ኢትዮጵያ በምርጥ ቡና ጣዕም የዓለምን ክብረ-ወሠን ሠበረች

0
1530

ኢትዮጵያ በዓለም ላይ እስካሁን በተደረገ የምርጥ ቡና ጣዕም ውድድር ተገኝቶ የማያውቅ ውጤት በማስመዝገብ የዓለምን የምርጥ ጣዕም ቡና ክብረ-ወሠን (ሪከርድ) መስበሯ ተገለጸ። በኢትዮጵያ ለኹለተኛ ጊዜ በተካሄደቀው የ‹ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ› የምርጥ ቡና ጣዕም ውድድር እስካሁን በዓለም ላይ ያልተመዘገበ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ሪከርድ መስበሯን ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ አስታውቋል። በዚህ የቡና ጣዕም ውድድር ላይ ከተመዘገቡት 1848 ተወዳዳሪዎች፣ 30 ቡናዎች ዓለም አቀፍ የውድድር መስፈርቱን አሟልተው ማለፋቸውን ፊድ ዘ ፊውቸር ኢትዮጵያ ቫሊዩ ቼይን አክቲቪቲ(Feed the Future Ethiopia Value Chain Activity) ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

30ዎቹ ቡናዎች በውድድሩ 87 ነጥብና ከዚያም በላይ በማምጣት አሸናፊ መሆናቸውን የፊድ ዘ ፊውቸር ኢትዮጵያ ቫሊዩ ቼይን አማካሪ ቅድስት ሙሉጌታ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል። እንዲሁም አምስት ቡናዎች ከ90 በላይ ውጤት በማስዘገብ ‹ፕሬዚደንሺያል አዋርድ› በመባል የሚታወቀውን የውድድሩን ከፍተኛ እውቅና ማግኘታቸው ተረጋግጧል። እስካሁን ድረስ በዓለም ላይ በተካሄዱት የምርጥ ቡና ጣዕም ውድድሮች ከ 87 በላይ ነጥብ በማምጣት 30 ቡና ያስመዘገበ አገር አለመኖሩን ቅድስት ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ የካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ አሸናፊ ቡናዎች በመጪው ሰኔ 30/2013 በ‹አሊያንስ ፎር ኮፊ ኤክሰለንስ› ድረ-ገጽ ላይ በቀጥታ በኢንተርኔት ግብይት ለ24 ሰዓታት በሚቆይ ጨረታ ለሽያጭ እንደሚቀርቡ ተገልጿል። ዓለም አቀፍ ጨረታውን ለመሳተፍ እስካሁን 137 ዓለም አቀፍ የቡና ገዥዎች በሰኔ 30/2013 በአልያንስ ፎር ኮሪያን ኤክሰለንስ ድረገጽ ላይ ለ24 ስዓታት በሚካሄደው ጨረታ ለመሳተፍ ተመዝግበዋል ተብሏል። ጨረታው የሚካሄድበት ጊዜ እስከሚደርስ ድረስ ተጨማሪ ዓለም አቀፍ ተጫራቾች ይመዘገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተመላክቷል።

ኢትዮጵያ ውስጥ የቡና ጣዕም ውድድር ለመጀመሪያያ ጊዜ የተካሄደው ባለፈው 2012 ሲሆን፣ የዘንድሮው ለኹለተኛ ጊዜ የተደረገ ነው። የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር፣ ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ ኢትዮጵያ በጋራ በመሆን በተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ ልማት የገንዘብ ድጋፍ የተካሄደ የምርጥ ቡና ጣዕም ውድድር ነው። ዘንድሮ በተካሄደው ኹለተኛው የቡና ውድድር ከተመዘገቡት 1848 ናሙና ቡናዎች፣ 150ዎቹ ለኹለተኛ ዙር ውድድር ማለፋቸውን ተከትሎ ከ150ዎቹ ቡናዎች ዓለም አቀፍ አሸናፊ የሆኑት ቡናዎች ተለይተዋል ነው የተባለው።

ባለፈው 2012 በተካሄደው በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የምርጥ ቡና ውድድር የተሳተፉት 1400 እንደነበሩ ቅድስት አስታወሰዋል። በመጀመሪያው ውድድር የመጀመሪያ ደረጃ አሸናፊ የሆነው ቡና በግልጽ ዓለም አቀፍ ጨረታ አንድ ኪሎ 407 ዶላር መሸጡ የሚታወስ ነው። ቀሪዎቹ ለመጨረሻ ጨረታ ቀርበው የነበሩ ምርጥ ቡናዎች እንደየተሰጣቸው ደረጃ በጨረታ ተሸጠው በአማካይ አንድ ኪሎ ግራም ቡና በ28 ዶላር ተሸጦ እንደነበር ተገልጿል። በዘንድሮው የጨረታ ውድድር አሸናፊ ሆነው የቀረቡ ቡናዎች ጥራት ከባለፈው ዓመት የተሻለ በመሆኑ በጨረታ ውድድሩ ከባለፈው ዓመት የተሻለ ዋጋ እንደሚገኝ ይጠበቃል።

የውድድሩ አሸናፊዎች አንደኛና ኹለተኛ ደረጃ የያዙት ከሲዳማ ክልል ሲሆን፣ ሶስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ከኦሮሚያ ክልል ነው። ከአራተኛ እስከ ዘጠነኛ ደረጃ አሁንም ከሲዳማ ክልል የተመረቱ ቡናዎች ሲሆኑ፣ 10ኛ ደረጃ የያዘው ከኦሮሚያ ክልል ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ የምርጥ ቡና ጣዕም ውድድር ከመጀመሩ በፊት አንድ ምርጥ የተባለ ቡና አንድ ኪሎ ከአምስት ዶላር ባልበለጠ ዋጋ ይሸጥ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፣ ውድድሩ በኢትዮጵያ መጀመሩ የአገሪቱ ቡና ምርጥ መሆኑን የዓለም አገራት እንዲያውቁት እድል ከፍቷል ተብሏል። የምርጥ ቡና ጣዕም ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ የተጀመረው በብራዚል ሲሆን፣ ዓላማውም ምርጥ ቡናዎች በጥሩ ዋጋ እንዲሸጡ ማድረግ ነበር። አሁን ላይ የቡና ውድድር ባለቤት መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው አልያንስ ፎር ኮፊ ኤክሰለንስ ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 134 ግንቦት 21 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here