ድርጅቱ በፖለቲካ አለመረጋጋት ለሚፈጠር የነዳጅ ዕጥረት አልጠየቅም አለ

0
644

• ለ15 ቀናት የሚሆን ቤንዚን እና ለ45 ቀናት የሚቆይ የነጭ ናፍጣ ክምችት አለ ተባለ

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በፖለቲካ አለመረጋጋት ለሚፈጠር የነዳጅ እጥረት ተጠያቂ እንደማይሆን አስታወቀ። የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ታደሰ ኃይለማርያም ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ድርጅታቸው ላለፉት ተከታታይ ቀናት አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያጋጠመው የነዳጅ ዕጥረት የነዳጅ አቅርቦቱ በሚገባባቸው መስመሮች በተከሰተ የፖለቲካ አለመረጋጋት መሆኑን ጠቅሰው ‹‹ይሁንና ድርጅታቸው በእንደዚህ ዓይነት የፖለቲካ አለመረጋጋት ለሚፈጠር የነዳጅ እጥረት ተጠያቂ አይሆንም›› ብለዋል።
ድርጅቱ ለ15 ቀናት የሚሆን ቤንዚን እና ለ45 ቀናት የሚቆይ የነጭ ናፍጣ ክምችት እንዳለው የገለጹት ሥራ አስኪያጁ የተፈጠረው ዕጥረት የመጠባበቂያ ክምችትን እንዲጠቀሙ አለማስገደዱንም ገልጸዋል። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ለሚፈጠሩ ችግሮችም በቂ ክምችት እንይዛለን ያሉት ታደሰ ‹‹ነገር ግን በየቦታው ችግር ይፈጠራል ብለን የያዝነውን ክምችት በየጊዜው እያወጣን አናባክንም›› ብለዋል። የነዳጅ እጥረት መባባሱንም ከሕገ ወጥነትና ነዳጁን በናረ ዋጋ ከመሸጥ ጋር እንደሚያያዝ የገለጹት ሥራ አስኪያጁ ‹‹የነበረንን የመጠባበቂያ ክምችት ብናወጣ ኖሮ እጥረቱ በእጥፍ ይስፋፋ ነበር›› ሲሉም አክለዋል።
በአውሮፓውያኑ 2016/17 ግምቱ 37 ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር የሆነ ሦስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነዳጅ በኢትዮጵያ ነዳጅ ኢንተርፕራይዝ አማካይነት ወደ አገር ውስጥ ገብቷል። ይህም የነዳጅ ዋጋ በ23 ነጥብ አንድ በመቶ፣ መጠኑ ደግሞ በ13 በመቶ ማደጉን ያሳያል። ከዚህ ውስጥ ከ363 ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ የሚሆነው ቤንዚን ነው። ምንም እንኳን አቅርቦቱ በ13 በመቶ ቢያድግም በአዲስ አበባ የቤንዚን እጥረት ሲታይ ቆይቷል።
የሌሎች አገሮችን ልምድ አንስተው የሚያብራሩት ዋና ሥራ አስኪያጁ እንደ ኬንያ ባሉ አገራት የነዳጅ መጠባበቂያ ክምችት የሚወጣው በፓርላማ ጸድቆ ነው ይላሉ። በቀጣይም የመጠባበቂያ ክምችቶችን በማሳደግ አስተማማኝ የነዳጅ አቅርቦት ለመፍጠር መታቀዱም ታውቋል።
ምንም እንኳን የነዳጅ አቅርቦት ችግር በተደጋጋሚ ቢስተዋልም የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በቀን አንድ ሚሊዮን 800 ሺሕ ቶን ነዳጅ ወደ አገር እንደሚያስገባ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 10 ጥር 11 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here