ጌትነት ወርቁ ይባላሉ። የእናት ፓርቲ ዋና ጽኃፊ ናቸው። በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ ሆነው ፓርቲያቸውን ወክለው በወሎ አምባሰል ወረዳ ይወዳደራሉ። ስለ ምርጫው አጠቃላይ ሂደት፣ ስላጋጠሙ ችግሮችና ስለ ፓርቲያቸው እንቅስቃሴ ከአዲስ ማለዳው ቢኒያም ዓሊ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ስለ ፓርቲያችሁ ትንሽ ቢያስተዋውቁን?
እናት ፓርቲ አገር አቀፍ ፓርቲ ነው። በዋናነት ለኢትዮጵያ ይበጃሉ ተብለው የሚወጡ ፖሊሲዎችና ፍልስፍናዎች ከኢትዮጵያዊነት የተለዩ፣ ከራሳችን የሚነጥሉን እንጂ ከራሳችን የሚያስታርቁን አይደሉም። መጀመሪያ የኮሚኒዝምን ጫማ ሞከርን፤ እሱ ሲሰፋን የሶሻሊስቱን ጎራ ተቀላቀልን። እሱም ቅጥያ ስለነበር አልሆን ሲለን አብዮታዊ ዲሞክራሲ አልን፤ ይህም ሰፋን። በተለይ ከሶሻሊስቱ ጎራ ቀድተን ያመጣነው አገሪቱ በደም ጎርፍ እንድትታጠብ ምክንያት ሆነ። ማንም የውጭ ጠላት ሳይወር ኢትዮጵያውያን ራሳቸው ራሳቸውን አጥፍተዋል። በተለይ ያ ትውልድ የሚባለው፣ ለአገር ብዙ ሊሠራ የሚችለው፣ እርስ በርሱ ተከፋፍሎ በፓርቲና በግል ውግንና መገዳደሉ በጣም የሚያሳዝን ነው። የእነሱ መጠፋፋት አሁን ላለንበት ሁኔታ በብዙ መንገድ ዳርጎናል ማለት ይቻላል።
ከባዱን ጊዜ ስላሳለፍን ከዚህ በኋላ ከውጭ የምናመጣቸው ፍልስፍናዎች እንደሚጠቅሙን ተገምግመው ካልሆነ በቀር ተግባራዊ መደረግ የለባቸውም። በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰማይ ስር ከራሳችን የሚወጣ ፍልስፍና መሆን አለበት። ፓርቲያችን ይህን የመሰለ አመለካከት ያለው፣ የውህድ ወግ አጥባቂ ፍልስፍናን የሚከተል ነው። ከ3ሺሕ አመታት በላይ አገራችን ያዳበረቻቸው የዕውቀት፣ የፍልስፍናና በተለያየ ዘርፍ ውስጥ ያሉ የዳበሩ እሴቶች አሉን። ያሉን እሴቶቻችን ተጠብቀው ከውጭ ደግሞ ስልጣኔ ያመጣቸው መልካም እሴቶች ተጣምረው መልካም ኢትዮጵያን ማምጣት ይቻላል ብሎ የሚያምን ፓርቲ ነው። 605 ዕጩዎችን አስመዝግቧል። ከእነዚህ ውስጥ 65ቱ እሳት የላሱ ሴቶች ናቸው።
እስካሁን ያለውን የምርጫ ሂደት እንዴት ትመለከቱታላችሁ?
የምርጫውን ሂደት በኹለት መክፈል ጥሩ ይመስለኛል። አንዱ ከፓርቲዎችና ከዕጩዎች ምዝገባ ጋር በተገናኘ ስላለፈው ሂደት የምናይበት ሲሆን፣ ለእኛ ጊዜው ከማጠሩ ውጭ ያን ያህል ጫና አልነበረብንም። የገንዘብ እጥረት ከመጀመሪያውም የነበረ ቢሆንም፣ ገዢው ፓርቲ ሁሉንም ነገር ይዞ በሚዘውርበት እኛን በመሰለ አገር ይህ አይገርምም። ብዙው ነገር በገንዘብና በታዋቂነት ነው የሚሰራው። እኛ ደግሞ አዋቂዎችን እንጂ ታዋቂዎችን ይዘን አልመጣንም። ሚዲያው ስለማያውቀን፣ ሕዝብም እንዲቀበለን እኛን የሚሰማበት ሁኔታ ስላልተመቻቸ ለማስተዋወቅ ከባድ ነበር። ሰው ብዙ ዕጩ አስመዝግባችኋል ቢለንም እኛ እነሱን ለማስመዝገብ የሆነውን ስለምናውቀው አያስደስተንም። እኛ ለራሳችንና ለበጎ ፈቃደኞቻችን አንደኛ ነን ብለን ነው የምንነግራቸው። ከጊዜ ጥበቱ ባሻገር የፖለቲካ ሥራን ቁጭ ብሎ መሥራት አይቻልም ነበር። ምርጫ ቦርድ ያስቀመጣቸውን መስፈርቶች አሟልቶ ለመመዝገብ በጣም ከባድ ነበር። አጠቃላይ ሂደቱ ትልቅ ራስምታት ነበር። የምርጫ ቅስቀሳን በተመለከተ ለመቀረጽ በጣም የተደራጀ ስቱዲዮ ይፈልጋል። እኛ ይህን መሰል አቅም የለንም። እንዲህ አይነት ነገሮችን እያሟላን ነው ሁሉንም ሂደት እያለፍን የመጣነው።
የቅርብ ጊዜውን ከተመለከትን ሂደቱን በጣም የሚያከብደው ከቅስቀሳ ጋር በተገኛኘ የገጠመን ችግር ነው። እኛ ዕጩ ያደረግናቸው አካባቢያዊ ተጽዕኗቸው ከፍ ያሉትን፣ በባህሪያቸውም የታወቁትን ስለሆነ፣ እንዲሁም እኛም የቅንነት ፖለቲካን ስለምናራምድ ነበር እነሱን ወክለን ለቅስቀሳ የላክናቸው። እነሱ ሲታወቁና በፊት የሞከርነው መዋቅር መሥራት ሲጀምር እንዲሁም ፓርቲውም ሲታወቅ በእኛ መደንገጥ ጀመሩ። ከዛ በኋላ የመንግሥት ካድሬዎች የሚሰሩት ተወርቶ የሚያልቅ አይደለም። ለአንዲት ወንበር ብሎ እንዴት ሰው አብሮ አደጉን ይጎዳል? በተለይ ገጠር አካባቢ ሽጉጥ ይተኩሳሉ፤ ክላሽ እየተጠቀሙ ያስፈራራሉ። በጣም የሚያሳዝነው አብሮት ኖሮ በማኅበራዊ ጉዳይ የሚያገኘውን ወንድሙን ቅድሚያ ያባብላል፤ እምቢ ካለ ያስፈራራል። ለምሳሌ፣ አንድ ዕጩአችንን በሽጉጥ ስተውታል። ሌላ ሴት ዕጩአችን አባብለዋት እምቢ ስትል የዕጩ ማስመዝገቢያ ቀን እስኪያልቅ ጠብቀው ከሥራዋ እንድትለቅ አስመርጠዋት ነበር። የምትሠራበት ግብረ-ሰናይ ድርጅት ሠራተኞቹ የፖሊተካ ተሳትፎ እንዳይኖራቸው ስለሚያዝ እኛ ዕጩ መቀየር የማንችልበትን ጊዜ ጠብቀው ከፓርቲያችን እንድትወጣ አስደርገዋል። የኑሮው ሁኔታ ያለሥራ መቀመጥ ስለማያስችል እኛ ለምርጫ ቦርድ ሰርዟት ብለን ደብዳቤ ጽፈን በቦታው ያለምንም ዕጩ እንድንቀር አድርገውናል። ይህ ከአዲስ አበባ በተራቀ ቁጥር ነገሮች ምን ያህል እየከበዱ እንደሚሄዱ ያሳያል።
ክፋታቸው ምን ያህል እንደሆነ ለማሳየት ሰሜን ወሎ የገጠመንን በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል። ዕጩአችን መወዳደሩን አለቃው ሲያውቅ በቦታው ሌላ ሰው ተካበት። ያለምንም ማስጠንቀቂያ ደሞዝ ማግኘት ካቆመ ሦስት ወር ሆኖታል። በሌላ በኩል በኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ምርጫ መደረግ አልነበረበትም። በዚህ ጉዳይ ማውራትም ሆነ መከራከር ይቻላል፤ ነገር ግን ጊዜ ስለሚፈልግ ለጊዜው መተዉ ይሻላል። ስልክ ሲደወልልን የሥራ ሪፖርት ለመቀበል ሳይሆን ማን ታስሮ፣ ማን ተተኩሶበት ይሆን? እያልን ነው የምንጠብቀው። ምዕራብ ጎጃም ፍኖተ- ሰላም ውስጥ አንድ የእኛ ዕጩ ሲቀሰቅስ ውሎ ሲመለስ ወንድሙንና አባቱን አሥረው ጠብቀውታል። ዕጩን ማሰር እንደማይችሉ ስላወቁ ቤተሰብን አሥረው እያሰቃዩ የክፋታቸውን ጥግ ያሳያሉ። በአጠቃላይ አማራ ክልል ሶስት ዞኖች ደቡብ ጎንደር፣ ምዕራብ ጎጃምና አዊ ዞኖች ምን እንደሚሆን ለመተንበይ ይከብዳል።
ከሥራ ገበታቸው ስለሚባረሩት በተመለከተ የምርጫ አዋጁ የመንግስት ሠራተኞች ያለደሞዝ ፈቃድ ወጥተው እንዲቀሰቅሱ ያዛል። ይህ ግን በሁሉም ፓርቲዎች በተመሳሳይ እየተፈጸመ አይደለም። ይህን እንዴት ያዩታል?
ነገሮች እየተዳሉ ነው የሚፈጸሙት። እኛ የገጠመንን ሂደት ለምርጫ ቦርድ ሪፖርት አድርገን ነበር። እነሱ ከሕግ ውጭ እንደሆነ በመጥቀስ ወደ ሥራ ገበታው እንዲመለስ ወይም መቀስቀስ ከፈለገ በአዋጁ መሰረት ለ3 ወር ያለደሞዝ ፈቃድ መውጣት ይችላል ብለው ነበር። ይህ ቢሆንም ግን ኃላፊው መቀበል አልፈለገም። በእዚህ ምክንያት 5 ቤተሰብ የሚያስተዳድር ሰው ተቸግሮ ነው ያለው። እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች በጎጥ የሚያምኑ ናቸው። ሰው ተወልዶ ባደገበት እንዲህ ከተደረገ በማይታወቁበት፣ ፀጉረ ልውጥ በሚባሉበት ቦታ ዕጩዎች ምን ሊደረጉ እንደሚችሉ መገመት ከባድ ነው። እኔ የማይገባኝ ሰው ሰው ላይ እንዴት አንደዚህ መጨከን መቻሉ ነው።
አጠቃላይ የክርክር ሂደቱን እንዴት ትገመግሙታላችሁ?
ክርክሩ በጣም ዘግይቶ ነው የተጀመረው። ለምርጫው መፋዘዝ አንዱ ምክንያት እሱ ነው። ከ3 እና 4 ወር ቀደም ብሎ ቅስቀሳ ሲጀመር ጀምሮ ቢሆን ከነግድፈቱም ቢሆን ጥሩ ነበር። የክርክሩን ጭብጥ በተመለከተ እንዳይያዙ የሚፈለጉ ጉዳዮች ነበሩ። በተለይ አሁን መናገር በማንፈልጋቸው 4 ነጥቦች እንዳንከራከርባቸው አድርገዋል። የሚቆሰቁሱን ከሆነ ርዕሰ ጉዳዮቹን ይፋ የምናደርጋቸው ይሆናል። ለጊዜው ማማረር ስለማንፈልግ ዝርዝሩን ከማሳወቅ ተቆጥበናል። ለምሳሌ፣ በአዲስ አበባ ጉዳይ፣ ባሕል፣ እሴትና ኃይማኖት ብለን በነዚህ ጉዳዮች ኢትዮጵያውያን ልንወያይና ልናውቅ ይገባል ብለን ብናስይዝም ተቀባይነት አላገኘም። በ10 ጉዳዮች እንከራከር ብንልም ቋንቋን ጨምሮ 4ቱ ነበሩበት። ኹለት በትግል እንዲገባ ብናደርግም 4ቱ ላይ ለመወያየት እንኳን ፈቃደኛ አይደሉም።
ከርዕስ መረጣው ባሻገር ሰው ባለበት አንወዳደርም ሲሉ ነበር። ሕዝብን ምረጠን የሚል ፓርቲ ሕዝብ ፊት አዳራሽ ውስጥ አንወዳደርም ማለቱ ራሱን የቻለ ችግር ነበር። ሰው ቢኖር የተዘጋጀ የበለጠ ይጠቀማል፤ ያልተዘጋጀ ግን የሚናገረው ሊጠፋበት ይችላል። ለዚህ ብለን እሺ ሰው ይቀነስ ብንልም ገዢው ፓርቲ አንድም ሰው ከተገኘ አልገኝም አለ። በዚህ ምክንያት ሁሉም ክርክሮች ስቱዲዮ ውስጥ ነው የሚቀረጹት። ኢሳት በትምህርት ፖሊሲና በኢኮኖሚ ዙሪያ ትንሽ ሰው በተገኘበት ያዘጋጀው ላይ ብልጽግና አልተገኘም። ኢሳትን የመሳሰሉ ሌሎች ተቋማት ባዘጋጁት ክርክርም ሰው ካለና የማይፈቅዱት ርዕስ ከሆነ መከራከሪያ ቦታው ሰበብ ፈጥረው አይመጡም። ለምሳሌ፣ በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ መከራከር አይፈልጉም። ይህ ሂደት በኋላ ላይ ብልጽግና ከሌለ ክርክር የለም የሚል ነገር ይዞ መጣ። ለምሳሌ፣ በኢትዮ ኤፍ ኤም ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ላይ የተጠሩ 4 ፓርቲዎች ከብልጽግና በስተቀር ቢገኙም ወደሌላ ቀን እንዲሸጋገር ተደርጓል። በፋና ቴሌቪዥን ደግሞ በከተሜነትና መሠረተ ልማት ጉዳይ ብልጽግና እስኪገኝ 3 ጊዜ ፕሮግራም ቀይረዋል። ባሕል፣ እሴትና እምነት ላይ እንድንከራከር እኛ አጀንዳ አስይዘን ነበር። እነሱ ግን እምነት እንዳይነካ ብለው ባሕልና ቱሪዝም ላይ እንዲገደብ አድርገው ለማክሰኞ ጠዋት ቀጠሮ ተይዞ ነበር። በጉዳዩ እውቀት ያለው ተከራካሪያችንን ከወልዲያ ዩኒቨርስቲ በአውሮፕላን እንዲመጣ አድርገን በሰዓቱ ቢገኝም የብልጽግና ተከራካሪ አልተገኘም ነበር። ክርክሩ ስለተበተነ ተወካያችን እንዲመለስ በመደረጉ እድሉ አመለጠን። አርብ ኢቢሲ ላይ በነበረ ክርክር ላይም ተወካያችን ከደብረ ታቦር እንዲመጣ አድርገን በድጋሚ የብልጽግና ተወካዮች ሳይገኙ ቀርተዋል። ዶክተር ሂሩት ስላልተገኘች ተብሎ ስቱዲዮ እንዳይገባ እንኳን ተከልክሎ የነበረ ቢሆንም፣ በጭቅጭቅ ተገብቶ ለማስረጃ ፎቶ ተነስተው ተለያይተዋል። ቅሬታችንን በጽሁፍ ጭምር ብናቀርብም እስካሁን ድረስ ታጥፎ አልተካሄደም። ይህን የመሳሰሉ ነገሮችን ስናይ ምን ማድረግ እንደሚፈልጉ አይገባንም።
በእኛ በኩል ግን ሃሳባችንን በተቻለን መጠን ባገኘነው አጋጣሚ ለመሸጥ እየሞከርን ነው። ብልጽግና መጀመሪያ አልገኝም ብሎ እንዳልነበር በኋላ ላይ በአንድ ጣቢያ 3 ክርክሮች ላይ ብቻ ነው የምሳተፈው ብሏል። በዚህም ትችት ሲደርስበት ሁሉም ላይ እገኛለሁ ብሏል። ለወደፊቱ በዝርዝር የሚወጣ ቢሆንም፣ ሕዝብ እንዲያውቀው ክርክር ላይ ቤተ-መንግሥት እየደወሉ ይጠይቃሉ። 30 ዓመት የኖረ ፓርቲ ስሙን ቀይሮ ቢመጣም እንዴት ራሱን ችሎ የሚከራከር አንድ ሰው ያጣል። ትልቅ ኃላፊነት ላይ ያለ ሰው በትንሽ ጉዳይ የበላዩ ጋር ሲደውል ምን ይባላል።
ከአቅም ጋር በተገናኘ አንዳንድ ፓርቲዎች የውጭ ድጋፍ አላቸው ሲባል ይሰማል። በዚህ ጉዳይ ላይ አቋማችሁ ምንድን ነው?
ይህን በተመለከተ እውነታውን ጊዜ ይመልሰዋል። ስለእኛ ፓርቲ የማውቀው ከፍልስፍናው ጀምሮ ሁሉ ነገር የራሳችን እንዲሆን ነው የምንፈልገው። ራሳችን አቡክተን ራሳችን መጋገር አለብን ብለን ነው የምናምነው። 101 ከመቶ የማምነው እኛ የማንንም ጣልቃ ገብነት የምንቀበልበት የሞራል ስብስብ ያለን አይደለንም። የትም ያለ ሰው ገንዘብ ሊሰጥህ ይችል ይሆናል እንጂ ጉዳይህ ውስጥ የመግባት እድል አይኖረውም። በተለይ ለውጭ ጣልቃገብነት የሚጋብዝ ምንም አይነት ተሳትፎ እንዲኖር አንፈቅድም። ከዓለም አቀፉ ዲፕሎማቲክ ማሕበረሰብ ጋር በተደጋጋሚ ተገናኝተን ተነጋግረናል። ስለ አገራችን ሁኔታ እንድንወያይ እድል ስለሰጡን ልናመሰግናቸው እንወዳለን። ባገኘነው እድል ፓርቲንና ሕዝብን ለይተው እንዲመለከቱ፣ መንግሥት አቅም በሚያጥረው በኩል እገዛ እንዲደረግለት ለማስገንዘብ ሞክረናል። ይህ ቢሆንም ግን አንዳንድ ጊዜ ማጣፈጫ ትሆናለህ።
የፓርቲዎች ገቢ ከየት እንደሚመጣ የማን ሂሳብ ውስጥ እንደሚገባ መታወቅ አለበት። ጋዜጠኞች ይህን ጉዳይ አጣርታችሁ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ አለባችሁ። የገቢ ምንጭ ብቻ ሳይሆን ሃሳባቸውን ከየት እንደሚያመጡም ሕዝብ ማወቅ አለበት። ለምሳሌ፣ በቅርብ ጊዜ ሃሳቡን የቀየረ ፓርቲ አለ። ከዚህ በፊት ሲያራምዱት የነበረውን አቋም አሁን ምርጫ መዳረሻ ላይ የሚቀይሩበት ምክንያት መታወቅ አለበት። ሰው እጁ ተጠምዝዞ ካልሆነ በስተቀር በ1 ወር ውስጥ መርሁን እንዴት ይቀይራል።
ከውጭ ጉዳይ ጋር በተገናኘ ከምዕራባውያን ጋር ያለንን ግንኙነት እንዴት ታዩታላችሁ?
በእኛ እምነት ሉዓላዊነትም ጥገኝነትም አለ። ሉዓላዊነታችን የቱ ድረስ ነው ብለን መጠየቁና መረዳቱ አስፈላጊ ነው። አሜሪካ ሪዞሊውሽን ስታወጣ አልነበረም ሉዓላዊነት ትዝ ሊለን የሚገባው። ወለጋ፣ ቤኒሻንጉልና ማይካድራ ሰው ሲሞትና እህታችን ስትደፈር ነው ሉዓላዊነታችን ሊነሳ የሚገባው። በአንድ ጀንበር ከተማ ሲወድም ሉዓላዊነት መደፈር እንደሆነ ያለን ግንዛቤ የተዛባ ነው። ሉዓላዊነት አሜሪካ ስትወር ወይም ሱዳን ድንበር አልፋ መሬታችንን ስትይዝ ብቻ አይደለም። በፓርቲያችን ፍልስፍና ሉዓላዊነት ከሰው ጋር የሚገናኝ ነው። አይደለም ኢትዮጵያዊ አፍሪካዊም ሆነ ማንኛውም ሰው ሲገደልና ማሕበረሰብ ሲደፈር ነው ሉዓላዊነት መነሳት ያለበት።
በቅርብ እንዳየነው ራሳችን ተፈትነን በወደቅንበት ዲፕሎማሲ ያመጣነውን ችግር ከሉዓላዊነት ጋር እያጣበቅን በተለያየ መንገድ ለጥጠን እያየነው ይመስላል። በዚህ ሰበብ ሰልፍ ያስወጣሉ፤ ሌላም ሌላም ይናገራሉ። በዚህ ጉዳይ መንግሥት ከምዕራባውያን ጋር ያለውን የዲፕሎማሲ ሂደት ያያዘበት መንገድ ትክክል አይመስለንም። ‹የነቀዘ ስንዴና ዋሽንግተን አልሄድም ብሄድ አድዋ ነው› የሚሉ ባላዋቂነት የሚነገሩ ቃላት ናቸው። የቤት ሥራን ለመወጣት መሞከር እንጂ ከነዚህ አካላት ጋር አተካራ መግባት ተገቢ አይደለም። ለምሳሌ፣ የአሜሪካ መንግሥት በመደበኛው ስርዓት በቀረበለት መሰረት አይደለም ማዕቀብ የጣለው። ሎቢስቶችን ተጠቅመው ይህን ማስደረግ ሲችሉ የእኛ አምባሳደሮች ግን በሚዲያ ቀርበው ማስረዳትና በአካል ተገኝተው መከራከርም ባለመቻላቸው ነው ይህ የሆነው።
ከረባትና ሱፉን አሳምሮ የሚቀመጠው ያ ሁሉ አምባሳደር ምንድነው ስራው? ለምሳሌ ትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ በጣም ያሳዝናል። በታሪክ መለስ ብለን ነገ ስናየው ልብ የሚነካ የምናፍርበት ነገር ነው። በእርዳታ በኩል ያሉትን ጅምሮችና እየሆነ ያለውን እንዴት ማስረዳት ያቅታል። በፈለጉት ጊዜ ቀጠሮ አሲይዘው ሊገቡ የሚችሉ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት ተብለው እንዴት እንዲህ እናፍራለን። ስለዚህ የአያያዝ ጉድለት አለበት ብለን እናምናለን። ይህ ቢሆንም ከነግብጽና ሱዳን ጋር ማኅበር ተቀምጠው እዛ የቀመሱት ጉሽ አስክሯቸው እኛ ላይ ሊያደርጉት ያሰቡት ምንም አይነት ነገር ቢኖር እኛ ኢትዮጵያውያን በፍጹም ልንታገሰው አይገባም። ለምሳሌ፣ በዓባይ ወንዝ ላይ የምንሠራቸውን ማንኛውንም አይት ሥራዎች ማንንም በማይጎዳ መልክ እንዲያወቁት አድርገን እንሠራለን እንነጋገራለን እንጂ ማንም አቁሙ ሊለን አይችልም። የግድቡ ግንባታ ዓድዋ 2 ነው። ለጭቁን ሕዝብ ነጻ የመውጣት ምሳሌ መሆኑን እናሳያለን ብለን በእኛ በኩል እናምናለን።
አሁን ከሚታየው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ምርጫው ፍትሃዊ ይሆናል ትላላችሁ? ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብስ እንዴት ይቀበለዋል ትላላችሁ?
በእኛ በኩል በጣም ተስፋ አድርገን ነው ወደ ምርጫው የገባነው። አሁን ላይ እያየናቸው ያሉ ነገሮች ግን እጅግ ያሳዝናሉ። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩም በተደጋጋሚ ለኢትዮጵያውያን ቃል ገብተው ነበር። አሁን ላይ ግን ዶ/ር አቢይ በቃላቸው እየተገኙ አይደለም። የታችኛው መዋቅር ከላይ ትዕዛዝ እየወሰደ የሚያደርገው ያስፈራል። ምርጫ ተከናውኖ በሰላማዊ መንገድ ስልጣን መሸጋገሩ ቀርቶ ሌላ ከዛ ያለፈ ድርጊት ሊከሰት ይችላል ነው ስጋታችን። ለምሳሌ፣ ቀደም ብዬ የጠቀስኳቸው ችግሮች በኋላ ምን ይፈጥራሉ የሚለው ያሳስበናል። የብልጽግና ቲሸርት የለበሰ ግለሰብ እንደፈለገ የሚያደርገውን ስናይ አሁን ያለው ሁኔታ በጣም ያስፈራል። ኃላፊነት እንደሚሰማው ዜጋ ምርጫው መደረግ አለበት ብለን እናምናለን። የዶ/ር አቢይ መንግስት ችግር አንዱ በኹለት እግሩ የቆመ መስሎ አሻጋሪ መሆኑ ነው። ይህን አንድ ዓመት ቆይተህ ከምርጫ በኋላ ትለቃለህ የተባለ ቢሆንም፣ የተከፈለ ልብ ያለው መንግስት ነው። አሁን ለገጠመን የዲፕሎማሲ ችግርም በሕጋዊ መንገድ የሚመሠረት መንግስት መኖሩ አገርን ይጠቅማል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ምርጫውን ትተው ከሚወጡ ይልቅ መኖራቸው ነው የሚጠቅመው። ሂደቱን የበለጠ ፍትሐዊ ያደርገው ነበር። እንደ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ምርጫ ቦርድና የፍትሕ ተቋማት፣ እንዲሁም ጥሩ ስም ባይኖረውም አፍሪካ ሕብረትን የመሳሰሉ ኖረው ሰላማዊ ፍትሐዊና ነጻ ምርጫ መደረጉን መገምገም ይኖርባቸዋል።
የምርጫ ቦርድ ተግባርን በተመለከተ የእስካሁኑን ሥራውን እንዴት አያችሁት?
ምርጫ ቦርድ ላይ ኹለት መልክ ነው ያለው። አንዱ የኃላፊዋ አስተዋፅኦ ነው። በጎውን በጎ ማለት የፓርቲያችን ፍልስፍና እንደመሆኑም እሳቸው ነገሮችን በተቻላቸው መጠን አድምጠው በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ለመስጠት የሚያደርጉት ጥረት ሊደነቅ ይገባል። በሌላ በኩል፣ ከአቅማቸው በላይ የሆኑ ተቋማዊ ማድረግ ያልቻሉት ጉዳይ አለ። ለምሳሌ፣ አንድ ዕጩ ሲታሰርብን ቀጥታ እሷ ጋር ነው የሚገባው። መረጃውን በመያዝ የመደራደር አቅሟን ተጠቅማ ነው ራሷ የምታስፈታቸው። ችግሩ ግን እዛው ቦታ ላይ በነጋታው ሌላ ዕጩ ይታሰራል። በግል ጥረቷ እንጂ ተቋሟ አግዟት ባለመስራቷ ችግሮች እንዳይደገሙ ትምህርት አይወሰድበትም። ተደጋጋሚ ሰቆቃ ውስጥ ናቸው ያሉት። የእኛ ዕጩ ቅዳሜና እሁድ ቀሰቀሳችሁ ተብለው ታስረው አስፈትተውልን በሚቀጥለው ቀን መልሰው ያስራሉ። መሪዋ በቅንነት ቢሠሩም ተቋማዊ ማድረግ ስላልቻሉ ነው ኹለት መልክ አለው ያልነው። የህወሓት እርሾም በጣም አስቸጋሪ ነው።
የምርጫው ውጤት ጋር በተገናኘ ፓርቲዎች ለመሸነፍም ዝግጁ ናቸው ይላሉ?
ሽንፈትን ለመቀበል የሚወስነው ሂደቱ ነው። ሌላው ይቅርና በሦስቱ የአማራ ክልል ዞኖች የሚመጣውን እንዴት እንቀበላለን የሚለውን ብናይ ለመወሰን አስቸጋሪ ነው። የእነሱ ጥረት ወጥተን እንዳንቀሰቅስ ነው። ብዙዎቹ እጩዎቻችን ያለደሞዝ ፈቃድ ወጥተው ነው እየቀሰቀሱ ያሉት። እኔ ፓርቲዬን ወክዬ የምናገረው ሽንፈት እኛን እንደማይመረን ነው። ምርጫ ሂደት እንደሆነ እናምናለን። ሂደቱ ላይ እንጂ ውጤቱ ላይ ያን ያህል አንጨነቅም። እኛ በተቻለን ሃሳባችንን ሸጠናል፤ ሕዝብ ይወስናል። ቢያንስ አሁን ካለው የተሻለ ትውልድ ይመጣል ብለን ስለምናስብ የሚያስጨንቀን የአገሪቱ እጣ ፋንታ ምን ይሆናል የሚለው ነው እንጂ፣ እኛ 4ኪሎ ሆነን ስለምንበላውና ስለምንጠጣው አይደለም። ከዚህ በኋላ በመበጣበጥና ድንጋይ በመወርወር ለውጥ ይመጣል ብለን አናምንም። ስለዚህ ሽንፈትን በፀጋ ለመቀበል ምንም ችግር የለብንም። ችግሩ ግን ሂደቱ አሳማኝ አለመሆኑ ነው። ከቤተ-መንግሥት ያሸበረቁ ቃላት እየተለቀቁ በተቃራኒው ታች ያለው መዋቅር ጃስ እየተባለ እጩዎቻችንን እንደበግ ሲያስሯቸው ይውላሉ። ሂደቱ ትክክል ካልሆነ ሁሉም ውጤቱን ለመቀበል የሚያስቸግረው ይመስለኛል። የእኔ ጥያቄ ብልጽግና ቢሸነፍ አምኖ ይቀበላል ወይ? የሚለው ነው።
ከሌሎች ፓርቲዎች የሚለያችሁ ዋናዋና ነገር ምንድን ነው?
ኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ በሴራ ፖለቲካ ውስጥ ተተብትቦ ያለፈ የፖለቲካ ምህዳር ነው ያላት። የሴራው ፖለቲካ ጸድቶ ቅኖች ወደፊት መምጣት አለባቸው ብለን ማመናችን ከሌሎች የሚለየን አንዱ ጉዳይ ነው። ሌላው የእኛ ፍልስፍና ሰውነት ላይ ማተኮሩ ነው። በዘውግ፣ በቋንቋ ሳንለይ እንዳባቶቻችን ሰው በሰውነቱ እንዲከበር ነው የእኛ ፍልስፍና። ቀደምት ሊቃውንት ጊዜያቸውን ያጠፉ የነበሩት በመላው ዓለም ባለ ሰው ላይ ነው። በሌላ በኩል ከምዕራባውያን እያመጣን የምንለጥፋቸው ፖሊሲዎችና ፍልስፍናዎች በጣም ዋጋ አስከፍለውናል ብለን ስለምናምን ፍልስፍናዎቻችን ኢትዮጵያዊ መሆን አለባቸው ብለን ማመናችን ከሌሎች ይለየናል። ለምሳሌ፣ አሁን አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ብለው እንደሚያታልሉን አይደለም። በሁሉም ዘርፍ በቂ እውቀት ስለነበረን እኛ እሱን እንድንጠቀም ነው ፍላጎታችን። ይህ ባለመሆኑ ከራሱ የተነጠለ ትውልድ አፍርተናል ብለን እናምናለን። በዚህ ምክንያት ከትውልዱ የሚጠበቅ ዝቅተኛው ስነምግባር ጠፍቷል። ለዚህ ማስረጃ ባለስልጣናት የሚናገሩትን መስማቱ በቂ ነው።
እንደቀድሞው የፍረጃ ፖለቲካ፣ እነ እገሌ ፓርቲ የዚህኛው ብሔርና ኃይማኖት ተከታይ ናቸው እየተባለ በእናንተም ላይ ስለመቀስቀሱ ምን ትላላችሁ?
ይህ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሾተላይ አንዱ መገለጫ ነው። ፓርቲያችን በሚያሳዝን ሁኔታ የዚህ ኃይማኖት ተከታይ የሚበዙበት ተብሎ ነበር። በኋላ የግለሰብ ተደርጎ፣ ቆይቶ ደግሞ የብልጽግና ነው ተብሎ ነበር። ይህን ብሎ የከሰሰ ግለሰብና ድርጅት መልሶ እነዚህ የሉበትም ብሎ እርስበርሱ የሚጣረስ ነገር ይናገራል። እኛ እንዲህ በተባለ ቁጥር ሳይሆን ተገቢ ጥያቄ ሲመጣ ተገቢውን መልስ እየሰጠን ለወደፊቱም እየተዘጋጀን ነው። እባካችሁ ተገኙልን ብለን የላክነውን አንድ ደብዳቤ ተጠቅመው በማይሆን መንገድ በፎቶሾፕ ሰርተው በሚያሳዝን መልኩ አሰራጭተውታል።
በፖለቲካው አለም ፍጹም ነን አትንኩን ባይባልም፣ ስህተት ካለ ብዙ መስማት የምንችል እንደሆንን አውቃለሁ። አሁን ያለው ትውልድ ደርሶ የሚመለስ አይደለም። ነካክተን ልንመለስ ሳይሆን የመጣነው ልናደርግ ነው። ሩቅ ከመሄዳችን በፊት ያጠፉ ካሉ ኑ ብለን ለማስተካከል እንችላለን። በአጠቃላይ እኛ ፓርቲ ውስጥ ከአመራሮቹ ጀምሮ የአባላቱን ዘር ምን እንደሆነ አናውቅም። የተለያየ ቋንቋ ቢናገሩም ዘራቸውን ቀርቶ የተወለዱበትን አካባቢና የመጡበትንም እንኳን አንጠይቅም። ዘር ብቻ ሳይሆን እኛ ጋር ኃይማኖትም አይጠየቅም።
ቅጽ 3 ቁጥር 136 ሠኔ 5 2013



