የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን 11 ቢሊዮን ብር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፈው የበጀት ዓመት መበደሩንና አጠቃላይ ዕዳው ወደ 29 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር መደረሱን አስታወቀ። እስካሁን ኮርፖሬሽኑ ወደ 781 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚሆነውን ዕዳውን የከፈለ ቢሆንም በጅምር ያሉትን ፕሮጀክቶች ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ብድር እንደሚያስፈልገው ብሔራዊ ባንክ አስታውቀ።
በአሁኑ ወቅት የአዋሽ – ኮምቦልቻ – ሃራ ገበያ የባቡር መሥመር እና የወልዲያ/ሃራ ገበያ – መቀሌ የባቡር መሥመር ግንባታዎችን በማካሔድ ላይ የሚገኘው ኮርፖሬሽኑ፥ በአሁኑ ወቅት በኹለት ምዕራፍ ተከፍሎ እየተገነባ ያለውን የአዋሽ–ኮምቦልቻ ወልዲያ(ሃራ ገበያ) የባቡር ፕሮጀክት የመጀመሪያው ምዕራፍ 95 በመቶ አጠናቋል።
የዛሬ አራት ዓመት የተጀመረው የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ወልዲያ(ሃራ ገበያ) ባቡር ፕሮጀክት 392 ኪሎ ሜትር ርዝመት ይሸፍናል። ነገር ግን የኹለተኛው ምዕራፍ ከኮምቦልቻ-ወልዲያ (ሃራ ገበያ) ማስገንቢያ የሚውለው ገንዘብ በወቅቱ ባለመገኘቱ የግንባታውን ሥራ በታቀደለት ጊዜ ለማከናወን ባለመቻሉ ፕሮጀክቱ ሊዘገይ ችሏል። የኹለቱም ምዕራፍ አዋሽ-ኮምቦልቻ-ወልዲያ(ሃራ ገበያ) የባቡር ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ 26 ባቡሮች የሚኖሩት ሲሆን፤ 20ዎቹ የዕቃ ቀሪዎቹ ደግሞ የሰው ማጓጓዣ ናቸው።
በሌላ በኩል፤ የወልዲያ/ሃራ ገበያ – መቀሌ የባቡር መሥመር ግንባታ ፕሮጀክት በመካሔድ ላይ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ መረጃ ያመለክታል። 216 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው ይህ የባቡር መሥመር የአማራ፣ ትግራይ እና አፋር ክልሎችን ያገናኛል። ወደ ጅቡቲ ወደብ በሚደረገው ጉዞ የሚወስደውን ጊዜ ከ50 በመቶ በላይ በመቀነስ የወጪና ገቢ ንግድን ያቀላጥፋል ተብሎ ይገመታል። ይሁን እንጂ ፕሮጀክቱ በገንዘብ እጥረት ምክንያት በሚገባው ልክ እየተካሄደ እንዳልሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።
እነዚህንና ሌሎች ፕሮጀክቶች ለመገንባት ብድር የሰጠው ንግድ ባንክ ባለፈው የበጀት ዓመት ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ወደ 37 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ያበደረ ሲሆን፥ ለአዲስ አበባ አስተዳደር ደግሞ 9 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በብድር መልክ ሰጥቷል።
ቅጽ 1 ቁጥር 10 ጥር 11 ቀን 2011