በርካታ ምሁራንን ሲያከራክር የቆየው እና ከጥር 2013 ጀምሮ ተቋርጦ የቆየው የታሪክ ትምህርት በኹለተኛው መንፈቅ የትምህርት ዓመት ለመስጠት መታቀዱን የሞጁሉ አዘጋጅ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የታሪክ መምህር የሆኑት ሳሙኤል ነጋሽ (ዶ/ር) ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በመጪው ኹለተኛው መንፈቅ የትምህርት ዘመን ትምህርቱን ለማካተት በቂ ጊዜ መኖሩ በሞጁሉ አዘጋጆች በኩል ምክክር ተካሂዶበት፣ ይስተካከሉ የተባሉ ነጥቦች ተስተካክለው ትምህርቱን ለመስጠት ዝግጅቱ ተጠናቋል። የታሪክ ትምህርት እንደመሆኑ መጠን አከራካሪ መሆኑ የሚታወቅ ነው የሚሉት ሳሙኤል፣ እንደማንኛውም ሞጁል በየአምስት ዓመቱ እየተሻሻለ ወቅቱ የሚፈልገውን የትምህርት ስርዓት ማስኬድ ይቻላል ብለዋል።
አሁን በ1ኛው መንፈቅ የትምህርት ዘመን ትምህርት የሚጀምሩ የአንደኛ ዓመት ተማሪዎች ወደ ኹለተኛ ዓመት ከመሻገራቸው በፊት 2ኛው መንፈቅ የትምህርት ጊዜ ላይ እንዲወስዱ ከጉዳዩ ጋር ቅርበት ካላቸው ሰዎች ጋር ተመክሮበት ተጠናቋል።
የታሪክ ትምህርቱ በተሰጠው ግብዓት መሰረት በርካታ ማሻሻያዎች እና እርማቶች ተደርገውበት፣ ከተለያዩ ምሁራን የተነሱ ግብዓቶች ተካተውበት፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ታሪክን ለማስተማር የሚያስችል እንዲሆን ተደርጎ ወደ ተግባር ለመግባት ታቅዷል ነው ያሉት።
በእኛ በሞጁሉ አዘጋጆች በኩል ያለው ተስፋ ትምህርቱ በእርግጠኝነት እንደሚጀመር ነው ያሉት ሳሙኤል፣ የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር መጀመር ትችላላችሁ የሚል ፍቃድ ከሰጠ ወደ ተግባር ለመግባት ኹሉንም ዝግጅቶች ማጠናቀቃቸውን ነው የገለጹት። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሚያደርጋቸው ውይይቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ሳሙኤል ጠቁመዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የደረሰበትን ደረጃ ለማወቅ አዲስ ማለዳ በተደጋጋሚ ብትጠይቅም ምላሽ ማግኘት አልቻለችም።
የታሪክ ትምህርት ሁሉም የአንደኛ ዓመት ተማሪዎች 2ኛ ሴሚስተር ላይ የሚወስዱት የጋራ ትምህርት (ኮመን ኮርስ) በመሆኑ በዚህ ዓመት ያሉት የማይወስዱት ከሆነ ቀጣይ ዓመት ላይ የኮርስ መደራረብ ተማሪዎች ላይ ሊፈጥር እንደሚችል ሳሙኤል ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
የታሪክ ትምህርትን በጋራ ትምህርትነት (በኮመን ኮርስ) ለሁሉም ተማሪ በዩኒቨርስቲ ደረጃ ለመስጠት የሚያስፈልጉ ግብዓችን በሙሉ ተማልተው ያለቀ ሲሆን፣ አንዳንድ የቃላት አጠቃቀም ላይ የተፈጠሩ አለመግባባቶች ተስተካክለዋል ሲሉ ሳሙኤል ገልጸዋል።
የታሪክ ትምህርት በተፈጥሮው ኹሉንም የሕብረተስብ ክፍል በአንድ ሃሳብ የማያስማማ እንደመሆኑ መጠን በሚያግባቡን ጉዳዮች እየተግባባን፣ ያላግባቡንን ጉዳዮች ደግሞ እያስተካከልን እንዲቀጥል ታስቧል ብለዋል።
የታሪክ ትምህርት የቀደመውን ሕዝብ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ገጽታዎች ለመረዳት የሚያስችል ነው ሲሉም ሳሙኤል ይገልጻሉ።
የታሪክ ትምህርት ቀሪው ትውልድ ከስህተቶች ተምሮ ራሱን እንዲያርም ለማስቻል በማሰብ እንደሚሰጥም ተናግረዋል።
ባለፉት ጊዜያት ለታሪክ ትምህርት ማስተማሪያነት የተዘጋጀው ሞጁል የተለያዩ የዘርፉ ምሁራንን አስተያየቶች ተካተውበት ለማስተማሪያነት ዝግጁ እንደነበር እና የኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ ታሪክ ማስተማሪያ ሞጁል ላይ ያተኮረ አውደ ጥናት በአዲስ አበባ ተካሂዶ እንደነበር ሳሙኤል አስታውሰዋል።
የተዘጋጀው ሞጁልም የተለያዩ ሂደቶችን አልፎ፣ በዘርፉ ምሁራን ጠለቅ ያሉ አስተያየቶች ተሰጥተውበተ የቆየ ቢሆንም ወደ ተግባር ሳይገባ ሲጓተት መቆየቱን ነው ሳሙኤል ያነሱት።
ሞጁሉ ከዚህ ቀደም በሰባት ምዕራፍ የተከፋፈለ እና 107 ርዕሶችን በመያዝ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ለኹሉም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለአስተያየት ተልኮ የተለያዩ ሀሳቦች ሲሰጡ መቆየቱንም አስታውሰዋል።
በመጀመሪያው የሞጁሉ ረቂቅ የተለዩ ችግሮች ሙሉ በሙሉ መታረማቸውና በተለያዩ መንገዶች የተሰበሰቡ አስተያየቶችም ተካተውበት ሞጁሉ ለተማሪዎች አቅም በሚመጥን ደረጃና ልክ ተዘጋጅቶ መቆየቱን አዲስ ማለዳ ተረድታለች።
ሞጁሉ ለማስተማሪያነት እንዳይውል ጥያቄ ሲነሳበት ከነበረው ጉዳይ መካከል አንዱ አብዛኞቹ ርዕሰ ጉዳዮች ያለምንም ማስረጃ የቀረቡ ናቸው የሚል ነበር። ከዚህ በተጨማሪም የታሪክ ጽሑፉ ሲጻፍ ማለፍ የሚገባውን ማለትም መረጃ መሰብሰብ፣ መለየት፣ ማደራጀት፣ ማቀናበር እና መተንተን የሚሉት ሂደቶች በሞጁሉ ዝግጅት ወቅት ያለመሟላተታቸውም ጭምር ለቅሬታ መሰረት የነበረ ጉዳይ መሆኑ ይታወሳል።
ቅጽ 3 ቁጥር 136 ሠኔ 5 2013



