የዓባያ እርሻ ልማት ለወላይታ ዞን ተዘዋወረ

0
828

የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ በደቡብ ብሔር፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል በወላይታ ዞን የሚገኘውን የዓባያ እርሻ ልማት በ15.2 ሚሊዮን ብር ሽያጭ ለወላይታ ዞን አስተላለፈ፡፡ የሽያጭ ውል ስምምነቱ ሰኔ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. በኤጀንሲው መሰብሰቢያ አዳራሽ የተካሄደ ሲሆን፣ዞኑ የእርሻ ልማቱን ዋጋ ከፊርማው በፊት ሙሉ በሙሉ ገቢ ማድረጉ ታውቋል፡፡
የፊርማ ሥነ ሥርዓቱ በኤጀንሲው የሥርዓት ግንባታ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዝናቡ ይርጋ እና በወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ተወካይና የዞኑ ፋይናንስ መምሪያ ኃላፊ በደስታ ዳና መካከል ተካሂዷል፡፡
እንደ ዝናቡ ገለጻ፣ ዞኑ እርሻውን በተሻለ ሁኔታ በማልማትና ዘመናዊ የኮርፖሬት አስተዳደርና ፋይናንስ ሥርዓትን በመተግበር ለአካባቢው ኅብረተሰብ ተጨማሪ ሥራ ዕድል መፍጠርና ምርቱን ለውጭ ገበያ በማቅረብ አገርንም ጭምር ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡ ደስታ ዳና በበኩላቸው በዞኑ የሥራ ዕድል ለመፍጠር መታቀዱን ጠቅሰዋል፡፡
ዓባያ እርሻ ልማት በወላይታ ዞን አበላ ዓባያ ወረዳ፣ ዓባያ ጉርቾ ቀበሌ የሚገኝና ቀደም ሲል የሰሜን ኦሞ እርሻ ልማት ድርጅት ተብሎ ይታወቅ በነበረው ድርጅት ስር ይተዳደሩ ከነበሩ እርሻ ልማቶች አንዱ ነው፡፡ ጠቅላላ የመሬት ይዞታው 1,234.39 ሄክታር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 1,180 ሄክታሩ ሊታረስ የሚችል እንደሆነ ይታወቃል፡፡


ቅጽ 3 ቁጥር 136 ሠኔ 5 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here