በመተከል ዞን በተደጋጋሚ የሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን በዘላቂነት ለማስቆም እና የቀጣናውን ሰላም ለማረጋገጥ ከወራት በፊት ጀምሮ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውቋል። በተሠራው ሥራም ተፈናቃዮችን ወደ ከቀያቸው ለመመለስ የሚያስችል የሰላም ሁኔታ መፍጠሩን ገልጿል።
ከሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ያደረጉ የቡለን ወረዳ ተፈናቃዮች ደግሞ ወደ ቀያቸው ከመመለሳቸው በፊት በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ሊረጋገጥ እንደሚገባ ጠይቀዋል። የመተከል ዞን ኮማንድ ፓስት መሪ ጄኔራል አስራት ዴኔሮ እንደገለጹት ደግሞ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ መከላከያ ሠራዊት ከተለያዩ የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመኾን በርካታ ተግባራትን ሲሠራ ቆይቷል። ተፈናቃዮችን ወደቀያቸው ለመመለስ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል።
በቀጣናው ጫካ ገብተው የነበሩ ከ3ሺሕ በላይ የታጠቁ ግለሰቦችም ወደ ካምፕ ተመልሰው የተሐድሶ ሥልጠና እየወሰዱ ነው ብለዋል። የሚቀሩ ጥቂት ኀይሎችንም ጠንካራ ኦፕሬሽን በመሥራት ወደ ካምፕ እንዲመለሱ እየተሠራ መኾኑን አብራርተዋል።
ተፈናቃዮችም ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ የተለያዩ አጀንዳዎችን ከሚሰጡ አካላት ራሳቸውን በማራቅ ወደ ቀያቸው ለመመለስ ዝግጁ መኾን እንዳለባቸው ጄኔራል አስራት አሳስበዋል።
የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ ጋሹ ዱጋዝ በበኩላቸው ኮማንድ ፓስቱና የተፈናቃዮች መልሶ ማቋቋም የጋራ ግብረኀይል በመቀናጀት ዜጎች ወደቀያቸው እንዲመለሱ ሲሠራ መቆየቱን ተናግረዋል። ወደ ቀያቸው የሚመለሱ ነዋሪዎችም በዘላቂነት የማቋቋም ሥራም በሂደት ይሠራል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም ተፈናቃዮች የሚቆዩበት የድንኳን ተከላ ሥራ ተሠርቷል፣ የውኃ መያዣ ሮቶ ተገዝቷል፣ መጸዳጃ ቤት ተሠርቷል፣ የውኃ መስመር ተዘርግቷል፣ የጸጥታውን ሁኔታ ለማስተካከል ጥረት መደረጉን አማራ ቲቪ ዘግቧል፡፡
ከዞኑ የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን በቀጣይ ሳምንት ጀምሮ የመመለስ ሥራ ይሠራል፣ ተፈናቃዮች መልሰው ከተቋቋሙ በኋላ ለሚፈጠረው ችግርም ዞኑ ኃላፊነት ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን መግለጹም ተመላክቷል፡፡
ቅጽ 3 ቁጥር 136 ሠኔ 5 2013


