አገራዊው ምርጫ ቀናት እየቀረው የምርጫ ቅስቀሳው ተጧጡፎ መስመሩ ግን እየተቀየረ ይታያል። የቅስቀሳ ፖስተር ለመለጠፍ በነበረ እሽቅድምድም ተጀምሮ፣ በመንገድ ላይ ቅስቀሳ ታጅቦ ወደ ክርክር ያመራው የቅስቀሳ ሂደቱ አሁን ፍትሐዊነቱ እያጠያየቀ ነው። ገዢው ፓርቲ የመንግሥት ንብረትንም ሆነ ኃላፊነትን ተጠቅሞ እንዳይቀሰቅስ የምርጫ አዋጁ ቢከለክልም ተግባራዊ እየተደረገ አይደለም።
ይባስብሎ መሳሪያ የታጠቀን ሳይቀር ቲሸርት እያለበሱ ፎቶውን በመለጠፍ ፍርሃትን ለመንዛት ሲሞከር እየታየ ነው። በመንግሥት ሥራ ላይ ሆነው ፈቃድ ሳይወጡ ለየትኛወም ፓርቲ ቅስቀሳ የሚያደርጉ የመንግሥት ሠራተኞችና ባለሥልጣናት በግልጽ መታየታቸው የተለመደ ቢሆንም፣ አሁን አሁን ግን ይህ አልበቃ ብሎ በሕዝብ ሀብት የተገነቡ የመንግሥትና የሕብረተሰቡን ሥራዎች የምርጫ መቀስቀሻ ሲደረጉ ይስተዋላል።
በህወሓት ይመራ የነበረው ኢህአዴግ ንብን ምልክቱ አድርጎ እንደንብ ታታሪ ነኝ ለማለት የምርጫው ሰሞን ዋና የመንግሥትነቱን ሥራ ትቶ፣ በዘመኔ የሠራኋቸው እያለ የመንግሥትን ሥራ እንደ ፓርቲ ሥራ አድርጎ መቀስቀሻ ማድረጉ የተለመደ ነበር። የሠራው ሲያንስበትም ኮንደሚኒም ቤት እገነባለሁ፤ ወንዝ እገድባለሁ፤ በስኳር አንበሸብሻችኋለሁ፣ አማላይ ፕሮጀክቶችን እጀምራለሁ ወይም አጠናቅቃለሁ በማለት ቃል ይገባ ነበር። ይህም አልበቃ ብሎት በየቦታው ለሚሠሩ ፕሮጀክቶች ቁጥሩ እስኪጠፋበት ድረስ የመሠረት ድንጋይ እየጣለ ምንም ሳይሠራቸው ቀጣዩ ምርጫ ይደርስበት ነበር።
የአሁኑ አመራርም ከዚያኛው አካሄድ ሳይማር እንደውም እንደጥሩ ተሞክሮ የቆጠረው ይመስል በብዙ እጥፍ አብዝቶት በተመሳሳይ መልክ እየቀሰቀሰበት ይገኛል። ይህን እድል ተቃዋሚዎች ሊያገኙት እንደማይችሉ በማሰብ የፉክክር ሜዳውን ብቻውን ጋልቦበት ለብቻው አሸነፍኩ ለማለት የቅስቀሳ ብቃት ማረጋገጫ ዋንጫውን ለራሱ ለመሸለም እየተጠባበቀ ይገኛል። ለቅስቀሳ ተብለው የሚመረቁት ፕሮጀክቶች ፓርቲው በራሱ ገንዘብ የሠራቸው አይደሉም። ግንባታዎቹን የሕዝብ ሀብትን ተጠቅመው አመራሮቹ ስላሥፈጸሙት ብቻ ሊቀሰቅሱበት ይገባል ወይስ አይገባም የሚለው አከራካሪ ቢሆንም፣ ከተቃዋሚዎቹ እይታ አንጻር ግን ፍትሐዊ መንገድ እንደማይሆን ግልጽ ነው። የፓርቲና የመንግሥት ግንኙነትና ተግባር ሊለያይ ሲገባው ከቀድሞው ሥርዓት ሳይማሩ በዛው መቀጠሉም ተገቢ አይሆንም።
ሕዝብ የአጭር ጊዜ የማስታወስ ብቃት(short memory) ነው ያለው እየተባለ በግልጽ ስለሚደሰኮር፣ ፕሮጀክቶቹ በተጠናቀቁ ጊዜ ቀድሞ መርቆ ማስረሳት እንዳይሆን ተብሎ ለሠሞኑ መከማቸታቸው ይነገራል። በዚህ እሳቤ ሕብረተሰቡ እስኪሰለች ድረስ በየቦታው ሪቫን በመቀስ እየቆረጡ “…ተመረቀ” እያሉ ማስነገሩ “ማርም ሲበዛ ይመራል” እንደሚባለው ሕዝብን ያማርራል። የምርጫ ቅስቀሳ ዓላማ ሕዝብ ፓርቲዎችን አውቆ እንዲገመግምና አወዳድሮ እንዲመርጥ እንጂ አንድ ፓርቲ ሕዝብን እንዲያጭበረብር እንዳልሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች።
በሕዝብ ሀብት እስከተገነቡ ድረስ ለፓርቲ መቀስቀሻ መዋል የሌለባቸው ግንባታዎች ወዲያው እንደተጠናቀቁ ተመርቀው አገልግሎት ቢሰጡ ሊያስመሰግኑ ይችላሉ። በተቃራኒው ዘግይተው ከተጠናቀቁ ማስወቀስ ብቻ ሳይሆን ሊያስቀጡ ይገባል። በበፊቱ ሥርዓት ተጀምረው ሲጓተቱ ቆተው ምርጫ ሲደርስ ተጠናቀቁ ማለቱ ሊያስገምት ቢችልም፣ በአጭር ጊዜ ተጀምረው በራሳቸው ጊዜ ወቅታቸውን ጠብቀው ከተጠናቀቁ በምርጫው ወቅት ቢሆንም መመረቃቸው ችግር አይኖረውም። መዘግየቱ ግን የተጠናቀቀው ግንባታ እሰኪመረቅ ድረስ ያስገባ በነበረው ገቢ ወይም ባስተጓጎለው አገልግሎት መጠን እንዲዘገይ ያደረገው ወገን ሊጠየቅ በተገባ ነበር። ለዚህ ምሳሌ የሚሆነው ተገንብቶ ካለቀ ከሳምንታት በኋላ ባለፈው ዕሮብ ተመርቆ አገልግሎት እንዲሰጥ የተደረገው የመርካቶ የአውቶብስ ተርሚናል ነው። እንዲህ አይነት በርካታ ምሳሌዎችን ማቅረብ ይቻላል። ይህ አይነት አካሄድ የመቀስቀሻ ዓላማውን ማሳካቱ ቀርቶ በተቃራኒው የነበረ ደጋፊን ሊያሳጣ እንደሚችል አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትወዳለች።
ለእንዲህ አይነት ዘዴ ይውላሉ ተብለው የተከማቹ ሥራዎችን በየቦታው ለመመረቅ ሰሞኑን እየተጣደፉ ነው። ኦሮሚያ ክልል ብቻ ከ10 ሺሕ በላይ ፕሮጀክቶችን ከምርጫው በፊት ያስመርቃል መባሉ መነጋገሪያ ሆኗል። በሌላ በኩል ከማን አንሼ ያሉ የአማራ ክልል ወረዳዎች ሳይቀሩ ዘመናዊ የትምህርት ቤት ሽንት ቤት ተመረቀ እያሉ፣ ገና የእንጨት ርብራብ ብቻ የተዘረጋበትን ጉድጓድ በምስል ያሳያሉ። አንዱ ሚዲያዎችን ሲያጨናንቅ ሌላው የሚያስመርቀው እያጣ በመካከል ልዩነትን ሊያሰፋ የሚችል አጋጣሚንም እየፈጠረ ነው። ለምርቃዎቹ የሚወጣ ወጪ ምርቃው ፈጠነም ዘገየም የሚቀር ባይሆንም፣ እንደተማሪዎች ምርቃ ፕሮጀክቶቹን በአዳራሽ ሰብስቦ መመረቅ ስለማይቻል የባለሥልጣናቱ የአጀብ ወጪብቻ ሌላ ፕሮጀክትን ሊያጠናቅቅ ስለሚችል ቢታሰብበት መልካም ነው።
በሌላ በኩል፣ ዘግይቶ የመመረቁን ያህል ሳያልቁ መመረቅም እንዳለ ይታወቃል። ለምሳሌ፣ የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ሲመረቅ የግንባታው 10 በመቶ ገና እንዳልተጠናቀቀ ተነግሯል። ሕዝብ አያውቅም እያሉ ለማሞኘት እንደምስራቃውያን ፍልስፍና ወሬን እየደጋገሙ ለማሳመን መጣሩ ለጊዜው ሊሰራ ይችላል። ዘመኑ የመረጃ ፍሰቱ የፈጠነበት እንደመሆኑ የድሮው አሠራርና ዘዴ ውጤታማ ላያደርግ የመቻሉ ዕድል ሰፊ ነው። ማንም ሰው ሊያታልለው የፈለገን ሰው ልጁም ቢሆን እንኳን እንደሚናደድበት ግልጽ ነው።
መሠረተ ልማቶችን በመመረቅም ሆነ የመሰረት ድንጋይ በማስቀመጥ ተፎካካሪ ፓርቲዎች መቀስቀስ ስለማይችሉ ሜዳውን ደልዳላና ፍትሐዊ ለማድረግ መንግሥት ኃላፊነት አለበት። ይህ ካልሆነ ገዢው ፓርቲ ይህን አደረግሁ ሲል እነሱ ደግሞ፣ “እነዚህን ድንጋዮች መሠረት ብለህ ጥለህ ረስተሃቸዋል፤ ለዚህ ብለህ ይህን ያህል ገንዘብ አክስረሀል፤ በማዘግየትህም ይህን ያህል ገቢ አስቀርተሀል” እያሉ ለሕዝቡ መረጃው የተሟላለት እንዲሆን በመንገር ቅስቀሳው የተማከለና ሚዛናዊ እንዲሆን ቢያደርጉ መልካም እንደሚሆን አዲስ ማለዳ እምነቷ ነው።
በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የማወናበጃና የማጓጊያ ቅስቀሳ ማድረጉ በምዕራባውያንና ንቃተ ህሊናቸው በዳበረ አገራት የተለመደ አይደለም። በእስያና ባላደጉ አገራት የተለመደ ቢሆንም እንደ አፍሪካ የሚዘወተርበት ያለ ግን አይመስልም። ገዢዎቹ፣ እነሱ ባይመረጡ ሥራዎች እንደማይሠሩ ለማሳመን ይጥራሉ። ሌሎቹ ቢያሸንፉ ምንም እንደማይሠሩ ራዕይ ያዩ ይመስል ከሙስና ተርፎ በሕዝብ ሐብት የተሰራን ተግባር እያሳዩ አድንቁን ይላሉ። በዚህ አይነት መንገድ ገጠር ያለውና በቂ መረጃን ከተለያየ ወገን የማያገኘው ሕብረተሰብ ሊታለል ይችላል ተብሎ ቢገመትም፣ አሁን አሁን ከቴክኖሎጂ ጋር በተገናኘ ከተማ የሚሆነውን የማይሰማ ዜጋ አለ ብሎ ለመገመት ያስቸግራል። ችግር ላይ ያለን ማማለል ቀላል ቢሆንም፣ በብዙ ወጪ ተጊጦ ያማረውን ከተማ እያስኮመኮሙ በልዩነቱ እንዲማረርና እንዲፈልስ፣ አሊያም ኑሮው ተስፋ አስቆርጦት ሠርቶ ከመለወጥ ይልቅ ለሌላ ዓላማ እንዲነሳሳ ሊደርገው ይችላል።
በምርጫ ቅስቀሳ ሕዝብ የሚቀሰቀሰው እንዲያውቅ እንጂ እንዲሳሳት አይደለም። አጭበርብሮ የተመረጠ ኮርጆ እንዳለፈ ተማሪ ከሥራ መባረርን ያስከትልበታል። በኩረጃ አንደኛ የወጣ ተማሪ በራሱ ሠርቶ ኹለተኛ ከወጣው በልጧል ተብሎ ሽልማት ሊያገኝ ይችላል እንጂ፣ ክብርንም ሆነ የመንፈስ እርካታን እንደማያገኝ ይታወቃል። ተገቢ ያልሆነ የቅስቀሳ መንገድን ሌሎቹም ሊከተሉ ቢችሉም ሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ መልካም ምሳሌ ሊሆን ይገባል። ተፎካካሪዎች መንግሥትም ሆነ ገዢው ፓርቲ በቀደደው ቦይ ከመፍሰስ ተቆጥበው የራሳቸውን የሥነ-ምግባር መርህ ቢከተሉ መልካም ነው። እስካሁን የተሰራው መልካም ጅማሮ እንዳለ ሆኖ የውድድር ሜዳው ፍትሐዊ ሆኖ ሕዝብ አውቆበት ሊጠቀምበት የሚያስችለው መደላድል አሁን ዘግይቶም ቢሆን በተሻለ ሆኔታ እንዲመቻች አዲስ ማለዳ ጥሪ ታቀርባለች።
ቅጽ 3 ቁጥር 136 ሠኔ 5 2013


