በአጣዬ ከተማ ሥራ ግቡ የተባሉ የመንግሥት ሠራተኞች ቅሬታ አሰሙ

አጣዬ ከተማ ሙሉ በሙሉ ከወደመች ወዲህ ሥራ አቁመው የነበሩ የከተማዋ የመንግሥት ሠራተኞች ከግንቦት 30 ጀምራችሁ ወደ ሥራ ገበታችሁ ተመለሱ መባላቸውን ተከትሎ ስጋት እንዳለባቸው በመግለጽ ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ አሰምተዋል፡፡

በርካታ ዜጎች የተፈናቀሉበት፣ የግልና የመንግሥት ንብረቶች የወደሙበት ክስተት አሁን ላይ ወደ አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት እንደተመለሰ ይነገራል።
ምንም እንኳን አሁን ላይ በከተማዋ አንጻራዊ ሰላም የሰፈነ ቢሆንም፣ በነጻነት መንቀሳቀስ አይቻልም ብለዋል የመንግሥት ሠራተኞቹ፡፡
ወደ ሥራ ገበታ መመለሱ ቀርቶ ኑሯችንንም በስጋት ነው የምንኖረው ያሉት የከተማው ነዋሪዎች፣ አሁንም ቢሆን ለደህንነታችን ምንም ዋስትና የለንም ብለዋል፡፡
ለዚህም ከአንድም ስድስት ጊዜ በተደጋጋሚ የተፈጠረው ግጭት እና አለመረጋጋት ትልቁ ማሳያ ነው ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
በስደት እና መፈናቀል መኖር ሰልችቶናል የሚሉት ደግሞ ሌሎቹ የከተማዋ ነዋሪዎች ናቸው፡፡

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው እነዚሁ ነዋሪዎች ወደ ቀያችን መመለስ እንፈልጋለን፤ ቀድሞ የምንመራውን አይነት የተረጋጋ ህይወት መኖር ናፍቆናል ይላሉ፡፡
ነገር ግን ሰላም ሰፍኗል ብለን በተመለስን ቁጥር ዳግም የማያባራ የሚመስል ግጭት ይፈጠራል ያሉት ነዋሪዎቹ አሁንም ስጋት ውስጥ ነን ብለዋል፡፡
የአጣዬ ከተማ ከንቲባ አገኘሁ መክቴ በበኩላቸው፣ የደረሰውን ጉዳት መልሶ ለማቋቋም የተለያዩ የድጋፍ ደረጃዎች እየተተገበሩ መሆኑን ገልጸው የዕለት ደራሽ ድጋፍ ማድረግ፣ ሃብትና ንብረታቸው የወደመባቸውን መደገፍ፣ በግጭቱ ምክንያት ደፍርሶ የቆየውን አካባቢያዊ ሁኔታ ወደ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት መመለስ፣ እንዲሁም በጉዳት ምክንያት የተቋረጠውን የመንግሥት አገልግሎት ማስጀመር እየተከናወነ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ አብራርተዋል።

አክለውም አጣዬ ከተማና አካባቢውን ወደ ነበረበት ለመመለስ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ገልፀዋል።
በከተማዋ ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር ተፈቶ ወደ ቀደመው ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለሱ መልካም መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዚሁ ተፈፃሚነት የመንግሥት ሠራተኞች ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው ብለዋል።
አያይዘውም ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር የተፈናቀሉ ወገኖችን በሙሉ ወደ ቀያቸው የመመለስ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።
መንግሥታዊ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ሁሉም ወደ ሥራ መመለሳቸውን የገለጹት አገኘው፣ ቀደም ብለው አገልግሎት የጀመሩ ተቋማትም በተጠናከረ መልኩ ሥራቸውን ቀጥለዋል ብለዋል።
ከተማዋን ዳግም ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የተደረገው ድጋፍም ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡

የመንግሥት አገልግሎት ሰጭ ተቋማትን በተሟላ አቅም ሥራ ለማስጀመር የተደረገው የቁሳቁስ ድጋፍም የከተማ አስተዳደሩን ጥረት ያግዛል ብለዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎችም በሀሰት በሚነዙ ወሬዎች ሳይሸበሩ ወደ ቀያቸው በመመለስ ከተማዋን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በአካባቢው የጸጥታ ሥራ ቀዳሚ ተግባር ተደርጎ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
ከሦስት ወራት በፊት በአካባቢው በተፈጸመ ጥቃት በአጣዬ ከተማና አካባቢው መጠነ-ሠፊ ሰብዓዊ ጉዳትና ከፍተኛ የንብረት ውድመት መድረሱ ይታወሳል።


ቅጽ 3 ቁጥር 136 ሠኔ 5 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here