በታላቁ የሕደሴ ግድብ ግንባታ ዓለም አቀፍ የውኃ ሕጎች ላይ የሚመክር 9ኛው አገር አቀፍ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጉባኤ በጎንደር ዩኒቨርስቲ ተካሂዷል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ድኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በጉባኤ መክፈቻ እንዳሉት የሕዳሴው ግድብ ለዘመናት ከተፈታተነን ድህነት ለመላቀቅ መንግሥትና ሕዝባችን በጋራ የጀመሩት የህልውናችን መገለጫ ነው።
ግድቡ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለተፋሰሱ አገራት ጭምር ዘመን ተሻጋሪ ፀጋ የሚያላብስ ታሪካዊ ክንዋኔ መሆኑን ተናግረዋል።
የታላቁ ሕደሴ ግድብ የሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው፣ “የሕደሴው ግድብ የአንድነታችንና የሉዓላዊነታችን መገለጫ የታሪካችን አሻራ ነው” ብለዋል።
የሕደሴው ግድብ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት መረጋገጥ የወቅቱ ጥያቄ ነው ያሉት ደግሞ የጎንደር ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር አስራት አፀደ ወይን ናቸው።
ለሁለት ቀን በቆየው ጉባኤ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ዓለም አቀፍ የውኃ ሕጎችን መሰረት ያደረጉ ሰባት ጥናታዊ ጽሁፎች በምሁራን ቀርበው ውይይት እንደተደረገባቸው ታውቋል።
ከጉባኤው ጎን ለጎን 3ኛውን ዙር የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሀ-ግብርን ታሳቢ ያደረገ የችግኝ ተከላ ስነስርዓት እንደሚካሄድ ተመላክቷል።
በጉባኤው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር፣ የሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባባሪያ ጽህፈት ቤት፣ ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የመጡ ምሁራን፣ አባምሳደሮችና የጎንደር ዩኒቨርስቲ አመራሮች ተሳትፈዋል።
ቅጽ 3 ቁጥር 136 ሠኔ 5 2013


