የብድር ስምምነቱ ተቃውሞ አስነሳ

0
579

ኢትዮጵያ ውስጥ በሚኖሩ ስደተኞች ምክንያት በኢትዮጵያ ምንም ዓይነት የምጣኔ ሀብት ጫና እንደማያስከትል በአዋጅ ቢደነገግም፤ ለስደተኞችና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ለማስፈፀም 83 ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት አገሪቷ መውሰዷ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተቃውሞ ገጠመው።
በኢትዮጵያ መንግሥት እና በዓለም ዐቀፍ የልማት ማኅበር መካከል የተደረገው የብድር ውል ስምምነት ጥር 6/2011 በስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ከተገለፀው የስደተኞች አያያዝ እና ክብካቤ ጋር የሚጣረስ ነው ሲሉ አባላት ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት ስደተኞች ከዓለም ዐቀፍ ለጋሾች በሚገኝ ገቢ እንደሚደገፉ የሚታወቅ ቢሆንም ስደተኞችን ማዕከል ያደረገ ብድር መፈፀሙ የማያግባባ ሐሳብ ነው ሲሉ የምክር ቤቱ አባላት ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። በገቢ፣ በበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርምሮ እንዲፀድቅ ለምክር ቤቱ የቀረበው የረቂቅ አዋጁ የውሳኔ ሐሳብ በርካታ አስተያየትና ጥያቄዎችን አስተናግዷል።
ከዓለም ዐቀፉ የልማት ማኅበር የተገኘው 83 ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዶላር የስድስት ዓመት እፎይታ ጊዜ ሲኖረው ከወለድ ነፃ እንደሆነና በ38 ዓመት ተከፍሎ የሚያልቅ የብድር ስምምነት እንደሆነ በረቂቅ አዋጁ ላይ ተገልጿል። ይህ ብድር በኹለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በኢንዱስትሪ መንደሮች ልማትና በሥራ ዕድል ፈጠራን ለማሳካት እና በኢትዮጵያ ተጠልለው ለሚኖሩ የተወሰነ ቁጥር ላላቸው ስደተኞች በምጣኔሀብት ተጠቃሚነት መርሃ ግብር ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚያግዝ ነው ተብሏል። ከዚህም በመነሳት በርካታ የምክር ቤት አባላት ሐሳባቸውን ለምክር ቤቱ አሰምተዋል።
በርካታ የሥራ አጥ ቁጥር ባለበት አገር ተበድረን ስደተኞችን እንዴት እናቋቁማለን የሚል ሐሳብ ከምክር ቤት አባሏ ገነት ተፈሪ ተሰምቷል። ሌላው የምክር ቤት አባል ተሾመ እሸቱ በበኩላቸው ‹‹የብድር ፖሊሲያችንን አይፃረርም ተብሎ የፀደቁት ብድሮች እስካሁን ልንመልሳቸው አልቻልንም፤ ጤናማ የብድር አካሄድ የለንም›› ብለዋል። ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ የብድሩን መፅደቅ በመደገፍ ከምክር ቤቱ ሐሳቦች ተነስተዋል። ብድሩ ያልነበረን ሀብት የሚፈጥር ነው በተጨማሪም ስደተኞች ተቀጥረው ሰርተው ሀብት የሚያፈሩበት ሁኔታ ስለሆነ ሊደገፍ ይገባል የሚሉ የድጋፍ ሐሳቦች ተነስተዋል። አሸናፊ ምቹ የተባሉ የምክር ቤት አባል ደግሞ ስደተኞች በጤና፣ በትምህርት እና በሌሎች የመሠረተ ልማት ዘርፎች በመንግሥት እየተደገፉ ነው ያሉት ስለዚህ ብድሩን እንደሌላ ድጋፍ መቁጠር እንችላለን ብለዋል።
ከምክር ቤቱ ለተነሱት አስተያየትና ጥያቄዎች የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ለምለም ሀድጉ ማብራሪያ ሰጥተውበታል። ‹‹ከብድር ውጭ ምን አማራጭ አለ?›› ሲሉ ምላሻቸውን የጀመሩት ለምለም አንደኛው አማራጭ እርዳታ እንደሆነ ገልፀው አሁንም 117 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ስምምነት ነው የተደረገው ብለዋል። ከዚህም ውስጥ 83 ነጥብ ሦስት ሚሊዮኑ ከወለድ ነፃ ብድር ሲሆን ቀሪው ደግሞ በእርዳታ መልክ የሚሰጥ እንደሆነ ተናግረዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ይህ የእርዳታ እና የብድር ስምምነት መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ለምለም ተናግረው ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል። የብድር ስምምነቱን በተመለከተ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳብ በሦስት ተቃውሞ ፣ በሦስት ድምጸ ታዕቅቦ በአብላጫ ድምጽ ፀድቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 10 ጥር 11 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here