ከደኅንነት መሥሪያ ቤቱ የተገኘውን መርዝ ማሽን ሊያነበው አልቻለም” መርማሪ ፖሊስ

0
689

በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት ቢሮ ተገኝቷል የተባለውን መርዝ የፌድራል ፖሊስ ፎረንሲክ ቢሮ ማሽን ማንበብ አለመቻሉን መርማሪ ፖሊስ ገለጸ። ፖሊስ ይሄን የገለጸው የቀድሞ የብሔራዊና መረጃ ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር የነበሩትና መርዙን በቢሮ ውስጥ እንዲቀመጥ አቀነባብረዋል በሚል የተጠረጠሩት ያሬድ ዘሪሁን ላይ ያቀረበውን ምርመራ ሰኞ፣ ጥር 6 ባሳወቀበት ወቅት ነው።
ፖሊስ መርዙን በሚመለከት ከፍርድ ቤቱ ለቀረበለት ጥያቄም መልስ በሰጠበት ወቅት መርዙ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል ተብሎ በመፈራቱ ለኢትዮጵያ ጨረራ ባለሥልጣን ተልኮ መልስ በመጠበቅ ላይ መሆኑንም ገልጿል። መርዙን በሚመለከትም የቀድሞ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጉዳዩን እንዳቀነባበሩት በተደጋጋሚ የሚያነሳው ፖሊስ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ምርመራዎችን እያደረገ መሆኑንም አስታውቋል። ጉዳዩን እየተመለከተ የሚገኘው የፌድራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ ወንጀል ችሎት ጉዳዩን በሚመለከት መርማሪ ፖሊስ መዘናጋት እንደታየበትም አስታውቋል።
በዚሁ ወንጀል ችሎት ጉዳያቸውን እየተከታተሉ የሚገኙትና በነ ጎሃ አጽብሃ መዝገብ የተጠረጠሩ ሰዎችም መርዙን በሚመለከት ለመናገር የሚፈልጉት ነገር እንዳለ ረቡዕ፣ ጥር 1 መጠቆማቸው አይዘነጋም። ይሁን እንጂ በዕለቱ የ10ኛ ወንጀል ችሎት ጉዳዩን በሚመለከት ምንም ነገር መስማት እንደማይፈልግ መናገሩም ይታወቃል።
በወቅቱ ተጠርጣሪዎቹም እኛ ባላደረግነው ወንጀል ስማችን እየጠፋ ነው በዚህም ምክንያት ትክክለኛ የመርዙን መምጫ እናስረዳለን የሚል መከራከሪያ አቅርበው እንደነበረም ይታወሳል። የተጠርጣሪው ጠበቆችም የመርዙም ሆነ ሌሎች ጉዳዮች በደንበኛችን ላይ ብቻ ያነጣጠረ ነው መርማሪ ፖሊስም በተደጋጋሚ የሚያነሳው ጉዳይ ተመሳሳይ ነው የሚል መከራከሪቸውን ለችሎቱ አስረድተዋል።
በሌላ በኩል ተጠርጣሪው በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በኃላፊነት የቆዩት ለሁለት ዓመታት ብቻ እንደሆነ ተናግረው፥ አሁን ላይ ግን ከሰሩባቸው ዓመታት ውጪ ባሉ ጊዜያት የተሠሩ ሥራዎች ተደምረው እየተጠየቁ መሆኑን ጠበቆቻቸው አስረድተዋል። የወንጀለኛ ሥነ ስርዓት ሕጉ በሚፈቅደው መሠረትም እስካሁን ግላዊ መረጃዎቻቸው ያልተጠየቁ ሲሆን መርማሪ ፖሊስ በተሰጠው ቀን መረጃዎችን እያቀረበም አይደለም የሚል መከራከሪያቸውን ለችሎቱ አሰምተዋል።
መርማሪ ቡድኑ በበኩሉ የቀሪ ምስክሮችን ቃል ለመቀበል ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልጉት አስታውቋል። ከሰብኣዊ መብት ጥሰቱ በተጨማሪም ስድስት ሚሊዮን ብርና 200 ሺሕ የአሜሪካ ዶላር ለግል ጥቅማቸው አውለዋል የሚለው መርማሪ ፖሊስ ቀሪ ሥራዎችን አጠናቆ ለመቅረብ ተጨማሪ ቀናት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤቱ ፖሊስ የቀሩትን ምርመራዎች አጠናቆ እንዲያቀርብ ተጨማሪ 10 ቀናት ፈቅዷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 10 ጥር 11 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here