የአዲስ አበባ ቅድመ ምርጫ ሂደት

0
813

ኢትዮጵያ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ቅድመ ምርጫ ሂደት ተግባራትን በማጠናቀቅ ላይ ትገኛለች። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማከናወን አብዛኛዎቹን የቅድመ ምርጫ ሥራዎች አጠናቆ ምርጫውን ለማካሄድ የሳምንት እድሜ ቀርቶታል። ምርጫው ሰኔ 14/2013 እንደሚካሄድ ቦርዱ ወስኗል። ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በተለያዩ ምክንያቶች በገጠሙት የቅድመ ምርጫ ተግባራት አለመጠናቀቅ ምክንያት በሰኔ 14ቱ ምርጫ አንዳንድ አካባቢዎች በተያዘው የምርጫ ሂደት ውስጥ እንደማይካተቱ ታውቋል። ይሁን እንጅ አዲስ አበባ ላይ ምርጫው ሙሉ በሙሉ ሰኔ 14 እንደሚካሄድ ነው እስካሁን ድረስ ያለው መረጃ የሚሳየው።

ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ በሂደቱ ላይ በተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል የተለያዩ ቅሬታዎች አስተናግዷል። በፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል የሚነሱ ጥያቄዎች አንዳንዶቹን ከምርጫው እራሳቸውን እንዲያገሉ እንዳደረጋቸውም በምርጫው የማይሳተፉ ፓርቲዎች ሲገልጹ ተደምጠዋል። በምርጫው ለመሳተፍ እስካሁን ድረስ የነበሩትን የቅድመ ምርጫ ሂደቶች ያለፉ ፖለቲካ ፓርቲዎችም በምርጫ ሂደቱ ላይ ቅሬታ እንዳላቸው እየገለጹ ነው።

በቅድመ ምርጫ ወቅት በፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል የሚነሱ ቅሬታዎችንና የገጠሙ እንቅፋቶችን መነሻ በማድረግ ትኩረቱን አዲስ አበባ ላይ አድርጎ የሚንቀሳቀሰው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ(ባልደራስ)፣ የአዲስ አበበባ ከተማ አስተዳደር ቅድመ ምርጫ ሂደት ላይ ትኩረት አድርጌ የዳሰሳ ጥናት አካሂጃለሁ ብሏል።

ባልደራስ ያደረገው ጥናት “በአዲስ አበባ በ218 የምርጫ ጣቢያዎች የታዩ ተግዳሮቶች የዳሰሳ ጥናት ውጤት” በሚል ርዕስ በ25 ገጽ የተሰነደ ሲሆን፣ የጥናቱ ዓላማ የቅድመ ምርጫ ሂደቱ (pre-election process) አካል የሆነውን የመራጮች ምዛገባ ሂደት (voter registration) ከነፃና ፍትሐዊ ምርጫ መርሆዎች አኳያ ምን ያህል ይጣጣማል የሚለውን ጉዳይ በጥናት ለማረጋገጥ ነው ብሏል። እንዲሁም በመራጮች ምዝገባ ሂደት ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን፣ የምርጫ ጣቢያዎች የሚገኙበት ሁኔታ እና አጠቃላይ የቅድመ ምርጫውን ሂደት የሚዳስስ ጥናት መሆኑን ነው ፓርቲው የገለጸው።

ፓርቲው አዲሰ አበባ ላይ በነበረው ቅድመ ምርጫ ሂደት ላይ አገኘኋቸው ያላቸውን ችግሮች በጥናቱ አስቀምጧል። በዚህም የምርጫ አስፈፃሚዎች የሚጠበቅባቸውን የስራ ኃላፊነት እንዳልተወጡ ከጥናቱ ለመረዳት እንደቻለ የተገለጸ ሲሆን፣ የምርጫ አስፈፃሚዎች አመላመል፣ ስለ ምርጫው ያላቸው ግንዛቤ ፣ በምርጫው ላይ ገለልተኛ አለመሆናቸው፣ የምርጫ አስፈፃሚዎች ትጋት የሚያንሳቸው መሆኑ በምክንያትነት ተጠቅሷል።

በጥናቱ ላይ እንደተገለጸው ከሆነ፣ ችግሩ የሚያጠነጥነው ምርጫውን በሚያስተዳድረው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ላይ ነው። በነበሩት ችግሮች አዲስ አበባ ላይ መራጮች ምርጫ ካርድ መውሰድ መቸገራቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል ባልደራስ በጥናቱ። ይህንኑ መነሻ በማድረግ አዲስ አበባ ላይ የመራጮች ምዝገባ ዳግመኛ ተከፍቶ መራጮች ካርድ እንዲያወጡ መደረግ አለበት የሚል ሀሳብ ቀርቧል።
ከምርጫ ካርድ ግር በተያያዘ በርካታ ቁጥር ያላቸው የምርጫ ጣቢያዎች 1500 የምርጫ ካርድ ሰጥተው የዘጉ ሲሆን፣ በእነዚህ አካባቢ የሚኖሩ ማሕበረሰቦች የምርጫ ካርድ እንዳልወሰዱ ፓርቲው በጥናቱ አረጋግጫለሁ ብሏል። በተመሳሳይ ሁኔታ 1500 ሳይመዘግቡ የተዘጉ የምርጫ ጣቢያዎች እንዳሉም መረዳት ይቻላል የሚለው የባልደራስ ጥናት፣ የምርጫ ጣቢያዎች ያለ ሰዓቱ እንደሚዘጉም የጥናት ውጤቱ ያመለክታል። ከዚህ በተጨማሪ በአንድ የምርጫ ጣቢያ ክልል ከአንድ በላይ ምርጫ ጣቢያዎች የተከፈቱ እንደነበር የጥናት ውጤት ይጠቁማል፤ ውጤቱ እንደሚሳየው ምርጫ ቦርድ ካወጣው ሕግ ጋር የሚፃረር ተግባር መሆኑ በጥናቱ ተገልጿል።

በሌላ በኩል የምርጫ ጣቢያዎች በመጠጥ ቤቶችና ቁማር ቤቶች አከባቢ፣ በፓርቲ ጽህፈት ቤት አከባቢ፣ በግለስብ መኖሪያ ቤትና በሥውር ቦታዎች ላይ የተከፈቱ እንዳሉ አረጋግጫለሁ ያለው የጥናቱ ባለቤት(ባልደራስ)፣ የምርጫ ጣቢያዎች የተከፈቱበት ቦታ ከምርጫ ሕጉ ጋር የሚፃረር እንደሆነ በጥናቱ ለመረዳት ችያለሁ ብሏል። የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 በግለሰብ ቤት የምርጫ ጣቢያ መክፈት እንደማይቻል ይገልጻል።

እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች ከነዋሪው ሕዝብ ጋር የማይጣጣሙ እና ቁጥራቸው አነስተኛ እንደነበር ከጥናቱ ተረድቻለሁ ነው ያለው ባልደራስ። በክፍለ-ከተሞች ውስጥ ብዙ ነዋሪ በሌለበት ቦታ በርካታ ምርጫ ጣቢያዎች የሚገኙ ሲሆን፣ ማስፋፊያ በሆኑ ክፍለ ከተሞች በተለይ በኮነደሚኒየሞች የሚገኙ ዜጎች ለምሳሌ (በየካ፣ቦሌ፣ አቃቂ) በቂ ምርጫ ጣቢያ እንደሌለ በጥናቱ ተረጋግጧል ተብሏል። በማስፋፊያ ክፍለ-ከተሞች ላይ በሚገኙት የምርጫ ጣቢያዎች በፖለቲካ ግፊት ምክንያት በቡድን ከኦሮሚያ ክልል እየመጡ የምርጫ ካርድ ቀድመው ስለወሰዱ በነዚህ አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች የምርጫ ካርድ ማግኘት እንዳልቻሉ ነው ባልደረስ በጥናቱ የገለጸው።

“ከብሔር እና የእምነት ማንነትም ጋር በተያያዘ የምርጫ ካርድ እንደሚታደል ከጥናቱ ለመረዳት ተችሏል። የምርጫ ካርድ መውሰድ የማይገባቸው(ምናልባት) ከሌላ አካባቢ የመጡ ዜጎች የሀሰት ምስክር በማቅረብ የምርጫ ካርድ እንደሚወስዱ በጥናቱ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው” ይላል የባልደረስ ጥናት። የምርጫ ሂደቱ ሁሉን አቀፍ እና እኩል አሳታፊ መሆን እንዳለበት የተቀመጠ ቢሆንም፣ የምርጫ ጣቢያዎች ከዚህ መርህ በተቃራኒ መልኩ እየሰሩ መሆኑን መገንዘብ ያስችላል ብሏል።

አንዳንድ ሰዎች በርካታ የምርጫ ካርዶች ያለአግባብ ማውጣታቸው፣ ከአጎራባች የኦሮሚያ ወረዳዎች እየመጡ ሰዎች ካርድ መወሰዳቸው፣ የምርጫ ቦርድ ከነዋሪዎች ጋር ተመጣጣኝነት ያለው የምርጫ ጣቢያዎችን አለመክፈቱ የችግሮቹ መንስኤዎች እንደሆኑ ለመረዳት እንደሚቻልም ተመላክቷል።

“የምርጫ ቦርድ አቋቋምኳቸው ያላቸው ንዑስ ጣቢያዎች ግልጽ አድራሻ የሌላቸው መሆኑ፣ በፍለጋ ቦታዎች አለመገኘታቸው፣ በአንድ ቦታ ላይ በተለይም በአንድ ቤት በርካታ ጣቢያዎች መገኘት፣በተከለከሉ ቦታዎች ማለትም በመጠጥ ቤቶች፣ በግለሰብ መኖሪያ ቤቶች፣ በጫት ቤቶች ላይ ምርጫ ጣቢያዎችን መክፈት ከምርጫ ሕጉ በተቃራኒ ያሉ አሰራሮች እንደሆኑ ማሳሰብ እወዳለሁ” ብሏል ባልደራስ በጥናቱ መደምደሚያ ላይ።

ፓርቲው ከደረሰባቸው የጥናት ግኝቶች አንጻር፣ 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ከቅድመ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ሂደት አንፃር ሲፈተሸ ነፃና ፍትሐዊነት የሚጎድለው፣ ከቅድመ ምርጫ መራጮች ምዝገባ አንፃር መርሆዎችን ያልተከተለ እና በበርካታ ችግሮች የተተበተበ እንደነበር ተረድቻለሁ ብሏል።

ባልደራስ ካቀረበው ዝርዝር ጥናት አንጻር ጥናቱ የመፍትሄ ሃሳብ ያለውን አስቀምጧል። በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ያልሆኑ ተመዝጋቢዎች በርካታ የምርጫ ካርድ ስለወሰዱ ምርጫ ቦርድ ጉዳዩን አጣርቶ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።

በማስፋፊያ ክፍለ ከተሞች ውስጥ የተካሄደው የምዝገባ ሂደት በርካታ ችግሮች ስላሉበት የምርጫ ምዝገባ ሂደቱ በምርጫ ቦርድ እንዲጣራ፣ የመራጮች ምዝገባ ሂደት ግልጽነት ስለሚጎድለው እና በበርካታ ችግሮች የተተበተበ ስለሆነ፣ የተፎካካሪ ፓርቲ ታዛቢዎች የምዝገባ ሂደቱን እንዲያጣሩ፣ የምርጫ ጣቢያዎች የሚገኙበት ቦታ በምርጫ ሕጉ መሰረት እንዲሆን ምክረ ሀሳብ አቅርቧል። የምርጫ አስፈጻሚዎች በግብረ-ገብነት የታነፁ፣ ገለልተኛ የሆኑ እና የሥራ ትጋት ያላቸው ዜጎች እንዲሆኑ ቦርዱ መሥራት እንዳለበትም በጥናቱ ላይ ተመላክቷል።

ባልደራስ በአዲስ አበባ ቅድመ ምርጫ ላይ ትኩረት አድርጌ አካሂጃለሁ ብሎ ባቀረበው የዳሰሳ ጥናት፣ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ዝቅተኛ ዓለም አቀፍ የምርጫ መሥፈርትን የማያሟላ ሆኖ አግኝቸዋለሁ ብሏል። ይህን ተከትሎ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ሰኔ 2/2013 ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ውይይት ባደረጉበት መድረክ ላይ የቦርዱን ሥራ ማጣጣል የሕዝቡን አመኔታ ሊሸረሽር ሰለሚችል ፓርቲዎች ቀድመው ከመደምደም ቢቆጠቡ ጥሩ ነው ብለዋል። ነገር ግን የፈለጉትን የመግለጽ መብት ስላላቸው ልንከለክላቸው አይገባም፤ ይሁን እንጅ ቀድሞ ውሳኔ ከመስጠት ጊዜ መጠበቅ የተሻለ እንደሚሆን ጠቁመዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 136 ሠኔ 5 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here