ወደ ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የሚመጡ የኮቪድ ተጠቂዎች ቁጥር በግማሽ መቀነሱ ተገለጸ

ወደ ኤካ ኮተቤ አጠቃላይ ሆስፒታል የሚመጡ የኮቪድ ህሙማን ቁጥር ካለፉት ወራት አንጻር ሀምሳ በመቶ መቀነሱን በሆስፒታሉ የኮቪድ ህክምና ማእከል የህክምና አገልግሎት ኃላፊ ዶክተር ናትናኤል በኩረጺዮን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ሆስፒታሉ ለኮሮና ህሙማን አገልግሎት የሚሰጥ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አሁን ላይ በየቀኑ ወደ ሆስፒታሉ የሚመጣው ታካሚና ጽኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ያለው ቁጥር በግማሽ ቀንሷል።
መጋቢትና ሚያዚያ ወር ላይ ከነበረው አጠቃላይ ውጤት አንጻር ግንቦት ወር ላይ መሻሻል እንዳለ ነው ዶክተር ናትናኤል የገለጹት።
እስካለፉት ጥቂት ጊዜያት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ የሚጠቁ ሰዎች ቁጥር ከማሻቀቡ የተነሳ ከሀምሳ በመቶ በላይ የሚሆኑት ታማሚዎች በጽኑ ህክምና ክፍል ውስጥ ይገኙ እንደነበር ያስታወሱት ዶክተር ናትናኤል፣ የሟቾችም ቁጥር አስጊ እንደነበር አንስተዋል።

ይህም ባሉት የህክምና መሳሪያዎች እጥረት ላይ ተጨምሮ ሁኔታውን አሳሳቢ አድርጎት እንደቆየም ጠቅሰዋል።
ወደ ኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ኮቪድ-19 ህክምና ማዕከል ከሚገቡት አንድ መቶ ግለሰቦች ሰማንያ ሶስት የሚሆኑት በተለያየ መጠን ኦክስጅን ያስፈልጋቸው እንደነበር አክለው ጠቅሰዋል።
በሆስፒታሉ ከዚህ ቀደም የጽኑ ህሙማን ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ የኦክስጅን እጥረት የተከሰተ እንደነበር ጠቅሰው፣ የኦክስጅን አምራቾች ወደ ስራ ገብተው ችግሩ መቀረፉን አንስተዋል።
ይህ ማለት ግን ቁጥራዊ መረጃው በዚሁ ይቀጥላል ማለት እንዳልሆነ ዶክተር ናትናኤል ገልጸው። የሚደረጉ የጥንቃቄ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል ብለዋል።

እንዴት ቀነሰ የሚለው ተጨማሪ ጥናት የሚያስፈልገው ነው ያሉት የማዕከሉ ኃላፊ፣ አዲስ የሚመጡ ታካሚዎች እና ኦክስጅን ያስፈልጋቸው የነበሩ ህሙማን ቁጥር በእጥፍ መቀነሱ ብቻ ታውቋል ብለዋል።
በኮሮና ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መቀነሱ የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነሱ ማሳያ ሊሆን እንደማይችልም አንስተዋል።

አያይዘውም በሆስፒታሉ የህክምና ባለሙያ እጥረት ችግር አሁንም እንዳልተቀረፈ የተናገሩት ዶክተር ናትናኤል፣ ሆስፒታሉ ባለው አቅም ሁሉ ተገቢውን አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
ኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ ገባ ከተባለበት ጊዜ መጋቢት ወር አንስቶ እስከ ግንቦት ሀያ ሰባት 2012 ዓ.ም ድረስ የተመዘገበው ዝቅተኛ የተጠቂዎች ቁጥር ሀያ ዘጠኝ ብቻ እንደነበር የወርልዶ ሜትርስ ድረ ገጽ አስነብቧል።

ቫይረሱ የስርጭት አድማሱን እያስፋፋ መምጣቱን ተከትሎ በሚያዚያ ወር ላይ 2ሺ 353 ያህል ተጠቂዎች የተመዝገቡበት ከእስከ ዛሬው ከፍተኛ የተባለለት ነበር።
በዚህም ረገድ አሁን ላይ አጠቃላይ በአገሪቷ የተመዘገበው የተጠቂዎች ቁጥር 273 ሺህ 678 ሲደርስ 4.231 የሚሆኑት ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸው አልፏል። 249 ሺህ 028 ያህሉ ደግሞ ከቫይረሱ ማገገም መቻላቸውን ድረ ገጹ አስነብቧል።

ይሁን እንጂ አሁን ላይ ይህ መረጃ እስከ ተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 280 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል በአንድ ወር ውስጥ ከግማሽ ሚሊዬን በላይ ሰዎች ክትባት አግኝተዋል መባሉ የሚታወስ ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 136 ሠኔ 5 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here