በሀዋሳ ከተማ ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ እንዳለ ተነገረ

0
806

በሀዋሳ ከተማ 85 ሄክታር መሬት ያለ ሥራ ታጥሮ መቆየቱንና ከፍተኛ የሆነ ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ መኖሩን የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።
የሀዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፣ በከተማዋ ለዓመታት ታጥረው የተቀመጡ ሰፋፊ መሬቶችና በሕገ-ወጥ መንገድ የተወረሩ መሬቶች መኖራቸውን አስገንዝበዋል።
በዙሪያው 12 የገጠር ቀበሌዎች መኖራቸውንና ይህም አርሶ አደሮች ለቤት መስሪያ ቦታ ፈላጊዎች ሲሸጡ መቆየታቸውን አስታውሰው፣ በዚህ ዓመት ይህን ሕገ-ወጥነትን በሚገባ ስንከላከል ነበር ብለዋል። በቦታው ካሉ ነባር አርሶ አደሮች በተጨማሪ ሌሎች ቤት እንዳይሠሩም ክልከላ ተደርጓል።
ታጥሮ በተቀመጡ ቦታዎች ላይ ባለሃብቶች ተጨባጭ ለውጥ የሚያሳይ ሥራ እንዲሰሩ የስድስት ወራት ጊዜ የተሰጣቸው ሲሆን፣ በዚህ ጊዜ አመርቂ ሥራ ማከናወን የተሳነቸውን ደግሞ መሬቱን ለመሬት ባንክ ገቢ እንዲደረጉ መወሰኑንም ጠቁመዋል። በቀጣይም ሕግ የማስከበር ሥራው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ምክትል ከንቲባው አረጋግጠዋል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ሐዋሳ ከተማ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሚኖሩባት ሲሆን፣ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እና ግንባታዎች ከሚከናወኑባቸው የአገራችን ከተሞች በቀዳሚነት የምትጠቀስ ናት።


ቅጽ 3 ቁጥር 136 ሠኔ 5 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here