ለ2013 ሰብል ዘመን ወደ አገር ዉስጥ የገባዉ ማዳበሪያ በ2012 ሰብል ዘመን ወደ አገር ዉስጥ ከገባው መጠን ጋር ሲነጻጸር በ24.6 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን የኢትዮጵያ ግብርና ኮርፖሬሽን ለአዲስ ማለዳ በላከው መረጃ ገልጿል።
በ2012 ሰብል ዘመን ከገባው 14,585,610 ኩንታል ማዳበሪያ ጋር ሲነጻጸር በዚህ ዓመት የገባው የማዳበሪያ መጠን በ 3.6 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ጭማሪ (24.6%) ማሳየቱን ከመረጃዉ ለማወቅ ተችሏል። ለዚህ የማዳበሪያ ፍላጎት መጨመር ምክንያቱ የአርሶ አደሩ የማዳበሪያ ፍላጎት ከዓመት አመት እየጨመረ በመሄዱ እንደሆነም ከኮርፖሬሽኑ የተገኘዉ መረጃ ይጠቁማል።
ከዚህም በተጨማሪ ማዳበሪያ የማይጠቀሙ አርሶ አደሮች ማዳበሪያ ተጠቃሚ የሆኑ አርሶ አደሮችን የተሻለ ምርት ውጤት ሲያዩ ወደ ማዳበሪያ ተጠቃሚነት መምጣታቸዉ ወደ አገር ውስጥ የገባው የማዳበሪያ መጠን ለመጨመሩ አንዱ ምክንያትም እንደሆነ ታዉቋል።
የአርሶ አደሩን ፍላጎት ለማርካት መንግሥት ከዉጭ ማዳበሪያ እያስገባ እንደሆነ የተናገሩት የኮርፖሬሽኑ ኮሚኒኬሽንና ማኅበራበራዊ ጉዳዮች አገልግሎት ኃላፊ ጋሻዉ አይችሉህም፣ እያንዳንዱ ፍላጎት በጥናት ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ገልጸዋል። በጥናቱ መሰረትም የዘንድሮ የማዳበሪያ ፍላጎት በ24.6 በመቶ ከአምናዉ ብልጫ አሳይቷል። ይህ የማዳበሪያ ፍላጎት በ2014/15 የምርት ዘመንም ጭማሪ ያሳያል ተብሎ ይገመታል ።
በአገር ዉስጥ ብቸኛ የማዳበሪያ አስመጪ የሆነዉ የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ለ2013/14 የሰብል ዘመን 18,169,220 ኩንታል ማዳበሪያ ለማስገባት አቅዶ ነበር።
እንደ ኮርፖሬሽኑ መረጃ ወደ አገር ዉስጥ የሚያስገባቸዉ የማዳበሪያ አይነቶችም አራት አይነት ሲሆኑ እነሱም፣ ኤንፒኤስ (NPS)፣ኤንፒስቢ (NPSB)፣ኤንፒስዚንቢ(NPSZnB) እና ዩሪያ( Urea) የተባሉ የማዳበሪያ አይነቶች ናቸዉ።
የማዳበሪዎቹ ዋጋ እንደ አይነታቸው እንደሚለያይ ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት ኃላፊው ከተጠቀሱት የማዳበሪያ አይነቶች ውስጥ ዩሪያ ከፍተኛ ዋጋ አለዉ ብለዋል።
ከእነዚህ የማዳበሪያ አይነቶች 15,047,713 ኩንታል የሚሆነው ጅቡቲ ወደብ መድረሱን ኮርፖሬሽኑ ለአዲስ ማለዳ በላከዉ መረጃዉ አስታዉቋል።
ከዚህም 12,127,510 ኩንታል ማዳበሪያ ወደ አገር ዉስጥ ተጓጉዞ በሕብረት ሥራዎች አማካይነት ለአርሶ አደሮች እየተከፋፈለ እንደሚገኝ ተገልጿል።
በእያንዳንዱ ክልል ያለዉን የገበሬ ማሳ ፍላጎትን መረጃ ሰብስቦ ለግብርና ሚኒስቴር በመላክ ሚኒስቴሩ የተላከለትን መረጃ መሰረት በማድረግ ጥናት እንደሚያደርግ ኮርፖሬሽኑ አስታዉቋል። በጥናቱ መሰረትም የሚገዛዉ የማዳበሪያ ፍላጎት ለኮርፖሬሽኑ ሲደርሰዉ ጨረታ አዉጥቶ ይገዛል።
አንዳንድ አርሶ አደሮች በበኩላቸዉ የአፈር ማበልጸጊያ ማዳበሪያዉ ቶሎ እንደማይደርሳቸዉ ይገልጻሉ። ከዚህም በተጨማሪ የማዳበሪያ ዋጋ እንደተወደደባቸዉ ሲናገሩ ይሰማሉ።
መንግሥት ይህንን ችግር ለመቅረፍ ዘንድሮ 4.5 ቢሊዮን ብር በመመደብ ከወደብ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ለማሰራጨት ለትራንስፖርት ድጎማ ማድረጉን ጋሻዉ ተናግረዋል።
የማዳበሪያ ዋጋ በዓለም ላይ በከፍተኛ ደረጃ ከአመት አመት ጭማሪ እያሳየ በመሆኑ መንግሥት የትራንስፖርት ድጎማ ማድረጉ አርሶ አደሩ ማዳበሪያ ተወዶበት ሳይገዛ እንዳይቀር ያግዛል ተብሏል። አርሶ አደሩ ማዳበሪያን በውድ የሚገዛ ከሆነ ምርቱን ለሕብረተሰቡ ሲያቀርብ ሊያስወድደዉ ይችላል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በብቸኝነት ከዉጪ ማዳበሪያ የመግዛት ኃላፊነት የተሰጠው መሆኑ ተገልጿል። ከዉጭ የማስገባትና የማሰራጨት ሥራዉ የተሰጠዉ ደግሞ ለኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ አገልግሎት ድርጅት ነዉ።
ወደ አገር ዉስጥ የገባዉ ማዳበሪያ ወደ አርሶ አደሩ ጋር እንዲደርስ የግብርና ሚኒስቴር፣የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽንና ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ አገልግሎት ድርጅት በጥምረት እንደሚሰሩ ኮርፖሬሽኑ ገልጻል።
ቀድሞ በነበረው አሠራር ፍቃድ ወስደዉ ማዳበሪያ ወደ አገር ዉስጥ የሚያስገቡ ባለሀብቶች የነበሩ ሲሆን፣ አሁን ላይ ግን የማስገባቱን ሥራ በብቸኝነት እየሠራ የሚገኘዉ የግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
ቅጽ 3 ቁጥር 136 ሠኔ 5 2013



