የጤና ሚኒስቴር በትግራይ ክልል ከሰብዓዊ አጋሮች ጋር መሥራቱ ተገለጸ
የጤና ሚኒስቴር በትግራይ ክልል የጤና አገልግሎቶችን ለማጠናከርና ወደሥራ ያልተመለሱ የጤና ተቋማትን ለመመለስ ከኤጀንሲዎች፣ከትግራይ ክልል ጤና ቢሮ እና ከሰብዓዊና የልማት አጋሮች ጋር የሚያከናውኗቸዉ ሥራዎች እንዳሉ ተገለጸ፡፡
በክልሉ በአጠቃላይ ከሚገኙት ጤና ጣቢያዎች እና ሆስፒታሎች በአሁኑ ወቅት 46.5% የሚሆኑት አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ተደርጓል፡፡
በየጤና ተቋማቱ መድኃኒት እና የሕክምና መሳሪያ ለሟሟላት በተደረገው ጥረት የጤና ሚኒስቴር ከመድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ እንዲሁም ከሌሎች ተጠሪ ተቋማት ጋር በመሆን ግምቱ ከብር 3.8 ሚሊዮን በላይ የመድኃኒትና የግብአት ድጋፍ አድርጓል፡፡
ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እና ኤጀንሲዎች ለተለያዩ የፕሮግራም ማስፈጸሚያ የሚውል በድምሩ ብር 2 ሚሊዮን በጥሬ ገንዘብ እንዲተላለፍ ተደርጓል፡፡
በክልሉ ለተፈናቀሉ ወገኖች መሰረታዊ የጤና አገልግሎት በነጻ እንዲያገኙ እየተደረገ ሲሆን፣ ይህን ሥራ ለማጠናከርም ቀደም ብለው ከነበሩት በተጨማሪ በክልሉ የሚገኙ 80 ሐኪሞች፤25 ነርሶች እንዲሁም 15 አዋላጅ ነርሶች (በድምሩ 120 የጤና ባለሙያዎች) ቅጥር በጤና ሚኒስቴር ድጋፍ ተከናውኖ በሁሉም የተፈናቃይ ማዕከላት በመመደብ ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን፣ ከፍተኛ የተፈናቃይ ቁጥር ባለበት 17 መጠለያ መለስተኛ ክሊኒክ እንዲቋቋም ተደርጓል።
ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን አስፈላጊውን ህክምናና ድጋፍ መስጠት እንዲቻል በድምሩ 57 የአእምሮ ጤናና የሥነ-ልቦናና ማኅበራዊ ድጋፍ ሰጪ ባለሙያዎች በስድስት ከተሞች አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ ተብሏል፡፡
ቅጽ 3 ቁጥር 136 ሠኔ 5 2013


