ወለጋ)፣ አሊቦ የምርጫ ክልል (ሆሮ ጉድሩ)፣ ጊዳም የምርጫ ክልል (ሆሮ ጉድሩ) እና ኮምቦልቻ የምርጫ ክልል(ሆሮ ጉድሩ) መሆናቸው ተግልጿል። በጋምቤላ ክልል ምርጫ የተራዘመባቸው ኹለት የምርጫ ክልሎች ሲሆኑ፣ በዲማ የምርጫ ክልል እና በአኮቦ የምርጫ ክልል ናቸው።
የእነዚህ የምርጫ ክልሎች የድምጽ መስጫ ከመደበኛው ድምጽ መስጫ ቀን ማለትም ሰኔ 14/2013 ለሌላ ጊዜ የተራዘመው፣ በፀጥታ ችግር የመራጮች ምዝገባ ያልተጀመረባቸው፣ የመራጮች ምዝገባ ተጀምሮ የተቋረጠባቸው እና በመራጮች ምዝገባ ሂደታቸው ላይ ቦርዱ ጉልህ የአሠራር ችግር በማየቱ ማጣራት እንዲደረግባቸው የወሰነባቸው ቦታዎች መሆናቸውን ቦርዱ አስታውቋል።

ለሌላ ጊዜ የተላለፉ የምርጫ ክልሎችን ጉዳይ በምርጫው ተሳታፊ የሆኑ ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው በቤኒሻንጉል ክልል የሚንቀሳቀሰው ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በክልሉ ተለይተው ፣ምርጫ የተራዘመባቸው አካባቢዎች ላይ የተወሰነው ውሳኔ ትክክል አለመሆኑን ለአዲስ ማለዳ ገልጿል። የፓርቲው ሊቀመንብር አመንቴ ገሽ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት ከሆነ፣ ምርጫው በጸጥታ ምክንያት የተራዘመባቸው የክልሉ ካማሺና መተከል ዞኖች ከክልሉ ተለይተው የተራዘመበት ሁኔታ ትክክል አይደለም ብለዋል።

አመንቴ አክለውም በፓርቲያቸው አቋም፣ በአሶሳ ዞን ያለው የጸጥታ ሁኔታ በክልሉ ካማሺና መተከል ዞኖች ካለው የተለየ አለመሆኑን በመጥቀስ ምርጫው መካሄድ ያለበት በተመሳሳይ ጊዜ መሆን አለበት ብለዋል። ምርጫ መራዘም ካለበት በክልሉ ሙሉ በሙሉ መራዘም አለበት እንጅ የተለዩ ቦታዎችን ምርጫ ማራዘም በመሰረታዊነት የምርጫውን ፍትሐዊነትና ሰላማዊነት የሚያጓድል ተግባር ነው ብለውታል። በክልሉ ምርጫ ይካሄድበታል ከተባለው አሶሳ ዞን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል አይደለም የሚሉት አመንቴ፣ አሶሳ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተንቃቅሰው ምርጫ መቀስቀስና የምርጫ ቅድመ ሥራዎችን መሥራት አልቻሉም ብለዋል። አሶሳ ላይ ያለውን የነባራዊ ሁኔታ አስቸጋሪነት በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን)፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ(ኢዜማ)፣ እናት ፓርቲና ሌሎችም ሆነው ለፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጉዳዩ ቀርቦ ውይይት እንደተደረገበት ጠቁመዋል።

በተደረገው ውይይት መሰርት የፖለቲካ ፓርቲዎች በዞኑ በነጻነት ተንቀሳቅሰው መሥራት የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባ ስምምነት ላይ ቢደረስም፣ እስካሁን ድረስ ተግባራዊ አለመሆኑን አመንቴ ጠቁመዋል። በዚህም ፖለቲካ ፓርቲዎች በክልሉ ያደረጉት የቅድመ ምርጫ ዝግጅት እጅግ ዝቅተኛ የሚባል መሆኑን ጠቁመዋል። በአሶሳ ዞን ምርጫ ቅስቀሳ ለማኬድ ፖለቲካ ፓርቲዎች መቸገራቸወን ከዚህ ቀደም ለአዲስ ማለዳ መግለጻቸው የሚታወስ ነው። ቦርዱ በገጠመው የቅድመ ዝግጅት እንቅፋትና የጸጥታ ችግር ለሌላ ጊዜ ያራዘማቸው አካባቢዎች ጉዳይ በሰኔ 14ቱ ምርጫ ላይ ተጽኖ ሊኖረው እንደሚችልም ተመላክቷል። እንደ አመንቴ ገለጻ ከሆነ፣ ምርጫው ኹለት ጊዜ መካሄዱ በመጀመሪያውም ይሁን በኹለተኛው ምርጫ ውጤት ላይ መጥፎ ጥላ እንደሚያጠላ ነው። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት በአንድ ክልል ውስጥ በተወሰኑ ቦታዎች ምርጫ ተደርጎ ውጤቱ መታወቁ በሌላ ጊዜ የሚደረገው ምርጫ ላይ ከፍተኛ የሀቀኝነት እና የጥርጣሬ መንፈስ እንደሚፈጥር በመግለጽ ነው።

ፓርቲው ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ አስገብቷል። ፓርቲው ለቦርዱ በጻፈው ደብዳቤ በቤኒሻንጉል ክልል ሦስት ዞኖች መኖራቸውን ጠቅሶ፣ በአንዱ ዞን ማለትም በአሶሳ ዞን ብቻ እንዲደረግና በኹለቱ ዞኖች እንዲራዘም መደረጉ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ ለሥነ ልቦና ጫና የሚዳርግ፣ እንዲሁም ፍትሐዊና ሰላማዊ የምርጫ ሂደቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ስለሚኖረው በክልሉ ሙሉ በሙሉ ምርጫው በአንድ ቀን እንዲካሄድ መጠየቁን አዲስ ማለዳ ለቦርዱ ከቀረበው ደብዳቤ መገንዘብ ችላለች።


ቅጽ 3 ቁጥር 134 ግንቦት 21 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here