“አንድ ዓመት የምርመራ ጊዜ ቢሰጣቸውም የሚያመጡት አዲስ ነገር የለም“ ኤርሚያስ ጠቅል አመልጋ

0
805

የቀድሞ የአክሰስ ሪል ስቴት ሥራ አስኪያጅ ኤርሚያስ ጠቅል ከኢፔሪያል ሆቴል ሽያጭ ጋር በተያያዘ ክስ ተመስርቶባችዋል። ተጠርጣሪው በ2003 ከኢፔሪያል ሆቴል ሽያጭ ጋር በተያያዘ የቀድሞ የሚቴክ ዋና ዳይሬክተር ክንፈ ዳኘውን (ሜጀር ጄነራል) ጨምሮ ከሌሎች የኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመመሳጠር ሆቴሉን በ72 ሚሊዮን ብር የተጋነነ ሒሳብ እንዲገዛ አድርገዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
ለሆቴሉ ግዢ ምን ያህል ብር ወጪ ሊሆንበት ይችላል የሚለውን በባለሙያ አስመረምራለሁ ያለው ፖሊስ ታክስን ጨምሮ ከ51 ሚሊዮን ብር በላይ ሆቴሉ እንደማያወጣም አረጋግጫልሁ ሲል ለችሎቱ አስረድቷል። በዚህም ምክንያት ተጠርጣሪው መንግሥት ማግኘት ከሚገባው ጥቅም 21 ሚሊዮን ብር አሳጥተዋል ሲል ገልጧል። ተጠርጣሪው በበኩላቸው ‹‹የሆቴሉ ግዢ ላይ በግለሰብ ደረጃ ያደረኩት ምንም ነገር የለም። በወቅቱ የአክሰስ ሪል ስቴት ሥራ አስኪያጅ የነበረኩ ሲሆን ከአምስት በመቶ ያነሰ ድርሻም ነው የነበረኝ ሲሉ ገልፀዋል። በዚህ ጉዳይ ላይም በተደጋጋሚ በሕግ አካል ጥያቄ ቀርቦብኛል ያሉት ተጠርጣሪው ከዚም በኋላ አንድ ዓመት የምርመራ ጊዜ ቢሰጣቸውም የሚያመጡት አዲስ ነገር የለም›› ብለዋል ። የሆነ ሰው ላይ መስክር እየተባለኩኝ ነው ያለሁት የሚሉት ኤርሚያስ ‹‹በማንም ላይ የምመሰክረው ምንም ነገር የለም›› ሲሉ ለችሎቱ በምሬት አስረድተዋል።
በተለይም ተጠርጣሪው ከግዢው ጋር በተያያዘ የቀድሞ የሆቴሉ ባለቤት ከነበሩት ጸጋዬ አስፋው ጋር በ2003 በ47 ሚሊዮን ብር ሆቴሉን ገዝቶ ነገር ግን ክፍያውን ሙሉ ለሙሉ ከፍሎ ሳይጨርስ ስምና ንብረቱን ወደ አክሰስ ሪል እስቴት ሳያዞርና የሦስተኛ ወገን ጥያቄ ያለበትን ሆቴል በአንድ ድርድር ከኃላፊዎቹ ጋር በመመሳጠር በተጋነነ ዋጋ መሸጣቸውን ክሳቸው ያመለክታል።
ኤርሚያስ በበኩላቸው ‹እኔ የማስተዳድረው ድርጅት ከሆቴሉ ሕጋዊ ተወካይ ከሆኑት ጸጋዬ አስፋው ጋር የውል ስምምነት ነበረው። በመሃል ግን ሜቴክ ሆቴሉን የመግዛት ፍላጎት ስለነበረው ከኛ ጋር የነበራቸውን ውል አፍርሰው፤ አዲስ ውል ከሜቴክ ጋር ተዋውለዋል›› የሚል መከራከሪያ ለችሎቱ አቅርበዋል። ‹‹በዚህ ጉዳይ ላይም በምንም ሁኔታ ተጠያቂ አልሆንም›› ያሉት ኤርሚያስ ችሎቱ የዋስ መብታቸውን እንዲያስከበርላቸው ጠይቀዋል።
ጥር 7/2011 በነበረው የጠዋቱ የችሎት ውሎ የፌድራሉ ከፍተኛ ፍረድ ቤት ልደታ ምድብ አስረኛ ወንጀል ችሎት በኤርሚያስ ጠቅል ጉዳይ ላይ ትእዛዝ ለመስጠት ከሰዓት በኋላ ቀጠሮ የያዘ ቢሆንም ከሰዓት በኋላ በነበረው ውሎ የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቷል።
ይህም የዐቃቤ ሕግና መርማሪ ፖሊስ መናበብ የጎደለው ሥራ መሆኑን የተረዳው ምድብ ችሎቱ የጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ መዝገብ በመዝጋት ተጠርጣሪው ጉዳያቸውን በዐሥራ አምስተኛ ምድብ ችሎት እንዲከታተሉ አዟል ።
በዕለቱም ተጠርጣሪው የተከሰሱበትን ወንጀል የተነበበላቸው ሲሆን ችሎቱ የሚያነሱትን የመብትና ሌሎች ጥያቄዎችን አዳምጦ ተጠርጣሪውን የዋስ መብት በመከልከል ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ሆነው እንዲከታተሉ አዟል ።
በቀረበባቸው ክስ ላይ የሚያነሱት መቃወሚያ ካለ ከጠበቆቻቸው ጋር ተመካክረው እንዲቀርቡ ያዘዘው ችሎቱ ለጥር 20 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 10 ጥር 11 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here