ሰኔ 14 ምርጫ የማይካሄድባቸው አካባቢዎች ኹለተኛው ዙር ምርጫ ጳጉሜ አንድ ይካሄዳል

0
1049

የጸጥታ ችግር ያለባቸው አከባቢዎች ምቹ ካልሆኑ በኹለተኛው ዙርም ላይካሄድ ይችላል

ኢትዮጵያ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ የምርጫ ቅድመ ሥራዎችን ስትሠራ ቆይታ የመጨረሻው የምርጫ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ የምርጫ ቅድመ ሥራዎችን እያከናወነ ባለበት ሁኔታ በተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች በተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ከመደበኛ አካባቢዎች አኩል የምርጫ ሂደቱ ያልተፈጸመባቸው ቦታዎች ነበሩ።
በመሆኑም ቦርዱ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ በኹለት ዙር ለማካሄድ በሁኔታዎች መገደዱን ተከትሎ በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ከሚደረግበት ሰኔ 14/2013 በተጨማሪ ኹለተኛ ዙር የምርጫ ቀን አስፈልጎታል። በዚሁ መሰረት የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ኹለተኛ ዙር ምርጫ ጳጉሜ 1/2013 እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ከትግራይ ክልል ውጭ ባሉ ክልሎች በተመሳሳይ ጊዜ ለማድረግ አቅዶ ሲሰራ ቢቆይም፣ በአንዳንድ አከባቢዎች ላይ በጽጥታ ምክንያት የምርጫ ቅድመ ሥራዎች በተገቢው ሁኔታ ባለመሰራታቸው ኹለተኛ ዙር ምርጫ ማካሄድ አስፈልጓል። በተጨማሪም ቦርዱ በመጨረሻው የምርጫ ሂደት ላይ ባለበት ሁኔታ የድምጽ መስጫ ወረቀት ኅትመት ስህትት እንደገጠመው ገልጿል።

በዚህም የደምጽ መስጫ ወረቀት ችግር በገጠመባቸው የምርጫ ክልሎች የድምጽ መስጫ ወረቀት ዳግመኛ ማሳተም በማስፈለጉ በተጨማሪ የምርጫ ክልሎች ምርጫውን ለኹለተኛ ዙር ማሸጋገርና፣ በተለይ በሶማሌ ክልል ቦርዱ በገጠመው የኅትመት ችግር የክልልና የሕዝብ ተወካዮች ምርጫ ሙሉ በሙሉ በኹለተኛው ዙር እንዲሆን ተወስኗል።

የድምጽ መስጫ ወረቀት ኅትመት ችግር ባጋጠመባቸው የምርጫ ክልሎች ላይ የድምጽ መስጫ ወረቀት ዳግመኛ ኅትመት ማስፈለጉን ቦርዱ ጠቁሟል። የድምጽ መስጫ ወረቀት ዳግመኛ ኅትመት ያስፈለገባቸው የምርጫ ክልሎች በአፋር ክልል ስድስት ምርጫ ክልሎች፣ በአማራ ክልል ኹለት ምርጫ ክልሎች፣ በጋምቤላ ክልል አንድ ምርጫ ክልል፣ በሶማሌ ክልል 12 ምርጫ ክልሎች እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል 10 ምርጫ ክልሎች መሆናቸውን ቦርዱ አስታውቋል።

በሐረሪ ክልል በክልሉ መንግሥት በኩል በቦርዱ ላይ በቀረበው ክስ መሰረት ፍርድ ቤት የወሰነውን ውሳኔ ለማስፈጸም ቦርዱ ተጨማሪ ጊዜና ኅትመት ስለሚያስፈልገው የክልሉ ምርጫ ሙሉ በሙሉ በኹለተኛው ዙር እንዲካሄድ ተወስኗል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በድሬድዋ ከተማ አስተዳደር፣ በሲዳማ ክልልና በጋምቤላ ክልል ቀድሞ ሰኔ 14/2013 ይካሄዳል የተባሉ ምርጫዎች በተያዘላቸው ጊዜ እንደሚካሄዱ የቦርዱ ሰብሳቢ ጠቁመዋል። በጋምቤላ ክልል ድምጽ መስጫ ወረቀት ዳግመኛ ሕትመት ቢያስፈልግም በክልሉ ክረምት ከገባ ምርጫ ለማካሄድ አስቸጋሪ መሆኑን በመገንዘብ ችግሩ ተስተካክሎ ምርጫው እንደሚካሄድ ተመላክቷል።

በሌላ በኩል፥ የደቡብ ምዕራብ ሕዝበ ውሳኔ ከሰኔ 14ቱ ምርጫ በኋላ መራዘሙን ቦርዱ አስታውቋል። የደቡብ ምዕራብ ሕዝበ ውሳኔ ጳጉሜ 1/2013 እንደሚደረግ ነው ቦርዱ የገለጸው።
ቦርዱ ኹለተኛውን ዙር ምርጫ ጳጉሜ 1/2013 ለማካሄድ በጸጥታ ችግር ከመጀመሪያው ዙር የተስተጓጎሉ አካባቢዎችን መንግሥት የጸጥታ ችግሩን በፍጥነት እንዲሻሻል አስቻይ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩ ካላደረገ ከኹለተኛው ዙር ምርጫ ላይካሄድ እንደሚችልም ሰብሳቢዋ ጠቁመዋል።

በመሆኑም መንግሥት በተለይ በቤኒሻንጉል ክልል መተከል ዞን ያለውን የጸጥታ ችግር አስተካክሎ ተፈናቃዮችን ወደ ቦታው መመለስ ካልቻለ በኹለተኛው ዙር ምርጫ ለማካሄድ እንደማይቻልም ሰብሳቢዋ አክለው ገልጸዋል። በመሆኑም መንግሥት ከወዲሁ መሥራት የሚጠበቅበትን ሥራ በትኩረት ሠርቶ የጸጥታ ሁኔታዎችን በማስተካከል አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሚጠበቅበት ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የጸጥታ ተቋማትና አካላት ኃላፊነታቸውን በሚገባ በመወጣት የጸጥታ ችግሮችን ለማሻሻል እንዲረባረቡ ስብሳቢዋ ጥሪ አቅርበዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 136 ሠኔ 5 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here